¶ "በቃላችን በአጋንንት ላይ ስሉጥ በኾነና ከፊታችንም አጋንንቱ ፈርተው ደንግጠው በሸሹ ጊዜ፣ አጋንንትን ስለ ገሠጸ እና እነርሱም ስለ ተገዙለት ማንም ሰው አይደነቅ። በእጆቹ እንዲህ የመሰሉ ነገሮችም በማይደረጉለት ሰውም ላይ ከቶ በንቀት አይነሳሳ፤ ኾኖም ከኹሉ አስቀድሞ የተለያዩ ሰዎችን ሕይወቶች እና ምግባራት ይመርምር ያስተውልም እንጂ። ከዚህም ጥልቅ ምርምር አምላካዊት ጸጋ ከማን ጋር እንደምትኖር እና የእግዚአብሔርም ጽድቅ በማን ላይ እንደያርፍ ያስተውላል፤ እነርሱም ደግሞ አጋንንትን ከሚያስወጡት ይልቅ የሚበልጥ መስተዋት ይኾንልናልና። ሰነፍ ሰው የአጋንንቱን ርኲሰታቸውንና ስለዚህም ደግሞ እንደሚገሠጹ መመልከት ሲቻለው፣ ደጎቹ ሰዎች ግን የአጋንንቱን አሠራራቸውን በሚገ’ባ መመርመር ይችላሉ። ከዚያም በተጋድሏቸው ይበረታሉ። አንድ ሰው የተከናወነ ፍጹም ገድለኛ መኾኑም ይኹን የተናቀ ሽቁጥቁጥ መኹኑ የራሱ ድርሻ ነው። በአጋንንት ላይ እጆቹን መዘርጋቱና የእነርሱም ከሥፍራው መሸሽ ግን የርሱ አይደለም፤ የሰማያዊት ጸጋ ነው እንጂ። ደቀ መዛሙርቱ እንዲሰብኩ የተላኩበትን ቅዱስ ወንጌል ሰብከው በደስታ ወደ ጌታቸው በተመለሱ ጊዜ፣ አጋንንትም እንኳ ለቃላቸው ስለ ተገዙላቸው ተደስተው ነበር። እንኪያስ ማንም ማስተዋል ያለ’ው ሰው ይኽንን ለእነርሱ የተሰጠውን መልስ ይመልከት፤ ያድምጥም። «ሰይጣናት ስንኳ ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ። ነገር ግን ስማችሁ በሰማያት ስለ ተጻፈ በዚህ ደስ ይበላችሁ እንጂ»/ሉቃ ፲፡፳/። እንግዲህ የስሞች በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ መጻ’ፍ እግዚአብሔርን በሚያስደሰት ምግባር ለመገ’ኘት ምስክር እና ለዚህም ነገር ለተገ’ቡት ደግሞ የቀና ልቡና ነው፤ በአጋንንት ላይ ያለ’ ስልጣን ግን በግልጥ የቤዛችንን ጸጋ [ትእምርት] ነው።" ¶
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ