ዓርብ 20 ኖቬምበር 2020

የኅዳር ፲፪ ዝክረ ቅዱሳን።

እንኳን #ለማር_ቅዱስ_ሚካኤል_ሊቀ_መላእክት እና #ለቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ፣ #ለቅዱስ_ፊላታዎስ_ሊቀ_ጳጳሳት ለሌሎቹም ንዑዳን ክቡራን ክብረ በዓላት በሰላም አደረሳችሁ።

የኅዳር ፲፪ ዝክረ ቅዱሳን። 

በዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
----------------------------------------------------------------

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

¶ አመ ፲፪ ለኅዳር በዛቲ ዕለት፥ ተዝካረ በዓሉ #ለመልአክ_ክቡር_ወግሩም_ማር_ቅዱስ_ሚካኤል_ሊቀ_መላእክት #ርእሰ_ኲሎሙ_ኃይላተ_ሰማይ መሐሪ ወርኅሩኅ ለዘመደ ዕጓለ እመሕያው ወዘይቀውም ኲሎ ጊዜ ቅድመ መንበረ ዕበዩ ለእግዚአብሔር ወይተነብል በእንተ ኲሉ ፍጥረት።

✍️፩-ኅዳር ፲፪ በዚህች ዕለት ለሰው ወገን ኹሉ የሚያዝንና የሚራራ በእግዚአብሔር የጌትነት ዙፋን ፊት ኹል ጊዜ በመቆም ለፍጥረቱ ኹሉ የሚማልድ #የመላእክት_አለቃ #በሰማያትም_ለሚኖሩ_ኃይሎች_ኹሉ_አለቃቸው_የኾነ_ለማር_ቅዱስ_ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው።

  + ይህም ቅዱስ መልአክ በእለተ እሑድ ከተቀጠሩት ግሩማን መላእክት መኻከል የነገደ ኃይላት አለቃ ሲኾን ሳጥናኤል በትዕቢቱ ከመንበረ ክብሩ በወደቀና ጸጋውን በተገፈፈ ጊዜ በነገደ ሳጥናኤልና በሌሎቹም ግሩማን መላእክት ኹሉ ላይ ስልጣት የተሰጠው፣ በትሕትናው የተሾመ የዋህና ደግ ርኅሩኅ ለሚጠሩት ፈጥቶ የሚደርስ፣ ዘወትር ፍጥረቱን ለማስማር ሳይደክም የሚለንምንና የሚራራ፣ መልአከ ምክር የተባለና የቀደመውን እባብ ክፉውን ዲያብሎስን ከሠራዊተ መላኽት ጋር ኹኖ ወደ ጥቅሉ አውርዶ የጣለው ግሩም መልአክ ነው።

  + ይህን መልአክ ክብሩንና ገናንነቱን፣ የተአምራቱን ነገር፣ የርኅራኄውን ነገር እንደምን ይናገሩታል? እንደኔ ያለ በኃጢአት የተዋረደ ሰውማ በምን አንደበቱ ይናገረው ይኾን?

  + በዚህች እለት ቅዱሱ ግሩም መልአክ በቸሩ አምላካችን በእግዚአብሔር ታዝዞ የአሕዛብን ሠራዊቶቻቸውን ኹሉ ደምስሶ ኢያሪኮን ለነቅዱስ ኢያሱ ሊሰጣቸው መጥቶ ተአምራት ያደረገባት እለት ናት። ቅዱስ ኢያሱም ይህን ግሩም መልአክ እንደየመለከተው ደንግጦ በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደልት። መልአኩም አረጋጋው፣ ኢያሱም ጌታዬ ከእኛ ወገን ነህን ወይስ ከጣላቶቻችን ወገን ነህ አለው። መልአኩም መልሶ ኢያሱ የቆምህባት ምድር የተቀደሰች ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ ብሎ አዘዘው። (ምክንያቱም በዚያ የቆመው የቸሩን የእግዚአብሔርን ስም የተሸከመ ግሩም መልአክ ነውና በፊቱ ራስን ዝቅ ሳያደርጉና የተደከሙትን ኹሉ ነገር ሳይጥሉ መቅረብ አይገባምና) ቅዱስ ኢያሱም እንደተባለው አደረገ። መልአኩም እኔ ለሰማያውያን ኃይላት ኹሉ አለቃቸው ነኝ። የመጣሁት የአሕዛብን ኹሉ ኃይላት ድል አድርጌ ኢያሪኮን ለእናተ እሰጣችሁ ዘንድ ነውና አትፍራ ብሎ አጽናናው። 

  + የቅዱሳን ሰማዕታትን ዜና ሕይወት ልብ ብለን ስናስተውል ደጋግሞ ከሞትና ከሥቃይ የሚያድናቸውንና በመከራ እንዲታገሡ የሚራዳቸውን አንድ መልአክ እናገኛለን። ይኸምው ብዙውን ጊዜ ታላቁ ግሩም መልአክ ማር ቅዱስ ሚካኤል ነው። እርሱም ልባቸውን ለቸሩ አምላክ ስም ሳይሰስቱ ሰማዕታት እንዲኾኑ ጥቡዕ የሚያደርግላቸው ነው።

  + ዳግመኛም ይህ ቅዱስ መልአክ በዚህች እለት ድንቅ ተአምራት ያደረገበትም እለት ነው። ይኸምው ቴዎብስታ የምትባል ሚስት የነበረቸው አንድ ዱራታዎች የተባለ ሰው ነበር። ዘወትርም የዚህን የዋህ መልአክ ዝክር ይዘክሩ ነበር። ኋላ ግን በአካባቢው በተከሰተው ችግር ምክንያት ምንም ምን ለዝክር የሚኾናቸውን አጡ። (ወንድሞቼ እኛስ ሲቸግረን የምንጨነቀው ለምንበላ ለምንጠጣው ነው) ከዚያም ከሚስቱ ጋር ተስማሙና የኹለታቸውንም ልብስ ሽጠው ለዝክር የሚኾን ገንዘብ ለማምጣት ዱራታዎች ልብሶቻቸውን ይዞ ወደ ገበያ ሲኼድና በልውጥ ለማግኘት ብዙ ቢደክም አልኾንለት አለ፣ በዚህም አዝኖ ሊመለስ ሲል ይህ ደግ መልአክ ከመንገድ በመኰንን አምሳል ተገልጠለትና አጽናንቶ በርሱ ስም ዋስ ኾኖለት ከበግ ሻጩ በግ ከዓሣ ሻጩም ዓሣ እንዲወስድና የዓሣውን ሆድ ግን እስኪነግረው ድረስ እንዳይቀድ ነገረው። ከስንዴ ሻጩም እንዲሁ ስንዴ ወሰደ። በኋላም ቤቱ ደርሶ ቢያይ ቤቱ በድንቅ በረከት ተመልቶ አገኘና እጅግ ደስ ተሰኘ። ዝክሩን ከዘከሩ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል ከቤታቸው ተገለጠላቸው፣ (አቤት መታደል፣ ግሩም መልአክን የሚያስተናግድ ቤት ድንቅ ነው!)። ለዱራታዎስም የዓሣውን ሆድ እንዲቀደው ነገረው። በውስጡም ሦስት መቶ የወርቅ ዲናር አገኘ። እጅግ አደነቀ። መልአኩም ይህን ያደረገላቸው እርሱ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል መኾኑን ነገርቅቸው፣ ደንግጠው ከፊቱ ወደቁ፣ አጽናናቸውና ይህን ገንዘብ ያለባቸውን ዕዳ እንዲከፍሉና የቀረውን ለራሳቸው እንዲያደርጎ ነግሮ፣ ዝክሩን እንዳያቋርጡ አዟቸው አረገ። 

  + ይህች እለት በዓለ ሲመቱም ናትና በሚገ'ባ እናከብራት ዘንድ የተገባ ነው። በዚህች እለት ስለፍጡራኑ ኹሉ፣ ስለዝናማት፣ ስለቀላያት፣ ስለነፋሳትና ስለፍጡራን ኹሉ ሰላምን ምሕረትን ይለምናልና። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በማር ቅዱስ ሚካኤል ጸሎትና ምልጃ ይማረን፣ የመልአኩንም በረከት በኹላችን እጽፍ አድርጎ ያሳድርብን ለዘላለሙ አሜን።

ሰላም እብል ኪያከ መልአከ
ርኅሩኀ ልብ ለኲሉ እንተ ኢኮንከ ድሩከ
ሚካኤል ሊቅየ ለለእቤለከ
ኅብአኒ በጽላሎትከ ነግሀ ወሠርከ
እስመ እምንእስየ እፈርህ ሀከከ።

✍️፪-ዳግመኛም በዚህች ዕለት #የታላቁ_ነቢይ_ሰማዕት_ሐዋርያ_ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቀ_መለኮት ቅድስት ራሱ በደብረ ማህው የታየችበት ነው። በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ሰላም ለአስተርእዮትከ ውስተ ደብረ ማህው ዮም
ዘምስለ ዘይት ጥዑም
ቃለ ዓዋዲ ዮሐንስ ዘንብረትከ ገዳም
በትንባሌከ ተፈኒዎ እምሥዋዐ ልዑል አርያም
ሦከ ኃጢአትየ ያውዒ ሚካኤል ፍሕም።

✍️፫-ዳግመኛም በዚህች ዕለት የኢትዮጵያ ንጉሥ ደጉ ጻድቅ #በእደ_ማርያም የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።

  + እንዲሁ በዚህች እለት ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ስድሳ ሦስተኛ የኾነ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_አባት_አባ_ፊላታዎስ አረፈ።

ሰላም ለከ ፊላታዎስ ሐዋርያ
ሊቀ ጳጳሳይ ዘእስክንድርያ
በዕብሬትከ አንፈሱ ሕዝበ ኢትዮጷ
ድኅረ ተሠይመ ላዕሌሆሙ ብእሴ ጒህልያ
እስከ ጽኡላነ ኮኑ ወለፀር ህብልያ።

ሰላም ለከ መሳዌ ኀፃውንት ዘአድማስ
በእደ ማርያም ስኩር ወአኮ በሜስ
ከመ የሀሉ ዝክርከ እንበለ ፈሊስ
እለ ይሜህሩ ሃይማኖተ ሥሉስ ቅዱስ
ደቂቀ ክህነት ወንግሥ ፈረይከ እምከርሥ።

(ምንጭ፥ ስንክሣር ዘወርኃ ኅዳር)
----------------------------------------------------------------
ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው በእንተ ማር ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት ወበእንተ ዱራታዎስ ወቴዎብስታ ወበእንተ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ወቅዱስ ፊላታዎስ ወበእንተ ጻድቅ በእደማርያም ንጉሠ ኢትዮጵያ ወበእንተ ኲሎሙ ቅዱሳን እለኮነ ተዝካረ በዓሎሙ በይእቲ እለት መሐረነ ለነ ለአባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ አሜን። 

እግዚኦ ተዘከር ኪዳን ዘወሀብኮሙ ለቅዱሳን አግብርቲከ ወአእማቲከ እለ አስመሩ ኪያከ፣ ወሶበ ተዘከርከ ዘንተ ተዘከር ከመ መሬት ንሕነ አባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ፣ ኢታርእየነ ሙስናሃ ለቅድስት ሀገሪትነ ኢትዮጵያ ወለቅድስት ቤተ ክርስቲያን።  ኢታጥፍአነ ተዘኪረከ ዘትካት፣ ፍጡነ ይርከበነ ሳህልከ እግዚኦ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ