ረቡዕ 7 ኖቬምበር 2018

❤️ የቅዱስ እንጦንስ እና የሰይጣን ቃለ ተዋስዖ ❤️

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

    + + +              + +  + +               + + +

ምንጭ፥ paradise of the holy fathers
               (መጽሐፈ ገነተ አበው ቅዱሳን)
ትርጉም፥ ዲያቆን መልአኩ ይፍሩ ዘውሉደ ብርሃን

❤️ . . . ዳግመኛም ጠላት በዚህ ትግል ድል እንደተደረገ እና ማታለሉም በጻድቁ ሰው ሐሳብ(ልቡና) እንደተናቀ እና እንደተወገደ ባየ ጊዜ፣ ጥርሱን አፋጨና ምናልባትም በማስፈራራትና በማስደንገጥ ፈቃዱን የሚፈጽምበት ዕድል አገኛለሁ በማለት ጮኸና ለጻድቁ ሰው ውሳጣዊ ክፋቱን በግልጥ አሳየው። በቅዱስ እንጦንስ ፊትም እንደ አንድ የህንድ(ጥቁር) ወንድ ልጅ ሁኖ ተገለጠና እንዲህ ይለው ጀመር "ማንን ታያለህ? መጥቻለሁ እናም እቆማለሁ፤ አንተንም አሸንፍህና ሌሎቹን እንዳደረግሁ አንተንም የተዋረድህ የወደቅህ አደርግሀለሁ"። እኒህን ቃላት እየተናገረምን ሳለ ንዑድ ክቡር የሆነ እንጦንስ በራሱ ላይ በትዕምርተ መስቀል ምልክት አማተበና ፍርሐቱን ተወ፤ ጠላትም የመስቀሉን ምልክት ዐይቶ ፈራ(ደነገጠ)። በዚህም ጊዜ ጻድቅ እንጦንስ (ሰይጣን) እንደፈራ ሲመለከት እንዲህ በማለት ይጠይቀው ጀመር "ማነህ አንተ እናም እንዲህ ያሉትን ቃላት በእኔ የሚሰ'ሙት በማን ድምጽ ነው?" ከዚያም ጠላት በሚዝት(በሚደነፋ) ሰው ዓይነት ኹኔታ እንዲህ ይለው ጀመር " እኔ፣ እኔ እንኳን ስሕተትንና ዝሙትን እወዳለሁ፤ እናም እኒያን (የሐሳብ) ውጊያዎችና ሽንገላዎች (ወደ ሰው ልጅ ልቡና) የማመጣ (የምጨምር) እኔ ነኝ። ብዙዎችን ወደ ስሕተት እንድወስድ (የምተጋ) እኔ ነኝ፤ እንዲሁም ማንኛውንም ሰው እዋጋለሁ፤ የጽድቅ ተቃዋሚ ነኝ። ነቢዩም እንኳ እንዳለው 'የዝሙት(የግልሙትና) መንፈስ'(ሆሴ፬፥፲፪) እኔ ነኝ፤ በእኔ የተደናቀፉ ሁሉ ወደ ስሕተት ገብተዋልና። ለብዙ ጊዜያት አንተንም የጎዳሁህ እኔ ነኝ፤ አንተም በሁሉም ነገር በእኔ ማዋረድ ተፈትነህ ነበር"

❤️   ብጹእ የሚሆን እንጦንስም እግዚአብሔርን አመስግኖ ታላቅ የሆነ ብርታት አገኘና እንዲህ አለ "ጠላቴ ሆይ የመስቀሉን ኃይል ለመቋቋም (የሚሆን) በአንተ ውስጥ ያለ እንደምን ዓይነት ኃይል አለና እንዲህ አሰብህ? በባህርይህም ጥቁር ነህና በቅጣትም እንደተ'ናነሰ ምስኪን ሕጻን ልጅ ደካማ ነህና እንዲህ ባለ'ው ሁኔታ በህንዳዊ (ጥቁር) ሕጻን ልጅ መልክዕ መገለጥህ ትክክል አድርገሃል። አንተ በእኔ ዘንድ እንደተናቀ ነህ፤ እናም በሽንገላዎችህ (በማስፈራራትህ) አልደነግጥም። ጌታዬም ረድቶኛልና በጠላቶቼ ላይ (በድል) እሰለጥንባቸዋለሁ"። ያም ጥቁን ነገር እሊህን ቃላት በሰማ ጊዜ፣ ከእንጦንስ ፊት ፈጥኖ ጠፋ። ይህም ቅዱስ እንጦንስ ከጠላቱ ጋር ያደረገው የመጀመሪያው ክርክር ነው። ይልቁንም ይህን እንጦንስ ለመርዳት፣ በሥጋው ኃጢአትን ድል ካደረገ እና የሕጉ ቅድስና በእኛ ውስጥ ይመ'ላ ዘንድ እንዲሁም ከመንፈስ በኋላ እንጂ ከሥጋ በኋላ እንዳንጓዝ ከአዳኛችን (ከቤዛችን) የተደረገ የመጀመሪያው ርዳታ ነው።(ሮሜ፰፥፬)
                        ይቆየን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር።

©ዘዲያቆን መልአኩ ዘውሉደ ብርሃን
ጥቅምት ፳፰/ ፳፻ወ፲፩ ዓ.ም
ሲቹዋን ቸንዱ/ ቻይና

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ