ሔዋኔ!
(በዲያቆን መልአኩ ይፍሩ)
እግዚአብሔር አክብሮኝ ከፍጥረታቶቹ፣
በአርአያው በአምሳሉ ሠርቶኝ በእጆቹ፣
ስኖረ በገነት ውስጥ እርሱ እንደፈቀደ፣
ብቻዬን ነኝና ሔዋንን ከጎኔ ሊፈጥር ወደደ።
ታዲያም
በማእከለ ነዊም ወነቂህ ሳለሁኝ፣
ከጎኔ አጥንት ወስዶ አጋር ፈጠረልኝ፣
አጥንትሽ ከአጥንቴ ሥጋሽ ከሥጋዬ፣
መሆኑን አውቄ ጠራሁሽ ሴት ብዬ።
አምላክም
ትዕዛዝን ሰጠኝ በርሱ እንድታመን፣
ፍጡር ለፈጣሪው ይታዘዝ ዘንድ ሲሆን፣
ከገነት ዕፅዋት ሁሉ ተፈቅዶልኝ፣
አንዲቱ በለስ ግን ለሕግ ተሰጠችኝ።
በዚህም ታምኜ ሰባት ዓመት ኖሬ፣
በእባብ አድሮ መጣ ያ ርኲስ ክፉ አውሬ፣
ወደኔ ቢመጣ፣
ሊያስተኝ ቢቃጣ፣
እኔ ሳሳፍረው አንቺ ተቀበልሺው፣
ምን ነበር ሔዋኔ ምክሩንስ ባትሰሚው?!
ከገነት ተባረርኩ፣
ከዕፀ ሕይወትም እንዳልበላ ታገድሁ።
አይ ሔዋን!?
በመጨረሻው ሰዓት ደግሞ በሱባዔ
ንስሓ ገብቼ ልታረቅ አምላኬን
ዲያብሎስ መጣና ገብርኤል ነኝ ብሎ፣
አሁንም ሲጠራኝ የተላከ መስሎ፣
አልቀበል ብለው ወዳንቺ ሲመጣ፣
ፈጥነሽ ለቀሽ ወጣሽ ምሕረት ሳይመጣ።
እሺ!
እሺ ይሁን ብዬሽ ተቀብለን ሄደን፣
ከገነት መግቢያዋ ከደጃፏ ደርሰን፣
ዲያብሎስ መሆኑን ገልጦ ነገረን፣
ምናለ ሔዋኔ አሁንስ ቢበቃን?
ግና! . . . . ግና!
አምላክ መድኃኔዓለም መሐሪ ነውና
መቶ ዓመት ጸሎት ሱባዔ ገብቼ፣
የኛን በደል ሊፍቅ በልጅ ልጅ ልጆቼ፣
ቃልኪዳን ገባልኝ መጣሁ ተደስቼ።
ሔዋኔ!
አሁን ላመስግንሽ
በክራር መሰንቆ ዜማ ልቀኝልሽ።
ቀድሞ በበደልሽ እጅጉን ሳማርር፣
አምላክን ወለድሽው በዚህች ትንሽ ምድር?!
ወይ ተአምር!
በአንቺው ወድቄ በአንቺው ልድን ነው?
አቤት አቤት አንተው!
አምላኬ ሆይ
ቸርነት ምሕረትህ ብዙ ነበር ለካ፣
በሔዋን ጠፍቼ ደግሜ በርሷ ልተካ፣
አምላክን ታቅፈሽ ጡትሽን አጥብተሽ፣
የሕይወቴን ብርሃን ይኸው ወልደሽ ሰጠሽ።
ሔዋኔ!
አሁን ላመስግንሽ፣
በክራር መሰንቆ ዜማ ልቀኝልሽ!
የተገባልኝ ቃል አምስት ቀን ተኩል፣
እንሆ በአንቺ ይኸው ተፈጽሟል።
ይደንቃል!
በአንቺ ምክንያት የሞት ሞትን ሞትኩኝ፣
ዳግመኛም በአንቺ ሕይወት አገኘሁኝ፣
እግዚአብሔር ይመስገን አንቺን ስለሰጠኝ፣
በአንቺም ምክንያት ከሞት ስላዳነኝ።
ፍጥረት ዘመረልሽ፣
አምላክ በመውለድሽ፣
ሕይወት በመያዝሽ፣
ድኅነት ስላመጣሽ፣
ሔዋኔ
አሁን ላመስግንሽ፣
በክራር መሰንቆ ዜማ ልቀኝልሽ።
ተጻፈ፡ በዲ/ን መልአኩ ይፍሩ ዘውሉደ ብርሃን
፳፻ወ፩ ዓ.ም
(የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ከጻፍኋቸው አንዲቱ። ለጊዜው ከመጻፍ ጋር ብንራራቅም ታነቧት ብዬ አጋራኋት።)
©ዲያቆን መልአኩ ዘውሉደ ብርሃን
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ