ማክሰኞ 6 ኖቬምበር 2018

➕➕➕ በእንተ መድኃኔዓለም ➕➕➕

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

. . . ለምን ተገለጠ፧. . . ድኅነተ ዓለም ለምን በሞት?. . . ከሞትም የመስቀል ሞት ለምን? . . . ለምን እርሱ ሆነ?. .

በአብ ስም አምኜ አብን ወላዲ ብዪ፣ በወልድ ስም አምኜ ወልድን ተወላዲ ብዬ፣ በመንፈስ ቅዱስ አምኜ መንፈስ ቅዱስን ሠራጺ ብዬ አምኜ፣ ምንም ለአጠይቆ አካላት(አካላትን ለማሳየት) ሦስት የምል ብሆንም መለኮቱ የሚያገናዝበው፣ አንዱ በአንዱ ሕልው፡ሁኖ የሚኖር አንድ አምላክ ብዬ በማመን ነገረ መስቀሉን ለማዘከር መናገር እጀምራለሁ። ለእመ ረከብክሙ ቀለመ ዘተናገርኩ በዘኢይደሉ አንትሙ አርትዑ ወኅድጉ ሊተ- በማይገባ የተናገርሁት ቀለም ብታገኙ ይቅር ብላችሁኝ ታቀኑት ዘንድ እጠይቃለሁ።

ነገረ መስቀሉን፣ ሥግው ቃልን የመከራውን ነገር ባሰበ ጊዜ የማይመታ ሕሊና፣ የማይጨነቅ አእምሮ፣ የማይንቀጠቀጥ ብረክ ፈጽሞ አይገኝም። በለምለም መስክ የሚመራቸውን እና ወደ እረፍት ውሃ የሚወስዳውን መልካሙን እረኛቸውን በጎቹ ሲገድሉት አይታ ምድር እንኳን ጨንቋት ስትንቀጠቀጥ ያየ ዐይን፣ ዐለታት የአንተን ቅዱስ ደም እንዴት ልንሸከም ይቻለናል ብለው ሲሰነጣጠቁ፣ ፍጥረት ሁሉ አንድ ሁኖ በመስቀል ከፍ ብሎ ዕርቃኑን ሁኖ በግፍ የተሰቀለው በእውነት ፈጣሬ ዓለማት መፍቀሬ ሰብእ ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ሲመሰክሩ ተመልክቶስ የርሱን አምላክነት የማይረዳና እጹብ ድብንቅ በማለት ለዚህ መጠን ለማይደኝለት ድንቅ ፍቅር በማድነቅ ምስጋና የማያቀርብና የማይገ'ዛ ማን ነው?!

#ለምን ተገለጠ
  + መፍቀሬ የዋሂይ ርግብ ቅዱስ ሕርያቆስ በቅዳሴው "ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት-ኃያል ወልድን ፍቅር ሳበው፤ እስከ ሞትም አደረሰው" በማለት በታላቅ ተመስጦ የሚነግረን ነገር ለዚህ ጥያቄ መልስ ነው። ኃያል አምላክን ማንም ማን #ሊመስለው እና በምንም በምን #ሊመሰል የማይቻል "ኅቡር ሕላዌሁ ነጽሮተ ገጹ ኪሩቤል (ምሉአነ አዕይንት) ኢይክሉ" የሚባልለት ድንቅ አምላክን እንደምስኪን ድሃ እንዲገለጥ ወደዚህ ታላቅ ትሕትና የሳበው ፍቅር ብቻ ነው። በዚያውም ላይ መፍቀሬ ሰብእ መድኃኔ ዓለም፣ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚገልጥልን "የተጠማ ሰው ለመጠጣት እንዲቸኩል እግዚአብሔርም (ከመዓት ይልቅ) ለምሕረት ይቸኩላል"ና ነው።
  + በመጽሐፍ ሐዋርያ ሊያስብል በሚያስደፍር ሁኔታ ሐዲስ ኪዳን ላይ አብሮ በአካል ጌታችን ከዋለበት ውሎ ካደረበት አድሮ ከርሱ የተማረውን እንደሚመሠክር እንደአንዱ የጌታ ደቀመዝሙር፣ ስለሐዲስ ኪዳን በሚያስደንቅ መንገድ የሚነግረን ቅዱስ ኢሳይያስም "የሟቹን ሞት አልፈቅድም" ብሎ እንደተናገረ በመግለጥ ቸርነቱን ይነግረናል።
  + ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ የደረሰልን መጽሐፈ አክሲማሮስም እንደሚነግረን በፍጥረት ሥርዓት ውስጥ ካሉት ከአሥራ ሁለቱ ነፋሳት ውስጥ የመዓት ነፋሳት የሚባሉት አራቱ ብቻ ናቸው። ይኸውም ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ እንዳለው "ርሑቀ መዐት ወብዙኃ ምሕረት" የሆነ መፍቀሬ ሰብእ አምላክ ነውና ስለዚህ ሊገለጥ ወደደ።
  + ከዚህ ላይ ጸረ አርዮሳውያን፣ የተዋሕዶ አርበኛ የሆነው ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ በነገረ ሥጋዌ ትምህርቱ የእኛ በመቅበዝበዝና በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ በክፋት ሠራዊት የማታለል ሥራ ውስጥ መኖርና አንድ ጊዜ አርአያ እግዚአብሔር የተሰጠን ሁነን ሳለን የዚህ ተካፋይ የሆን' እኛ ከፍጹም መጥፋት በፍጥነት እየተንደረድርን ሲያይ ይህን' ነገር ቸርነቱ ታግሳ ማየት ስላልቻለች ይህ መከራችን የሕያው ፍቊር አምላክን ፍቅሩን ጠራችው በማለት ይነግረናል። የተገለጠውም #ለድኅነተ ዓለም ነው እንጂ ለርሱ ምንም ምን ሊረባው አይደለም። አስቀድሞ ሰይጣን እንደኔ ያለ ድንቅ ፍጡር ስለማያገኝ ደግሞ ይመልሰኛል ብሎ በትዕቢት ቢናገር ማንም ማን ሊመስለው የማይቻል የአምላኩን አምሳል ገንዘብ ያደረገ ልዩ ፍጥረት ፈጠረ። ዳግመኛም አምላክ ትሆናለህ ብሎ ከክብር ቢያዋርደውም የሰይጣንን ተሳልቆ በራሱ በሰይጣን ላይ አደረገበትና ሥጋን አምላክ አደረገው። "ከመ ትንስቶ ለጸላኢ" እንዳለ ልበ አምላክ።

#ድኅነተ ዓለም በሞት ለምን?
+ ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ እንደሚነግረን፣ ሰው የተሰጠቸውን የጦም ሕግ በመሻሩ የመጣችበት ቅጣቱ በባሕርዩ የነበረችውን እና በርሱ ላይ ምንም ምን ስልጣን ያልነበራትን ሞትና ሙስና መቃብርን በርሱ ላይ እንድትሰለጥን ኃይልን አጎናጽፏታልና ይህ በንስሐ ብቻ የሚመለስ እንዳይደለ በጥልቀት ተንትኖ ያስረዳል። አዳም ሲፈጠር በመዋቲ እና በሕያው መኻከለኛ ሁኖ ነበር። ትእዛዙን ቢጠብቅና ቢታግሥ ኖሮ፣ ፍጹም ሕያውነትን ገንዘብ አድርጎ ሞትን ልክ እንደቀድሞው እንደሰለጠነባት ለዘለዓልም ሰልጥኖባት ይኖር ነበር። መቼም መች አታገኘውም ነበር። ነገር ግን በሠራው በደል የመጣበት ቅጣት ባህርያዊ ጉስቁልናን አምጥታበታለችና ይህች የጎሰቆለች ባህርዩ ወደ ቀደመ ክብሯ መመለስ ስላለባት ሞት አስፈለገ።
  + እግዚአብሔርም ፈታሔ በጽድቅ ኰናኔ በርትዕ ነውና የፈረደው ፍርዱም መፈጸም ስላለበት ሞት አስፈለገ።

#የመስቀል ሞት ለምን?
+ ይህን ለማስረዳት ከቅዱስ አትናቴዎስ ትምህርት በከፊል እንውሰድ።
  " . . . እርሱ አንገቱን የተቆረጠውን የዮሐንስን ዓይነት ሞት አልሞተም፤ እንደኢሳይያስም በመጋዝ አልተሰነጠቀም። ቤተክርስቲያንን ለሚከፋፍል ሁሉ ከዚህ በኋላ ምንም ዓይነት ምሕረት እንደሌለው ለማጠየቅ በሞቱ ጊዜ እንኳን አካሉን ሳይከፋፈል እንዳለ' ጠብቆታል።

✝️  . . . ክርስቲያን (ክርስቶስ) ለምን በመስቀል ሞት እንደተሰቃየ እና በሌላ መንገድ (ሞቱ) ለምን እንዳልሆነ ለማወቅ ቢፈልግ ይህንን እንመልስለታለን፥ ለእኛ የሚጠቅም(የሚበጅ) የሆነ ሌላ ምንም ምን ዓይነት መንገድ የለምና ጌታ ለእኛ ሲል በርግጥም እጅግ መልካም የሆነውን አንዱን ሞት ተቀበለ። በእኛ ላይ የወደቀውን ርግማን ሊሸከም መጣ፤ ታዲያ የተረገመውን ሞት በመቀበል ካልሆነ በቀር በሌላ መንገድ እንዴት "ርግማን"(ገላ 3፥13) ሊሆን ይችላል። እንዲሁም "በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው" (ገላ3፥13) ተብሎ ተጽፏልና ያ ሞት መስቀሉ(የመስቀል ሞት ነበር)።
✝️  ዳግመኛም የጌታ ሞት የሁሉም ቤዛ ነው፤ እናም "በመካከል ያለው የጥል ግድግዳ" (ኤፌ 2፥14) በርሱ ፈራረሰና የአሕዛብም መጠ'ራት ሆነ። ሰው እጆቹን ዘርግቶ ሊሞት የሚችለው በመስቀል ላይ ብቻ ነውና ካልተቸነከረ እንዴት ሊጠራን ይችላል? ዳግመኛም እዚህ ጋር የቀደሙ ሕዝቦቹን (እስራኤል ዘሥጋን) በአንዱ፣ አሕዛብን ደግሞ በሌላኛው እጆቹ ጠርቶ ሁለቱንም በርሱ አንድ ያደርጋቸው ዘንድ ነውና የእጆቹ መዘ'ርጋትና ሞቱን እንዴት የተመቸ(fitness) እንደሆነ እንረዳለን። ይህ ቢሆንም ቤዛ ስለሚሆን ስለሞቱ ሁኔታ አስቀድሞ "እኔም ከምድር ከፍ ያልሁ እንደሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ"(ዮሐ 12፥32) በማለት ራሱ ተናግሮ ነበር።

✝️   ዳግመኛም አየሩ፣ ከሰማይ ከወደቀ በኋላ የርሱን ዓመጽ(disobedience) ከሚጋሩት ክፉ መናፍስት ጋራ በመሆን ነፍሳትን ከእውነቱ ለመከልከልና እውነቱን ለመከተል የሚጠሩትንም (መንፈሳዊ) እድገታቸውን ለመግታት የሚደክመው የዘራችን ጠላት የሆነው የዲያብሎስ ግዛት (መነኻሪያ) ነበር። ሐዋርያውም ይህን ሲያመለክት ነበር ". . .በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ.  . ."(ኤፌ 2፥2) በማለት የተናገረው። ነገር ግን ጌታ ዲያብሎስን ይጥለው ዘንድ እና ሐዋርያውም እንደተናገረው "በመጋረጃው ማለትም በሥጋው.  . ."(ዕብ 10፥20) ወደ ገነት (ወደ ሰማይ) የምንወጣበትን "መንገድ" ሠራልን። ይህ ደግሞ መደረግ ያለበት በሞት ነው፤ ታዲያ በአየር ላይ በሚሆን ሞት ይኸውም በመስቀል ላይ ካልሆነ በቀር እንዴት ባለ' ዓይነት ሞት ይህ ሊደረግ ይችላል?

✝️   ዳግመኛም ጌታ መከራ መቀበሉ እንዴት ትክክለኛ እና የተገባ እንደሆነ ተመልከቱ። ስለዚህም "ከመሬት ከፍ" በማለቱ ከጠላት ክፉ ጫናዎች ሁሉ አየሩን ንጹሕ አደረገው። "ሰይጣንን እንደመብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ"(ሉቃ 10፥18) አለ፤ እና ስለዚህም ዳግመኛ "አርኅዉ ኆሀተ መኳንንት፥ ወይትረኃዋ ኆሀት እለ እም ፍጥረት፥ ወይባእ ንጉሠ ስብሐት - እናንተ መኳንንቶች፣ ደጆቹን ክፈቱ፥ የዘለዓለም ደጆች ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ"(መዝ 23(24)፥7) በማለት ወደገነት የሚወስደውን መንገድ ዳግም ከፈተልን። የሁሉም ጌታ ስለሆነ፥ የትኛዎቹም የርሱ ሥራዎች ሁሉ ለርሱ(ለሠሪያቸው) የተዘጉ አይደሉምና አካላዊ ቃል የደጆቹ መከፈት ለርሱ የሚያስፈልገው አይደለም። በፍጹም፤ ይህ ያስፈለገን በራሱ ሰውነት የተሸከመን እኛ ነን እንጂ። ይህንንም አስቀድሞ ስለሁሉ ፈንታ ለሞት አሳልፎ ሰጠውና ከዚያም በርሱው ወደገነት (ወደ ሰማይ) የሚወስደውን ጎዳና ሠራልን።" (St Athenasius on incarnation-Chapter 4)

#ይህን ለምን ሌሎቹ ማድረግ አልቻሉም?

+ ይህንንም ለማድረግ እና ደቂቀ አዳምን ከሞት ነጻ ለማድረግ፣ ፍጹም ሕያው የሆነ እና በሞት የማይሸነፍ አካል ያስፈልጋል። ስለዚህ ባለዕዳ ባለዕዳን ካለበት ብድር ዕዳ ነጻ ሊያደርገው እንደማይችል ሁሉ በዕዳ ውስጥ የነበሩት የኦሪት ካህናትና ነቢያት ደቂቀ አዳምን መታደግና ወደ ቀደመ ክብሩ መመለስ አልቻሉም።
+ ይህ የሚያድነው አካል ደግሞ መስዋዕት ለመሆን መሞትና መነሳት በዚህም ሞትን መግደል አለበት። መላእክት ደግሞ በባህርያቸው የማይሞቱ ናቸውና ስለዚህ መላእክት አልሆኑም። ይህም ብቻ ሳይሆን የበደለው የሰው ልጅ ስለሆነ ካሣ መክፈልም ያለበት የዚያ ወገን የሆነ ይኸው ሰው የሆነ ነውና ስለዚህ አዳኙ ሲገለጥ የሰውን ዕዳ የሚከፍል የሰው ወገን ዘመድ ሁኖ ሳለ ሕያው የሆነ ሞት የማያሸንፈው መሆን ይኖርበታል። ይህን ደግሞ መላእክት ማድረግ አይቻላቸውም።
+ ከሦስቱ ሕያዋን ፈጣሬ ዓለማት አጋእዝተ አለም ሥሉስ ቅዱስ ደግሞ ለምን እርሱ ተገለጠ ትለኝ እንደሆነ፣ አካላቸው ስማቸው ስማቸው ግብራቸው ነውና የአብ አካላዊ ግብሩ መውለድ ብቻ ስለሆነ ዘለአለም አብ ሲባል ይኖራል እንጂ ወልድ ወይም መንፈስ ቅዱስ ሊባል አይቻልም። የወልድም አካላዊ ግብሩ መወለድ ነውና በተለየ የአካል ግብር ስሙ ዘለዓለም ወልድ ሲባል ይኖራል እንጂ አብ ወይም መንፈስ ቅዱስ ሊባል አይቻልም። መንፈስ ቅዱስም በተለየው የአካል ግብር ስሙ መንፈስ ቅዱስ እንጂ አብን ወይም ወልድን ሊባል አይቻልም። ስለዚህም ከአብ አብን አህሎና መስሎ ከርሱ የተገኘው ወልድ ከአብ ተለይቶ የኖረበት ጊዜ የለም። ስለዚህ አብ ወልድን በመውለዱ በአካል ግብር ስሙ አብ ሲባል ይኖራል። ወልድም ከአብ ያለመቀዳደም በመገኘቱ ዘለዓለም ወልድ ሲባል ይኖራል። ስለዚህም በማኅፀነ ማርያም ሊያድርና ሊወለድ የሚገባው አካላዊ ቃል ወልድ ነው። እርሱ ሲወለድ ሥላሴ በፈቃድ አንድ ናቸውና በሦስቱም ፈቃድ ነው። #ድኅነተ ዓለም #ሥምረተ ሥላሴ ፈቃደ ሥላሴ ናትና። ይህቺ ሥምረተ ሥላሴ ግን በግብር የተፈጸመበት መወለድ ግብሩ የሆነው አካላዊ ቃል ወልደ እግዚአብሔር ነው።
  + እንግዲያማ ይህ በተለየ አካሉ ለድኅነተ ዓለም ለኩነተ ሥጋ የተገለጠው ወልደ እግዚአብሔር እግዚአብሔር ነዋ።
ይህ ገርሞት ደንቆትኮ ነው ማር ሶርያዊ ቅዱስ ኤፍሬም "ንዑ ርእዩ ዘንተ መንክረ፤ ወዘምሮ ዘምሩ በእንተ ምሥጢር ዘተከሥተ ለነ እስመ ዘኢይሰባእ ተሰብአ ቃል ተደመረ ወዘአልቦ ጥንት ኮነ ቅድመ ወለዘአልቦቱ መዋዕል ኮነ ሎቱ መዋዕል - ኑ ይህን ድንቅ ተመልከቱ፤ ሰው ያልሆነ እርሱ ሰው ሁኗል ቃል ተዋሕዷልእና ጥንተ የሌለው (ሥጋ አዳም) ከቀድሞ ጀምሮ የኖረ ተባለ ዘመን የማይቆጠርለት (መለኮት) ዘመን የሚቆጠርለት ሆኗልና ስለዚህ ድንቅ ምስጢር መዘምርን ዘምሩ" በማለት ያመሰግናል።

ኦ መድኃኒታችን ስላፈሰስኸው ደምህ፣ ስለአማኑኤል ስምህ፣ ስለድንግል ርኅርኅተ ሕሊና የዋሂት ርግብ እናት ስለጻድቃን ቅዱሳን ወዳጆችህ ብለን በኃጢአት የተዳደፍን እኛ በደለኛ ልጆችህን እንደቸርነትህ ብዛት ማረን ይቅድ በለን። አሜን በእውነት ያለሐሰት ይሁን ይደረግልን።
ይቆየን።
©ዘዲያቆን መልአኩ ዘውሉደ ብርሃን
ጥቅምት ፳፯-፳፻ወ፲፩ ዓ.ም
ሲቹዋን ቸንዱ/ ቻይና

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ