የኅዳር ፲፯ ዝክረ ቅዱሳን።
በዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
----------------------------------------------------------------
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
¶ አመ ፲፯ ለኅዳር በዛቲ ዕለት፥ ኮነ ፍልሰተ ሥጋሁ #ለቅዱስ_መምህረ_ኲሉ_ዓለም_ዮሐንስ_አፈወርቅ።
✍️፩-ኅዳር ፲፯ በዚህች ዕለት የዓለም ኹሉ መምህር የኾነው የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሥጋው ፍልሰት ተደረገ።
❤️+ ስለዚህ ታላቅና ግሩም ቅዱስ ምን መናገር ይቻላል በእውነት?! የኔታ እንዲህ አሉ፣ " ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን በትክክል ለመግለጥ ራሱን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን መኾን ያስፈልጋል!"። በአማን አፈወርቅ ዘአልቦቱ ምሳሌ፣ #ሙሐዘ_ትርጓሜያት #ወሊቀ_ሊቃውንት #አፈ_በረከት #አፈ_መዐር #አፈ_ዕንቊ #አፈ_ጳዝዮን #አፈ_ርኄ . . #መምህረ_ኲሉ_ዓለም ነው።
❤️ + እንግዲህ የዚህ ታላቅ ቅዱስ ዜና እንደኔ ባለው ጎስቋላ ስለተነገረ እንዳያዝንብኝ ይቅርታውን እና የርሱንም እርዳታ እየጠየቅሁ ለበዓሉ ማዘከሪያ እጅግ ጥቂት ብቻ እላለሁ። አፈ ወርቅ የተባለውን የቊስጥንጥንያውን ኮከብ ብሩህ ቅዱስ ዮሐንስን በምን ቃል እንገልጠው ይሆን?!
❤️+ ይህ ቅዱስ አባቱ አስፋኒዶስ (ሴኮንዶስ) ሲባል እናቱ ደግሞ አንቱዛ (አትናስያ) ትባላለች። ደገ'ኛ ክርስቲያኖች ናቸው። የተወለደው በ፫፻፵፱ዓ.ም ሲኾን አባቱም ገና በልጅነቱ በማረፉ እርሱን የማሳደጉ ድካም በእናቱ ላይ ኾነ። ቅዱስ ዮሐንስ ከዓለሙ የፍልስፍና ጥበብም ኾነ ሕግ ያልተማረው ምንም ምን አልነበረም። እንዲያውም መምህሩ ክርስቲያኖች ነጥቀው ባይወስዱብን ኖሮ እኔን የሚተካው እርሱ ነው ብሎ እስኪተማመንበት ድረስ ድንቅ ዕውቀት ከማስተዋል ነበረው።
❤️+ ከዚህም ኹሉ ዓመታት በኋላ ቅዱሳት መጻሕፍትን ተማረ። ቅዱስ አባታችን ማር አፈወርቅ ዮሐንስ ለቅዱሳት መጻሕፍት እና ለማንበብ የነበረው ፍቅር እጅግ ልዩ ነው። እጅግ ይወደውም የነበረ አንድ ደግ ባልንጀራው የኾነለት ባስልዮስ የሚባል ደግ ባልንጀራ ነበረው። እርሱ እና የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እናት በሊቁ ሕይወት ትልቅ ቦታ አላቸው። ቅዱስ ዮሐንስ ለመመንኰስ በወደደ ጊዜ እናቱ ከእርሷ ጋራ እንዲኖር ስለወደደች እርሷ እስክታርፍ ድረስ ራሱን የትሕርምትን መንገድ እያለማመደ አብሮአት ቆየ። እርሷም ስታርፍ የነበረውን ሀብት ንብረት ኹሉ ለድኆች መጽውቶ እጅግ ጥብቅ የኾነውን የትሕርምት ሕይወቱን የሚያደርግበትን ቦታ ለይቶ ወደ በረሓ ወጣ። በዚያም ከባልንጀራው ከቅዱስ ባስልዮስ (ይህኛው ባስልዮስ፣ ባስልዮስ ዘቂሣርያ አይደለም ሌላ ነው) ጽኑዕ ገድልን ሲጋደል ከመኖሩ የተነሳ ከጨጓራ ሕመም ጀምሮ በብዙ ይሠቃይ ነበር።
❤️ + ቅዱሱ አባታችን ሊቀ ሊቃውንት መምህረ ኲሉ ዓለም አፈወርቅ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሲተረጉም ዲያቆን እያለ ብሉያትን ቅስና ከተቀበለ በኋላ ደግሞ ሐዲሳትን ተርጉሞአል። ከዚያም በኋላ ያስተማራቸውን ትምህርቶች ዘርዝሮ ማን ይጨርሳቸዋል? እርሱ ከድውያን ጋር እንደሐኪም ኹኖ፣ ከሙሽሮች ጋር ልክ ሙሽራ እንደሚኾነው ኹኖ ከመነኩሳትና ከባሕታውያን እንደባለ ጽኑዕ ገድል ተሐራሚ መነኰስ ባሕታዊ ኾኖ፣ ከወጣቶች ጋር እንደወጣት ከአዕሩግ ጋር እንደአዕሩግ፣ ከፈላስፎች ጋር እንደታላቅ ሊቅ ፈላስፋ ብቻ ከኹሉም ጋር እንደሚመቸው ኹኖ ሲያስተምር ያየው ሰው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ታላቁ አባታችን አንድ ሰው ነው ብሎ መጥራት ይቸግረዋል። እርሱ ለኹሉም እንደሚስማማው አድርጎ ማስተማር ያውቅበታል። (ይህን ድንቅ ሊቅ መምህር የሰጠን አባታችን እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን!!)
❤️+ ቅዱስ ዮሐንስ ከትምህርቱ ጣዕም የተነሳ በኹሉ እጅግ ይወደድ ነበርና ዘወትር ትምህርቱን ለመስማት ኹላቸውም አይጠግቡትም። እርሱም ድርሳናትን የመድረስና የመተርጎም የቅዱሳት መጻሕፍት ኹሉ ጸጋ ያደረበት ገና በዲቁና ሳለ ነበር። ከጊዜም በኋላ የቊስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳሳት ሲያርፍ ንጉሡ አርቃዴዎስ ቅዱስ ዮሐንስን እጅግ ይወደው ነበርና ለምን እንደሚወሰድ እንኳ ሳያውቅ ወደ ቊስጥንጥንያ አስመጥቶት በ፫፻፺፯ዓ.ም ሊቀ ጵጵስና ተሾመ።
❤️ + ሊቀ ጳጳሳት ከኾነም በኋላ በሚያስተምራቸው ትምህርቶቹና ተግሣጻቱ እጅጉን የሚወደድ ነበርና ከትምህርቱ ጣዕም የተነሳ "አፈወርቅ" ተብሎ ተጠራ። ዳግመኛም ንጉሡ የ"ኢያዕመራ እስለ አመ ወለደት ወልደ ዘበኲራ"ን ትርጓሜ እንዲያስረዳው ቅዱስ ዮሐንስን ቢጠይቀው እርሱ በመለሰለት ድንቅ መልስ ምክኗት የእመቤታችን ሥዕለ አድኅኖ እየዞረችው "ሠናየ ተናገርከ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ሠናየ ተናገርከ ዮሐንስ ልሣነ ወርቅ" ብላዋለችና ይህን ሰምተው ዮሐንስ "አፈወርቅ" አሉት። ቅዱስ ዮሐንስ አባታችን ድርሳናቱን ልብ ብሎ ላስተዋለው ሰው ተዋሕዶን በሚገባ የሚሰብክ ቅዱስ ነው። ይኸውም ሊታወቅ ድርሳናቱ ኹሉ በጎ የኾኑ የምስጢራት መፍሰሻ ሲኾኑ ከዚሁ አሠናስሎ ደህሞ ወደ ሕይወት የሚተረጎሙ የምግባራትን ነገር ይጽፋል። ስለዚህም የቅዱስ ዮሐንስ ድርሳናትን ልዩ ከሚያደርጋቸው ነገሮች አንዱ ድርሳናቱ ኹለት ክፍል አላቸው። አንደኛው የትርጓሜ ወይም ሀተታ ክፍል ሲኾን ሌላኛው ደግሞ የምግባር ክፍል ነው።
❤️+ እርሱ እውነተኛ መምህር ነው፣ መምህር ዘበአማን ወመገሥፅ ዘኢያደሉ ለገጽ- ፊት አይቶ የማያደላ እውነተኛ መገሥጽ፣ ነገሥታትን የማይፈራ በድኃው የማይመካበት እውነተኛ ቅዱስ ነው። በዚህም የተነሳ ነው ዕረፍቱ የኾነው። ይህም እንዲህ ነው፣ ቅዱስ ዮሐንስ አንድ ቀን ንግሥቲቱ አውዶክስያ የአንዲትን ድኃ ሴት ቦታ በመውሰዷ ልትመልስላት እንደሚገባ አጥብቆ ነገራት ገሠጻትም። አልሰማም ባለችውም ጊዜ አወገዛት፣ ከቅዱስ ቊርባንም ለያት። ይህም ስላስቆጣት እርሱ በምግባር ጉድለትና በምንፍቅና ካወገዛቸው ኤጲስ ቆጶሳት ጋር ኾና ወደ ደሴተ አጥራክያ አጋዘቸው። ከስደትም ከተመለሰ በኋላ ዳግመኛ አጋዘቸውና በስደት ሳለ "ስለኹሉም ነገር ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን" ብሎ ግንቦት ፲፪ ዕለት በክብር አረፈ። ንግሥቲቱ አውዶክስያም ይህን ታላቅ ቅዱስ በማሳደዷ አልተጠቀመችበትም፣ በጭንቅ ደዌ ተቀስፋ አርፋለች።
❤️ + ቅዱስ ዮሐንስ ካረፈ ከሠላሳ አምስት ዓመታት በኋላ በታናሹ ቴዎዶስዮስ ዘመነ መንግስት የሥጋው ፍልሰት ኾኗል። ይህም የሆነው ፓትርያርኩ ቅዱስ ጵሮክለስ ስለቅዱስ ዮሐንስ ሲያስተምራቸው በሕይወቱ እጅግ ከመደነቃቸው የተነሳ ሳያስጨርሱት እባክህን አሁኑኑ ቅዱስ ዮሐንስን አምጣልን ብለውታል። በዚህም የሥጋው ፍልሰት ኾኗል።
❤️ + ቅዱስ ዮሐንስ ሕይወቱ ትምህርቱ፣ ትምህርቱ ሕይወቱ የኾነ ድንቅ ምድራዊ መልአክ ሰማያዊ ሰው፣ ሊቅ መምህር ወመገሥጽ ዘኢያደሉ ለገጽ፣ ኃያል ተሐራሚ መነኰስ፣ ድንቅ መንፈሳዊ መተርጉም ነው። ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን አፈወርቅ ወዕደ ወርቅ ቅዱስ ዮሐንስን ስትጠራው፥
√አፈ ዕንቊ
√አፈ መዐር
√አፈ ርኄ
√አፈ ሶከር
√አፈ አፈው
√ልሣነ ወርቅ
√አፈ በረከት፣ ርዕሰ ሊቃውንት
√ሐዲስ ዳንኤል
√መምህረ ኲሉ ዓለም
√መምህር ወመገሥጽ ዘኢያደሉ ለገጽ እያለች ነው።
❤️+ይህም ሊቅ ለቅዱስ ጳውሎስ የነበረው ፍቅር ልዩ ነው። ስለርሱ ስንቱን እንዘረዝር ይሆን? ለዕረፍቱ ጊዜ ይቆየን ሌላው። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በማር ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ጸሎት ይማረ። በረከቱም እጽፍ ድርብ ኹላ በዝታ ትደርብን ለዘላለሙ አሜን።
ስላም ለፍልሰተ ሥጋከ ዮሐንስ አፈወርቅ
ሀገረ ሢመትከ ቊስጥንጥንያ እምገዳመ ስደት ርሑቅ
መንፈስየ ሐድስ እግዚኦ ውስተ ከርሥየ ዕሩቅ
በዘይትዓቀብ ውስቴቱ ትምህርተ ዚአከ ጽድቅ
ከመ ውድየተ ወይን ሐዲስ በሐዲስ ዝቅ።
(❤❤
+ኦ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስተብቊዕ ለነ ለውሉድከ ደቂቀ አዳም
+ሰሚዓነ ተግሣፀከ ከመ ንድኃን እምእሳቱ ዘኢይጠፍዕ ወዕጼሁ ዘኢይነውም
❤❤
❤❤አፈ ወርቅ አፈ መዐር ቅዱስ አባታችን ዮሐንስ ልሣነ ወርቅ ሆይ ድኩማን ልጆችህን በምልጃህ አስበን፣ ከማይጠፋው እሳትም ታሻግረን ዘንድ በጽኑዕ ቃልኪዳንህ ተማጽነንብሃል።❤❤)
✍️፪-ዳግመኛም በዚህች ዕለት #የቡሩክ_አብርሃም እና #የሚስቱ_ሐሪክ መታሰቢያቸው ነው። ዳግመኛም #የወጺፍ_ጻድቃን መታሰቢያቸው ነው። በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ሰላም ለከ አብርሃም ቡሩክ
ወለብእሲትከ ሐሪክ
ዘፈረይክሙ ሕፃነ ቅዱስ አምላክ
ጺሑ ሊተ ፍኖተ ለበዊእ ኀበ ቦእክሙ ምስማክ
እስመ ፍኖትየ ተሐጽረ በሦክ።
ሰላም እብል ጻድቃነ አምዓተ
ገዳመ ወጺፍ ይዒሉ እለ መነኑ አብያተ
እስከ ረከብህ በኀሢሥ ዘአምላከ ያዕቆብ ቤተ
ኢወሀቡ ለመልታሕቶሙ እሙኀዘ አንብዕ ዕረፍተ
ወለዐይኖሙ ካዕበ ምንተኒ ኅድመተ።
✍️፫-ዳግመኛም በዚህች ዕለት ለማስተማር የተጠራ #የአበ_ምኔቱ_የአባ_ሲኖዳ መታሰቢያው ነው። በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ሰላም ለሲኖዳ እንተ አትሐተ ግብሮ
እንዘ አበ ምኔት ውእቱ ዘተጸውዐ ለምህሮ
አልባበ ድኩማን ያዕርፍ እምርሕቀተ ማይ እምተጽዕሮ
ቀዲሖ ሌሊተ ወፀዊሮ እንበለ መኑ ያእምሮ
ለለበዓቶሙ ይሜጡ አንቢሮ።
(ምንጭ፥ ስንክሣር ዘወርኃ ኅዳር፣ ድርሳነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)
----------------------------------------------------------------
ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው በእንተ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አፈ በረከት መምህረ ኲሉ ዓለም ወቅዱስ ሲኖዳ አበ ምኔት ወበእንተ ቡሩክ አብርሃም ወብእሲቱ ሐሪክ ወቅዱሳን ጻድቃን እለወጺፍ ወበእንተ ኲሎሙ ቅዱሳን እለኮነ ተዝካረ በዓሎሙ በይእቲ እለት መሐረነ ለነ ለአባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ አሜን።
እግዚኦ ተዘከር ኪዳን ዘወሀብኮሙ ለቅዱሳን አግብርቲከ ወአእማቲከ እለ አስመሩ ኪያከ፣ ወሶበ ተዘከርከ ዘንተ ተዘከር ከመ መሬት ንሕነ አባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ፣ ኢታርእየነ ሙስናሃ ለቅድስት ሀገሪትነ ኢትዮጵያ ወለቅድስት ቤተ ክርስቲያን። ኢታጥፍአነ ተዘኪረከ ዘትካት፣ ፍጡነ ይርከበነ ሳህልከ እግዚኦ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።
t.me @deaconmelakuyifru
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ