ሐሙስ 1 ኖቬምበር 2018

"እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ" ( ዮሐ8፡12)

ቻናሉን በመቀላቀል እና ለሌሎችም በማጋራት እንማማር ዘንድ በትሕትና እጠይቃለሁ። ለወዳጆቻችሁም አጋሩ

https://t.me/deaconmelakuyifru/131

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
"እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ" ( ዮሐ8፡12)
➕➕➕➕➕➕➕➕➕➕➕➕

ሥግው ቃል መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ያለምክንያት አይደለም እኔ ብርሃን ነኝ የለው።ብርሃን የምንለው የሰውን ልጅ በትክክል ማየት እንዲችል የሚያደርገው ነው። የሰው ልጅ ብርሃን በህይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታና ጥቅም ካላቸው ነገሮች አንዱ እና ዋነኛው ነው።ይኸውም የሆነበት ምክንያት ለመረዳት ያስችለን ዘንድ ምሳሌ እንመልከት።

አንድ ሰው ቤቱን ሰርቶ ከጨረሰ በኋላ በቤቱ ውስጥ ለመኖርና የሚያስፈልጉትን ተግባራት ለማከናወን የግድ ብርሃን ያስፈልገዋል። ስለዚህም ሲል በቀን ከሆነ ፡_ ብርሃን ለማግኘት መስኮትና በር ይሰራል፡ በማታ ከሆነ ደግሞ ኩራዝ ወይም ፋኖስ ወይም ያሻውን እንደአቅሙ ሊጥቀም ይችላል። ይህንም የሚያደርግበት ምክንያት ጨለማ ባለበት ቦ ታ ፍርሃትና ጭንቀት ይነግሳል።ክፉና ደጉን መለየት አይቻልም፡ ተስፋ መቁረጥም ሊመጣ ይችላል። ለምሳሌ እግዚአብሔር ብርሃናትን ባይፈጥር እና የሰው ልጅም ካለምንም ብርሃን ህይወቱን ቢመራ ምን እንደሚከሰት ብናስበው ሰው ተስፋ አይኖረውም ነበር።ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ ይኖር ነበር። መሽቶ ከተኛ በኋላ የጠዋቷን ፀሐይ የማያያት ከሆነ ተስፋው ይመነምናል።ይህ ነበር እግዚአብሔር ብርሃናትን የመፍጠሩ አንዱ ምክንያት።ከዚህም በመነሳት ብርሃን የሚሰጣቸው ወሳኝ የሆኑ ጥቅሞች አሉ።

1ኛ. ፍርሃትና ጭንቀትን ያስወግዳል

ይኸውም ይታወቅ ዘንድ በየገዳማቱ በምንሄድበት ወቅት አምሳለ ሲኦል የሚባል ዋሻ ውስጥ ስንገባ በትክክል የሚሰማን ስሜት ፍጹም ጭንቀትና ፍርሃት ነው። ይኽም የሆነው ምንም አይነት ብርሃን ወደ ውስጥ ስለማይገባና ፍጹም ጨለማ ስለሆነ ነው። ከብዙ ፍርሃትና ጭንቀት በኋላ ልክ ከዚያ ዋሻ በወጣንበት ሰዓት ብርሃን ስናገኝ ሲሰማን የነበረው ጭንቀትና ፍርሃት ሁሉ ይጠፋል።ለምን?ብርሃን አግኝተናልና ነው።

2ኛ.መደረግ ያለበትን ተግባር በትክክል ማከናወን እንድንችል መንገዱን ያሳየናል

የሰው ልጅ የእለተ እለት ተግባሩን በትክክልና በተፈላጊው መንገድ ያከናውን ዘንድ ብርሃን ያስፈልገዋል።ያለዚያ ሊሰራው የፈለገውን ነገር በትክክል ማከናወን አይችልም። ምክንያቱም የሚፈልገውን ነገር ማንሳትና ማስቀመጥ ይቸገራል። ያለብርሃን ምንም ሊያደርግ አይችልም።

3ኛ በጨለማ የሰወረውን ነገር ደግም ሆነ ክፉ ያጋልጣል። በጨለማ የሰው ልጅ ሊሰርቅ ይችላል። በጎም የሆነ ስራ ሊሰራ ይችላል። ነገር ግን የሰው ልጅ ክፉ ስራን በግላጭ ለመስራት አይደፍርም። ምክንያቱም ኀፍረቱ ስለሚገለጥበት ነው። ታዲያ በዚህ ሰአት ብርሃን ክፉውን መልካም፡ ጥቁሩን ነጭ ወይም ወንዱን ሴት አድርጎ አያሳየንም።ይህም ማለት አይዋሽም ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነበር ቅዱስ ዳዊት ስለእግዚአብሔር ቃል ሲናገር ሕግህ ለመንገዴ መብራት ለእግሬም ብርሃን ነው ያለው።

4ኛ (ከላይ በምሳሌው በተገለጸው መሰረት) ተስፋን ያለመልማል
በዚህም መሠረት ነበር አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር ወልድ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ የለው። ይህም ሲባል መድኃኒታችን እርሱ ብርሃናችን ነው ። ያለርሱ ምንም ማድረግ አንችልም። (ዮሐ15፡5)

እርሱ የኛን ፍርሐትና ጭንቀት ያስወግድልናል። ከላይ በርዕሱ በተገለጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ የምናገኘው ታሪክም የሚነግረን ይሀንኑ ነው።ሴቲቱ ተከሳ ስትመጣ ፍጹም በሆነ ፍርሃትና ድንጋጤ ውስጥ ነበረች። ጸሐፍትና ፈሪሳውያኑ ግን የራሳቸውን በደል መመልከት ተስኗቸው በፍጹም ጭካኔ ለፍርድ አቀረቧት።ነገርግን መድኃኔዓለም እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ እንዳለው ለሁለቱም አበራላችው። ከሳሾቹም በደላችውን ተመልክተው ከፍርድ እንዲቆጠቡ እርሷም ከፍርሐቷ እንድትድን።

ለከሳሾቿ ከናንተ መካከል በደል የሌለበት አስቀድሞ ይውገራት ብሎ በደላቸውን እንዲመለከቱ አብርቶላቸዋል። ለዚህም ነበር ከሳሾቹ ሁሉ ተራ በተራ እየወጡ የሄዱት።

ለተከሳሿም እኔ አልፈርድብሽም በሰላም ሂጂ በማለት የማረጋጋት ብርሃንን አበራላት።ነገር ግን ምንም በዚህ ቃል ቢያረጋጋትም እውነተኛ ፈራጅ ነውና ደግመሽ አትበድይ በማለት በደለኛ እንደነበረች ነግሮ ተስፋ ሰጥቶ ሸኝቷታል።

ወዳጆቼ፡ እግዚአብሔር አምላካችን ሁላችንንም ይፈልገናል። በሕይወት እንድንኖር የርሱ የሁልጊዜም መሻቱ ነው። እርሱ ሊያበራልን በመፍቀድ (ማቴ11፡28 እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።) በማለት ይጠራናል። ምን ያህሎቻችን ፈቅደንለት በብርሃኑ ብርሃንን እያየን ይሆን? አንድ የቤት ባለቤት ቤቱን ከሰራ በኋላ ብርሃን ለማግኘት መስኮትና በር መክፈት ይኖርበታል። ይህን ማድረግ ካልፈለገ ግን ብርሃን ሊያገኝ አይችልም። ካላግኘ ደግሞ ከላይ የጠቀስናቸው ነገሮች ይከሰታሉ።

እኛም በሕይወታችን ትልቅ ፍሬን ማፍራትና መለወጥ የምንሻ ከሆነ የልባችንን በር በንስሐ ልንከፍተው ይገባል። የቤቱ ባለቤት የሚያገኘው የብርሃን መጠን በመስኮትና በሩ ስፋት ይወሰናል።ይህ ሁሉ የሆነው ግን ብርሃኑ አስገድዶት ሳይሆን በበጎ ፈቃዱ ለራሱ ጥቅም ሲል ነው። እግዚአብሔርም በህይወታችን የሚሰጠን ፍሬ ለርሱ ባሳየነው የትጋትና የድካም መጠንና ጥንካሬ ይወሰናል። ለዚህም ነው በመጽሐፍ ‘ ‘ኮከብ እም ኮከብ ይሄይስ ክብሩ” የተባለው።

ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት፡ የእመ አምላክ አማላጅነት የቅዱሳን ጻድቃን ተራዳኢነት አይለየን።

የቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት ከሁላችንም ጋር ይሁን።

ወስብሃት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር፡፡ይቆየን!
(በ2009 ዓ.ም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፋሲል ግቢ ጉባኤ ከተሰጠ ትምህርት የተዘጋጀ)
©ዘዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
2009ዓ.ም

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ