እንኳን #ለማር_ቅዱስ_ሚናስ_ሰማዕት እና #ለሊቀ_ጳጳሳት_ቅዱስ_ሚናስ_ዳግማዊ፣ #ለቅዱስ_ቂርቆስ_ወቅድስት_ኢየሉጣ ለሌሎቹም ንዑዳን ክቡራን ክብረ በዓላት በሰላም አደረሳችሁ።
የኅዳር ፲፭ ዝክረ ቅዱሳን።
በዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
----------------------------------------------------------------
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
¶ አመ ፲፭ ለኅዳር በዛቲ ዕለት፥ ኮነ ሰማዕተ #ቅዱስ_ሚናስ ዘትርጓሜ ስሙ ምእመን ወቡሩክ።
✍️፩-ኅዳር ፲፭ በዚህች ዕለት የስሙ ትርጓሜ ቡሩክና የታመነ የኾነ #ቅዱስ_ሚናስ በሰማዕትነት አረፈ።
+ ይህም ቅዱስ አባቱ አባቅዮስ ከሚባል አገር ሲሆን ስሙም አውዶክስዮስ ነው። እርሱም አገረ ገዥነት ተሹሞ ሳለ ወንድሙ ተመቅኝቶት በንጉሥ ዘንድ ነገር ሠራበት፣ ንጉሡም ከዚህ አንስቶ ወደ አፍራቅያ አገር ሰደደውና በዚያም አገረ ገዥ አድርጎ ሾመው። እርሱም ደግና ለሰው አዛኝ፣ ለድኃ የሚራራ፣ የዋህ ነውና የአገር ሰዎች ኹሉ እጅጉን ይወዱት ነበር። እናቱም ልጅ ስላልነበራት በዚህ ታዝን ነበር። አንድ ዕለት ወደ እመቤታችን ቤተ ክርስቲያን በእመቤታችን በዓል ቀን ስትኼድ የክርስቲያንን ወገኖች ያማሩ ልብሶች ለብሰው ከልጆቻቸው ጋራ ደስ እያላቸው ሲገቡበየቻቸው። በእመቤታችንም ሥዕለ አድኅኖ ፊት እያለቀሰች ጽኑዕ ተማጽኖን ተማጸነች። ቡሩክ የሆነ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ልጅ እንድትሰጣት ተማጸነች። ከሥዕሏም አሜን የሚል ድምጽ ሰማች።
+ በኋላም ወደቤቷ ገብታ ለባሏ ይህን ነገር ነገረቸው፣ እርሱም የእግዚአብሔር ፈቃዱ ይሁን አለ። ከጥቂት ቀና በኋላ ይህ ደገ'ኛ መስተጋድል ሰማዕት ቅዱስ ሚናስ ተጸነሰ። ስሙንም ደግሞ ከሥዕለ ማርያም እንደሰማችው ስያሜ ሚናስ ብለው ጠሩት። ጥቂትም በአደገ ጊዜ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተማሩት። ዐሥራ ኹለት ኢኣነትም ሲሆነው፣ በመልካም ሽምግልና ኹኖ አባቱ አረፈ። ከርሱም በኋላ በሦስተኛው ዓመት እናቱ አረፈች። ቅዱስ ሚናስ ሰማዕቱም ብቻውን ቀረ።
+ መኳንንቱም አባቱን አብዝተው ከመውደዳቸው የተነሳ ቅዱስ ሚናስን በአባቱ ፈንታ ምስፍናን ሾሙት፣ እርሱም አምልኮተ እግዚአብሔርን እንዳጸና ቆየ። ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም ቸሩን የክብር ባለቤት ክርስቶስን በካደውና ሰዎች ጣዖታትን እንዲያመልኩ ጊዜ ብዙዎች ስለቸሩ ክርስቶስ ፍቅር ሰማዕት ኾኑ። ቅዱስ ሚናስም ይህን ሲሰማ ሹመቱን ትቶ ወደ ገዳም ገብቶ በታላቅ ተጋድሎ እየተጋደለ ለብዙ ዘመናት ኖረ። በአንዲቱም ዕለት ሰማያት ተከፍተውለት ለቅዱሳን ሰማዕታት የሚሰጣቸውን የብርሃን አክሊላት ሲያቀዳጇቸው ተመለከተ፣ እንዲሁም ስለክርስቶስ ስም በመከራ የደከመ ይህን አክሊል ይቀበላል የሚል ቃልን ሰማ። በዚያንም ጊዜ ወደ ከተማ ተመለሰና ክብር ይግባውና በክርስቶስ ስም ታመነ፣ እርሱም ከከበሩ ሰዎች ወገን ነበርና ኹላቸውም አብዝተው ለመኑት አባበሉት፣ መኰንኑም ብዙ ቃልኪዳን እየገባ ሊያባብለው ቢሞክር አልኾነለትም፣ ኋላም ባልሆነለት ጊዜ ጽኑዕ ሥቃያትን አሠቃየው፣ ቅዱስ ሚናስ ግን ልቡ ለቸሩ የክብር ባለቤት አምላካችን ጨክኖ ስለፍቅሩ ለመሞት መጥቷልና ልቡ ፈጽሞ አልተናወጸበትም። መኰንኑም ማሠቃየትን በሰለቸ ጊዜ ቅድስት ራሱን በሰይፍ ከሰውነቱ ይለዩዋት ዘንድ አዘዘ። ቅዱሱም የሰማዕትነትን አክሊል በመንግስተ ሰማያት ተቀበለ። (ቅዱሱ ሦስት አክሊላትን የተቀዳጀ ድንቅ መስተጋድል ሰማዕት ነው።) እርሱንም ተመልክተው ብዙዎች በቸሩ አምላካችን አምነው ሰማዕት ኾኑ። ከዚያም የቅዱስ ሚናስን ሥጋ ይዘው በእሳት እብዲያቃጥሉት መኰንኑ አዘዘና ሊያቃጥሉት ቢሉ አልኾነላቸውም። ምእመናንም ወስደው ዘመነ መከራው እስኪፈጸም በአማረ ቦታ አኖሩት።
+ ዘመነ ሰማዕታትም ካለፈ በኋላ የመርዩጥ አገር ሰዎች ከአምስቱ አገሮች ሠራዊትን ሊያከማቹ ወደዱ። የቅዱስ ሚናስንም ሥጋ ረዳት ይኾናቸው ዘንድ ከእርሳቸው ጋር ወሰዱት። በባሕርም ላይ በመርከብ እየኼዱ ሳሉ አንገታቸው እንደገመል ፊታቸው ደግሞ እንደከይሲ ያሉ አራዊት የቅዱስ ሚናስን ሥጋ ሊልሱ አንገታቸውን ሲያስረዝሙ ከቅዱስ ሚናስ ሥጋ እሳት ወጥታ በላቻቸው። ይህንም ተአምራት ያዩት ኹሉ በቅዱሳኑ ላይ ድንቅን የሚያደርገውን እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
+ ወደ እስክንድርያም ሊኼዱ ወደው የቅዱስ ሚናስንም ሥጋ ወደዚያ ሊወስዱ በገመል ጭነው ቢሉ ገመሉ አልንቀሳቀስም አለ፣ በሌላም ገመል ቢሉ አልኾነም። በመጨረሻም እግዚአብሔር የወደደው ቦታ መኾኑን አውቀው በዚያ በክብር ቀበሩት። ለብዙ ዘመናትም በዝዝያ ከኖረ በኋላ ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር አምላካችን የአንድ እረኛ ምክንያት በበጎቹ ገለጠው። የዚህም ዜና በሰኔ ዐሥራ አምስት ቀን ይተረካል፣ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በታላቁ ሰማዕት ማር ቅዱስ ሚናስ ጸሎት ይማረን፣ በረከቱም እጽፍ ኹና ትደርብን ለዘላለሙ አሜን።
ሰላም ለከ ሐራዊ መስፍን
ሰማዕተ መድኅን
ዘሰመየተከ ሚናስ ዘፆረተከ ማሕፀን
አመ ጸለየት ጸሎተ እንዘ ይእቲ መካ'ን
እምሥዕለ ማርያም ሰሚዓ ዘይቤ አሜን።
✍️፪-ዳግመኛም በዚህች ዕለት የእስክንድርያ ስሳ አንደኛው ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_አባ_ሚናስ_ዳግማዊ አረፈ።
+ ይህ ቅዱስ በታናሽነቱ ያለፍላጎቱ ወላጆቹ ሚስት አጋቡት። እርሱም የወላጆቹን ትእዛዝ ላለመተላለፍና እነርሱንም ላለማሳዘን ሥርዓቱን ኹሉ በቤተ ክርስቲያን ፈጸሙ። ይህ ኹሉ ግን ለርሱ ልክ እንደሕልም እንጂ እውነት እንደኾነ አያስብም ነበር። በኋላም ወደ ሙሽሪቷ አዳራሽ ሲገባ ትክ ብሎ ተመለከታትና እኅቴ ሰው ዓለሙን ኹሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ቢያጠፋ ምን ይጠቅመዋል። እንግዲህ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ ቃል ኪዳን እንድርግ አላትና ቃል ተገባቡ። በኋላም በዚያው ትቷት ወደ ገዳመ አስቄጥስ ገባና በአባ መቃርስ ገዳም ውስት በዚያ መንኲሶ በገድል ተጸምዶ መኖር ጀመረ። ከርሱ በፊት የነበረው ሊቀ ጳጳሳት ሲያርፍም ያለውዴታው በግድ ሊቀ ጳጳዳት አድርገው ሾሙትና በወንጌላዊው ማርቆስ ወንበር ተቀመጠ።
+ እርሱም መንጋዎቹን በቅን ፍርድ እየጠበቃቸውና እያስተማራቸው ዐሥራ ስምንት ዓመት ኑሮ በሰላም አረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ በረከቱም እጽፍ ድርብ ኹና ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ሰላም እብል ለሚናስ ዳግም
እንተ ለብሰ ፃማ በውስተ ገዳም
ወመነነ ኲሎ ፍትወተ ሥጋ ወደም
ረስዮ ከመ ጽላሎት ሀልዎተ ዝንቱ ዓለም
ወከመ ጽሙዕ ዘይሰቲ በሕልም።
ሰላም እብል ዘጳኲምዮስ ቤተ
ዘጸገወቶ ማርያም አዕባነ ብርሃን ክልኤተ
በዛቲ ዕለት ከመ አድምዐ መባሕተ
ጢሞቴዎስ አብ ቀደሰ ክሡተ
ወኢየሱስ ክርስቶስ አተበ መሥዋዕተ።
✍️፫-ዳግመኛም በዚህች ዕለት #የቅዱስ_ቂርቆስ_ሰማዕት ልደቱ ነው።
(ምንጭ፥ ስንክሣር ዘወርኃ ኅዳር)
----------------------------------------------------------------
ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው በእንተ ቅዱስ ማር ሚናስ ሰማዕት ወቅዱስ ሚናስ (ዳግማዊ) ሊቀ ጳጳሳት ወቅዱስ ቂርቆስ ሰማዕት ወእሙ ቅድስት ኢየሉጣ ወበእንተ ኲሎሙ ቅዱሳን እለኮነ ተዝካረ በዓሎሙ በይእቲ እለት መሐረነ ለነ ለአባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ አሜን።
እግዚኦ ተዘከር ኪዳን ዘወሀብኮሙ ለቅዱሳን አግብርቲከ ወአእማቲከ እለ አስመሩ ኪያከ፣ ወሶበ ተዘከርከ ዘንተ ተዘከር ከመ መሬት ንሕነ አባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ፣ ኢታርእየነ ሙስናሃ ለቅድስት ሀገሪትነ ኢትዮጵያ ወለቅድስት ቤተ ክርስቲያን። ኢታጥፍአነ ተዘኪረከ ዘትካት፣ ፍጡነ ይርከበነ ሳህልከ እግዚኦ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ