ሐሙስ 1 ኖቬምበር 2018

ዳሰሳ ዘመጽሐፈ በርለዓም ወየወሴፍ


💌(ዲ/ን መልአኩ ዘውሉደ ብርሃን)
         ✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

✝️ መጽሐፉን ተርጉሙ ለዚህ ላደረሰልን እና እኔንም ለማንበብ እድለኛ ላደረገኝ ዲ/ን የሺዋስ መኳንንት ምስጋና ይግባውና ጀምሬ እንዳያልቅብኝ እየተመኘሁ እየቆጠብሁ ባለበውም እንኳ ምኞቴ ሳይሳካ እንደጓጓሁ ካለቁብኝ ልዩ መጻሕፍት መኻከል አንዱ ይህ መጽሐፈ በርለዓም ወየወሴፍ አንዱ ነው። ከመጽሕውፉ የሽፋን ገጽ ሥዕል ጀምሮ እስከ መጽሐፉ የውስጥ ክፍል የቃላት አመራረጥ ድረስ ጽሑፉን ለአንባቢዎቹ ቅርብ ለማድረግ ያደረገውን ጥረትና ጥንቃቄ ሳላደንቅ አላልፍም።
   
    ሙሉ መጽሐፉ ልዩ በሆነ አቀራረብ የቀረበ ሲሆን ተርጓሚውም አስቀድሞ ስለመጽሐፉ ፋይዳ በመግለጥና ስለጸሐፊው የሚገባውን ማብራሪያ በመስጠት ነው የሚጀምረው።

    ትረካውንም ከአሥራ ሁለቱ ብርሃናተ ዓለም አንዱ የሆነውን የሐዋርያው ቅዱስ ቶማስን ወደ ሕንድ መምጣት በመናገር ጀምሮ በሕንድ ከዚያ ጀምሮ እየተስፋፋ ስለነበረው የክርስትና ሃይማኖት በማተት ከዚያም ስለተነሳ አንድ ዓላዊ ንጉሥ በመናገር ወደ ትረካው ዋናው ክፍል ይገባል። ንጉሡም የነበረበትንም ሁኔታ ሲገልጥ ለጣዖት አምልኮ የነበረውን ፍቅር እና ክርስቲያኖችንም የሚያሳድድ እና በተለይም ምንኲስናን እጅግ የሚጠላ እንደነበር በመናገር ነበር።
    ይህም ንጉሥ ልጅ ይወለድለትና ታላቅ የደስታ በዓል በማድረግ ስለልጁ የወደፊት ሕይወት እንዲነግሩት ለመጠየቅ የታወቁ ጠቢባን የተባሉትን ኮከብ ቆጣሪዎች ከየአቅጣጫው አስጠርቶ በቤተመንግሥቱ እንደጋበዛቸው እናነባለን። ሌሎቹ ኮከብ ቆጣሪዎች ስለልጁ፣ ወደፊት፣ ከቀደሙት ነገሥታት የበለጠ ጠንካራ እና ሀብታም የሆነ ንጉሥ እንደሚሆን ሲነግሩት ከነርሱ ወገን ከሁሉም በትምህርቱ የላቀው ኮከብ ቆጣሪ ግን ልጁ የክርስትናን ሃይማኖት እንደሚቀበልና ከዚህም (ከነገሥታቱ) ወንበር በሚልቅ ወንበር ላይ እንደሚቀመጥ፣ ከዚያም ሐሳቡ ማንም ማን ሊያናውጠው እንደማይችል ይነግረዋል። ንጉሡም ይህን ከሰማ በኋላ ለብዙ ጊዜያት አእምሮው ስለተረበሸ ልጁን ከቤት እንዳይወጣ እና ምንም ዓይነት ችግር ነክ የሆኑ ነገሮች ለምሳሌ ሞት፣ ረሐብ፣ የመሳሰሉ የችግር ሁኔታዎችን እንዳያውቅ በማድረግ ደብቆ ያሳድገው ነበር።
    ይህን ሁሉ እና ከዚህም የላቁ ሌሎችንም ጥንቃቄዎች ቢያደርግም ግን ንጉሡ ልጁን ከዚህ ጥያቄ መፈ'ጠር ሊከለክለው አለመቻሉን እናነባለን። ከዚያም በኋላ ከቤት ወጥቶ ለመጎብኘይ እንደሚሻ ንጉሡን በመጠየቅ ወጥቶ ሲዘዋወር በጠባቂዎቹ ስሕተት ምክንያት አንድ ሽማግሌ አይቶ ስለሽምግልና ምንነት በመጠየቅ እንዳወቀ እና ሞት የሚባል ነገር መኖሩንም ሲያውቅ ሐዘን እንደገባው ይነግረናል።

    ለነዚህ የልብ ጥያቄዎቹ መልስ ለማግኘትና ከሐዘኑም ለማረፍ በሚፈልግበትም ጊዜ የጥበብ ባለቤት ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር ለታላቁ በርለዓም ለተባለው መናኝ ይህን ገልጦለት በርለዓም ራሱ ከነበረበት በረሓ ወጥቶ ወደ ቤተ መንግሥት ያደረግውን ጉዞ ይተርካል። በርለዓም እንዴት ባለ' ጥበብ ወደ ቤተ መንግሥት እንደገባ እና የወሴፍን በምን ሁኔታ እንዳገኘው በመተረክ ይቀጥላል።

   ከዚያም በማስከተል ሰፊውን የመጽሐፉን ክፍል የሚይዘው፣ ጥልቅ የሆኑ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች የተዳሰሱበትና ልዩ ተመስጦ ውስጥ የሚከተው የበርለዓም እና የየወሴፍ ቃለ ምልልስ ነው። በዚህም ውስጥ በሚያስደንቅ ሁኔታ የተገለጡ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ተዳሰውበታል። ለአብነትም ያህንል ስለሀልዎተ እግዚአብሔር፣ ስለሰው ነጻ ፈቃድና ነገረ ድኅነት፣ ስለምስጢራተ ቤተክርስቲያን፣ ስለቅዱሳት ሥዕላት፥ የቱን ትቼ የቱን አንስቼ መዝለቅ ይቻለኝ ይሆን? ብቻ ምን አለፋችሁ ድንቅ የሆነ ትምህርታዊ ትንታኔ የተሰጠበት ቃለ ተዋሥኦ ነበር።

    ከዚህም አለፍ በማለት የበርለዓምን ወደ በረሓ መመለስ ይነግረንና በርለዓምና የወሴፍ ከተለያዩ በኋላ፣ የወሴፍ ከበርለዓም በመለየቱ ያሳለፈውን የሰቀቀን ጊዜ፣ የሚያስደንቀውን የሠለስቱ ደቂቅን የእነቅዱስ እስጢፋኖስንና ድንቅ የሆኑትን የእነቅድስት አርሴማ ዓይነት ጽኑዕ የሆነውን የየወሴፍን መንፈሳዊ ተጋድሎ በመተረክ ይቀጥላል። ንጉሡ የልጁን ክርስቲያን መሆን ባወቀ ጊዜ ከጎዳናው ሊያስተው የተጠቀመባቸውን እጅግ ከባድ የሆኑ ፈተናዎችና ጥበቦች፣ የወሴፍም እነዚያን እንዴት በጥበብና በጸሎት እንዳለፋቸው፣ ንጉሡም በተንኮል ያመጣው በርለዓም ነው ተብሎ በውሸት እንዲመሰክር የቀረበው ጠንቋይም እንኳ ስሑታንን ለማሳፈስ እግዚአብሔር በዚያ ጠንቋይ አድሮ  ያስተማረውን ድንቅ ትምህርት እና ጠንቋዩም ከዚያ ክፉ ሥራው ወጥቶ ወደ እውነት ስለመምጣቱ፣ የወሴፍ በዚህም የተጋድሎ ጽናቱም የተነሳ አባቱንና የሚገዛቸውን ሕዝቦች እንዴት ወደ እውነት እንደመራቸው፣ ብቻ ምን ልበላችሁ ገድለ ሰማዕታቱን እዚሁ ታገኙታላሁ።

   በመጨረሻም የወሴፍ በእነቅዱስ መቃርስ እና ቅዱስ እንጦንስ ዓይነት አነዋወር እንዴት እንደኖረ፣ የገጠሙት የሰይጣን ፈተናዎችና ያለፈበት መንገድ ከዚያም የሕይወቱን ፍጻሜ እና ሌሎችንም ጥቃሚ ትምህርቶች በመግለጥ ትረካውን ይቋጫል።
    ከላይ በከፊል ለመዳሰስ ከሞከርሁትም በላይ የሆኑ ድንቅ ድንቅ የጥበብ ምሳሌዎችና ትምህርቶችን የያዘ ልዩ መጽሐፍ ሲሆን መጽሐፉን ተርጉሞ ለዚህ ያደረሰልንን ውድ ወንድማችን ዲ/ን ዶ/ር የሺዋስ መኳንንትን ከልብ እያመሰገንሁ፣ መጽሐፉን ያላነበባችሁ እንድታነቡት፣ ያነበባችሁ እንድትደግሙት፣ ላላነበቡትም ወዳጆቻችሁ ሁሉ እንድትጋብዙት በመጋበዝ  ይህቺን የብርሃን ጭላንጭል የሆነች ጦማር ከዚህ አበቃለሁ።
❤️   ውድ ወንድሜ ዲ/ን የሺዋስ እንደስምህ የሺዎች ዋስ የሆነ መጽሐፍን አበርክተህልናልና አዛኝት ዋስ ጠበቃ ቅዱሳን ሁሉ ከለላ ይሁኑህ፤ ብዕርህን ታለምልምልህ። ዳግም በሌላም ሥራ እንደምንገናኝ ጽኑዕ እምነቴ ነው።
    
                    ©ዲያቆን መልአኩ ይፍሩ ዘውሉደ ብርሃን
                                መስከረም 21-2011 ዓ.ም
                                 ናዝሬት አዳማ/ ኢትዮጵያ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ