የኅዳር ፲፰ ዝክረ ቅዱሳን።
በዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
----------------------------------------------------------------
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
¶ አመ ፲፰ ለኅዳር በዛቲ ዕለት፥ ኮና ሰማዕተ #ቅዱሳት_ደናግል_አጥራስስ_ወዮና።
✍️፩-ኅዳር ፲፰ በዚህች ዕለት #ቅዱሳን_ደናግል_አጥራስስ_እና_ዮና በሰማዕትነት አረፉ።
+ እሊህም ቅዱሳን በአንድነት ሰማዕትነትን የተቀበሉት በዚህች ዕለት ነው። ቅድስት አጥራስስ ጣዖታትን ለሚያመልክ ንጉሥ ለእንድርያኖስ ልጁ ስትሆን አዳራሽ አሠርቶ ከማንም እንዳትገናኝ አድርጎ ለብቻዋ አኖራት። እርሷ ግን ስለዚህ ዓለም ከንቱበት ታስብ ነበርና በልቡናዋ ቸሩን አምላክ ትፈልግ ስለነበር እውነተኛውን ጎዳና ይመራት ዘንድ የእውነት በተመስጦ ትለምነው ነበር። ከልመናዋም ጽናት የተነሳ አንድ ቀን በራእይ "ወደ ፍላጽፍሮስ ልጅ ወደ ድንግሊቱ ዮና መልእክት ላኪ፣ እርሷ የእግዚአብሔርን መንገድ ትመራሻለች" የሚላትን አየች። ስትነቃም በልቧ እጅጉን ደስ ተሰኘች።
+ መልእክተኛም ልካ ድንግሊቱን የፍላጽፍሮን ልጅ የሆነችውን ቅድስት ዮናን አስጠራቻት። እርሷም ስትመጣ ከእግሯ በታች ሰገደችላትና እውነተኛውን መንገድ ታስተምራት ዘንድ ለመነቻት። ቅድስት ዮናም ደስ በመሰኘት የቀናውን የሃይማኖት መንገድ ታሳያትና ትገልጥላት ገባች። የእግዚአብሔር ልጅ ሰው የሆነበትን ምክንያት ከቀዳሜ ፍጥረት ቅዱስ አዳም ድቀት ጀምራ ስለሰብዓ ትካት ጥፋትና በንፍር ውኃ መጥፋት፣ ከዚያም የጥፋት ውሃ ስምንት ነፍሳት ስለመትረፋቸው፣ ከጥፋት በኋላ ስለሕዝብ መብዛትና ስለተምልኮ ጣዖት መስፋፋት፣ አበ ብዙኃን ቅዱስ አብርሃም ስለመጠራቱ . . እያለች ስለትንቢተ ነቢያት እና ስለቸሩ ጌታችን መገለጥ ስለመከራ መስቀሉ፣ በመጨረሻም ስለስሙ ሲሉ መከራ የሚቀበሉት እንደምን ያለ ድንቅ ክብር እንደሚያገኙ ነገረቻት። በዚህም ቅድስት አጥራስስ በጌታችን ስም አመነች።
+ ይህ ኹሉ ሲደረግ ግን አባቷ አያውቅም ነበር። በኋላ አባቷ ሊድራት ስለወደደ ልጄ ከመሞሸርሽ በፊት ለአምላካችን ለአጵሎን ዕጣን አሣርጊ አላት። እርሷ ግን መልሳ አባቴ የነፍስህና የሥጋህም ጌታ እያለ ስለምን በእሊህ ጠፊ ከንቱ ጣዖታት ነፍስህን ትጎዳለህ አለችው። አባቷም እንዲህ ያለውን ነገር ከርሷ በመስማቱ ተደንቆ ማን ልቡናዋን እንደለወጠ ሲያጣራ የፍላጽፍሮን ልጅ ድንግሊቱ ዮና መኾኗን ሰማ። እርሱም ተቆጥቶ ጉድጓድ አስቆፈረና እሳት እጅግ አድርጎ አስነደደ። ኩለቱም የንገሥታት ልጆች ነበሩና ከልብሳቸው አላራቆቷቸውም፣ ነገር ግብ ስለነርሱ መሞት ያዘኑ ኹሉ እንዲህ ካለው ምክራቸው ለጥቂት እንዲተዉ እሊህን ቅዱሳን ለመኗቸው። እንርሱ ግን ስለስሙ መከራን ለመቀበል በጥብዓት ቆርጠዋልና ወደኋላ ከቶ አላሉ። እሳቱም ከጉድጓዱ ወጥቶ ሲንቀለቀል፣ እሊህ ኹለት ደናግልን እጅ ለእጅ እንደተያያዙ ጨመሯቸው። ወደ ምሥራቅም ዞረው ረጅም ጸሎትን ከጸለዩ በኋላ ነፍሳቸውን በእግዚአብሔር እጅ ሰጡ። የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበሉ።
+ እሳቱም ስንኳን ሰውነታቸውን ልብሳቸውን አለመንካቱን የተመለከቱ ኹሉ እጅግ አደነቁ። ምእመናንም ቅዱስ ሥጋቸውን ወስደው የመከራው ዘመን እስኪያልፍ በክብር አኖሯቸው። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በእሊህ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን፣ በረከታቸውም እጽፍ ድርብ ኹኖ ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።
ሰላም ለዮና መጽሐፈ ክርስቶስ መጽሐፋ
ወለአጥራስስ ሱታፋ
በእንተ ሃይማኖት ርትዕት ወበእንተ ጽኑሕ ተስፋ
ሶበ ተወርዋ አሐቲ እደ ካልዕታ ሐቂፋ
ማዕከለ እሳት ኅቡረ አዕረፋ።
✍️፪-ዳግመኛም በዚህች ዕለት ከንዑዳን ክቡራን አንቅዕት ንጹሐን ከኾኑ ከዐሥራ ኹለቱ ሐዋርያት አንዱ #ቅዱስ_ሐዋርያ_ፊልጶስ በሰማዕትነት የሞተበት መታሰቢያው ነው።
+ ይህ ቅዱስ የሚያስተምርበት ዕጣው ወደ አፍራቅያ እና ወደ አውራጃዋ ኹሉ በሆነ ጊዜ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በውስጧ ሰበከ። እነርሱንም ድንቆች ተአምራትንም ጭምር አድርጎ ወደ ቀማች ሃይማኖት ከመለሳቸው በኋላ ወደ ሌላ አገር ሔዲ የከበረ ወንጌልን ማስተማር ጀመረ። ከእነርሱም ብዙዎች ያመኑ ሲኖሩ ያላመኑት ግን በንጉሡ ለመወደድ ብለው ሊገድሉት ይወዱ ነበር። ይዘውትም ጽኑዕ ሥቃያትን አሠቃዩት፣ እርሱ ግን ይሣለቅባቸው ነበር፣ ስለምን የነፍሳችሁን ድኅነት አታስቡም? ይላቸው ነበር። እነርሱ ግን ብዙ ካሠቃዩት በኋላ ዘቅዝቀው ሰቀሉት፣ ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ። ሥጋውንም በእሳት ሊያቃጥሉ ቢሉ የእግዚአብሔር መልአክ ኹላቸውም እያዩት መጥቶ የቅዱስ ፊልጶስን ሥጋ ወሰደባቸውና ከኢየሩሳሌም አገር ውጪ አግብቶ ሠወረው። ኹሉም ይህን ተአምራት እንዳዩ ከቅዱስ ፊልጶስ አምላክ በቀር ሌላ አምላክ የለም ብለው አመኑ።
+ ሥጋውም ይገለጥላቸው ዘንድ ሦስት ቀንና ሌሊት ከጦሙ በኋላ በሦስተኛው ቀን ተሰጥቷቸዋል። እነርሱም በቸሩ እግዚአብሔር አመኑ፣ ከሥጋውም ብዙ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ፣ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በአባታችን በቅዱስ ሐዋርያ ፊልጶስ ጸሎት ይማረን፣ በረከቱም እጽፍ ኹና ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✍️፫-ዳግመኛም በዚህች ዕለት ከሮሜ አገር #ቅዱስ_ኤላውትሮስና #እናቱ_ቅድስት_እንትያ በሰማዕትነት አረፉ።
+ ይህም ቅዱስ እግዚአብሔርን የሚፈራ አንቂጦስ ከሚባል ኤጲስ ቆጶስ ዘንድ ዲቆና ተሾመ፣ ደግሞ በዐሥራ ስምንይ ዓመቱ ቅስና ተሾመ። ከዚህም በኋላ በሃያ ዓመቱ አላሪቆስ ለሚባል አገር ጵጵስና ተሾመ። በዚያም ወራት ንጉሥ እንድርያኖስ ወደ ሮሜ አገር መጣ፣ ስለኤላውትሮስም በሰማ ጊዜ ይዞ ያመጣው ዘንድ ፊልቅስ የተባለውን የጦር አለቃውን ላከው። እርሱም ሲኼድ ቅዱስ ኤላውትሮስን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል ሲያስተምር አየው፣ በትምህርቱም አመነና የክርስትናን ጥምቀት ተጠመቀ።
+ ኤላውትሮስም ከንጉሡ ፊት እንደቀረበ ንጉሡ "ስለምን ተሰቅሎ ለሞተ ሰው ባሪያ ትሆናለህ፣ ራስህን ነጻ ለምን አታደርግም" አለ እየዘበተ። ቅዱስ ኤላውትሮስም መልሶ ነጻነትስ ያለ በጌታዬ በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንጂ በሌላ በምንም አይደለም አለው። ንጉሡም ትቆጥቶ የእሳት ምድጃ ውስጥ ጨመረው። ነገር ግን የእሳቱ መንኰራኲር ራሱ ተቆራርጦ ወደቀ፣ እሳቱም ጠፋ። ይህም ንጉሥ በቅዱስ ኤላውትሮስ ላይ የሚያደርግበትን ነገር ቢያጣ ምን እንደሚያደርግ እስኪያስብ ወደ ወህኒ ቤት ጣለው። በወህኒም ሳለ የገነት ዖፍ መብልን አመጣችለትና በልቶ ጠገበ። ቆሊሪቆስ የተባለውም መኰንን ይህን በማየቱ አምኖ በሰማዕትነት ሞተ።
+ ከዚህም በኋላ ፈረሶችን አምጥተው በሠረገላ ላይ እንዲጠምዷቸው፣ ቅዱስ ኤላውትሮስንም ከሠረገላው በታች አሥረው ሕዋሳቱ እስኪሰነጣጠቅ ፈረሶችን እንዲያስሮጡአቸው አዘዘ። በዚህም ጊዜ መልአከ እግዚአብሔር ከተፍ አለና ያንን ማሠሪያ ፈትቶ ቅዱስ ኤላውትሮስን ከፍተኛ ተራራ፣ አራዊት የሚኖሩበት ቦታ አደረሰውና በዚያ ተወው። ቅዱስም እግዚአብሔርን እያመሰገነ በዚያ ሲኖር ንጉሡ እንድርያኖስ ለአደን ወታደሮቹን ቢልክ ወታደሮቹ ቅዱሱን አገኙትና ወደ ንጉሡ አቀረቡት። ንጉሡም ለአናብስት ሰጠው፣ አናብስቱ ግን መጥተው ላበቱን ላሱለትና ተደፍተው ሰገዱለት፣ ተመልሰው ግን ከአረማውያን ወገን የሆኑ ሰዎችን መቶ ሃምሳ የሚሆኑ ገደሉ። ንጉ
ሡም በዚህ እጅጉን ተቆጥቶ ኹለት ወታደሮችን አዘዘና ቅዱስ ኤላውትሮስን እና እናቱን ቅድስት እንትያን በጦር ወግተው እንዲገድሏቸው ኹለት ወታደሮ
ችን አዘዘ። እናቱም የልጇን አንገት እንዳቀፈች ወግተው ገደሏቸው። እነርሱም የድል የሰማዕትነትን አክሊል ተቀዳጁ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በእሊህ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን፣ በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ሰላም ለፊልጶስ ጽዑረ አባል በመቅሠፍት
ወለኤላውትሮስ ርጉዝ በብልሐ ኲናት
ምስለ እንትያ እባእ ኀበ ተርህወ ገነት
ያሩጸኒ መዓዛሆሙ ወጼናሆሙ ዕፍረት
ለዝ ሐዋርያ ወለዝ ሰማዕት።
✍️፬-ዳግመኛም በዚህች ዕለት #የየዋህ_አትናቴዎስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ለእግዚአብሔር ነአኲቶ በእንቲአከ መቅድመ
ወናተሉ ካዕበ ለኂሩትከ ሰላመ
አትናቴዎስ የዋህ እንተ ኢተአምር ቆመ
መፍትው እንበይነዝ ይስምዩከ ስመ
ስቴ ሠናየ ወእክለ ጦዑመ።
(ምንጭ፥ ስንክሣር ዘወርኃ ኅዳር)
----------------------------------------------------------------
ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው በእንተ ቅዱሳት አጥራስ ወዮና ደናግል ሰማዕታት ወቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ ወበእንተ ቅዱስ ኤላውትሮስ ወእንትያ እሙ ወበእንተ ቅዱስ አትናቴዎስ የዋህ ወበእንተ ኲሎሙ ቅዱሳን እለኮነ ተዝካረ በዓሎሙ በይእቲ እለት መሐረነ ለነ ለአባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ አሜን።
እግዚኦ ተዘከር ኪዳን ዘወሀብኮሙ ለቅዱሳን አግብርቲከ ወአእማቲከ እለ አስመሩ ኪያከ፣ ወሶበ ተዘከርከ ዘንተ ተዘከር ከመ መሬት ንሕነ አባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ፣ ኢታርእየነ ሙስናሃ ለቅድስት ሀገሪትነ ኢትዮጵያ ወለቅድስት ቤተ ክርስቲያን። ኢታጥፍአነ ተዘኪረከ ዘትካት፣ ፍጡነ ይርከበነ ሳህልከ እግዚኦ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።
t.me @deaconmelakuyifru
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ