በስመ አብ ወወልድ ወአንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
✍ይህ ነገር በተለይም ከኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ያሉ ወንድሞች የሚያነሱት አንዱ ጥያቄ ነው። ነገረ ድኅነትን፣ ምሥጢረ ሥጋዌን በተረዳ መንገድ ላገናዘበ ክርስቲያን ግን የሚከብድ ጥያቄም አይደለም።
ከቃሉ መሠረታዊ ትርጉም እንነሳና ወደታች በከፊል ጉዳዩን እንመልከተው።
ቤዛ ፥ በቁሙ ዋጋ፣ ካሣ፣ ልውጥ ምትክ፣ ዐላፊ ዋቢ፣ ዋስ መድን፣ ተያዥ ጫማ ጥላ ጋሻ የመሰለው ኹሉ። "ቤዛ ነፍሱ ለብእሲ ጥሪተ ብዕሉ።" "አኮ በቤዛ።" "ቤዛ ኲሉ ኃጢአትከ።" "ማእስ ቤዛ ማእስ።"(ምሳ ፲፫፥፰፤ ኢሳ ፵፭፥፲፫፤ ኤር ፲፭፥፲፫፤ ኢዮ ፫፥፬)
ቤዛ በሌላም ወገን በደቂቅ አገባብ ሲገባ ልዩ ትርጉም አለው። ይኸውም ከዚህ ብዙ የሚርቅ አይደለም። እሱም ስለ ፈንታ፣ ምክንያት ማለት ይሆናል። ይህም ማለት በምሳሌ ብናየው ጌታችን "እሜጡ ነፍስየ ቤዛ አባግዕየ" ሲል ይገኛል። ትርጉሙም "ነፍሴን ስለበጎቼ አሳልፌ እሰጣታለሁ" ማለት ነው።
የቤዛን ትርጉም ለመግቢያ በጥቂቱ ካልን፣ ይህን ያነሳነው በሰፊው ለመነጋገር አይደለምና ለሌላ ጊዜ እናቆየው። ወደ ተነሳንበት ነገራችን እንመለስና ትርጉሙን እናመሳክረው።
እመቤታችን ርኅርኅተ ኅሊናን ቤዛዊተ ዓለም ብለን እንጠራታለን።
👉ቤዛ ከላይ በመግቢያው እንዳየነው አንዱ ትርጉሙ ልውጥ ምትክ ማለት ነው። ይኸውም በአንዱ ፈንታ ሌላው ተገብቶ የዚያኛውን ዋጋ ሲከፍል፣ ዕዳውን ሲቀበል፣ በአጠቃላይ ልክ እንደዚያኛው ሰው ሁኖ የርሱ የሆነውን ነገር ሁሉ ሲተካ ቤዛ ተብሎ ይነገራል። "ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ" የተባለላት ብጽእት እመቤት ወላዲተ አምላክም ቤዛ ናት።
+ ቀዳሚት ሔዋን ድንግልና ሕሊናዋን ገሣ' ኃጢአትን ጸንሳ ሞትን ስትወልድ ዳግሚት ሔዋን የዋሂት ርግብ እመብርሃን ድንግል በክልኤ ሁና ጸንታ በመገኘት ሔዋን ያጣቸውን ድንግልና በርሷ ፈንታ ምትክ አድርጋ አቅርባለችና። የሔዋንን የድንግልና ካሣ በሔዋን ተገብታ መልሳለች። ሕዝ ፵፬፣ ኆኅት ኅትምት መባሏም አንዱ ለዚህ ነውና።
+ ሔዋን ድንግልናዋን አጥታ የወለደቸው ልጅ ወንድሙን የገደለ ነፍሰ ገዳይ ሆነ። እመብርሃን ግን በሔዋን ምትክ ሁና የወለደችው ልጅ ስለሁሉ ነፍሱን አሳልፎ የሚሰጥ፣ ንጉሥ ሁንክ ሳለ በአገልጋዮቹ የሚሰቃይ፣ ባዕለ ጠጋ ሁኖ ሳለ እንደምስኪን ድሃ የተቆጠረ ነውና። ይኸውም ስለ ድኅነተ ዓለም ነው።
ቤዛዊተ ዓለምና ስደቷ
+ ቀዳሚት ሔዋን በበደለችው እና ባስበደለችው በደል በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ከመካነ ፍስሐ ገነት ስደት መጦብን ነበር። በዚህም ምክንያት በስደት ዓለም ስንቅበዘበዝ ዐይታ አንጀቷ የማይችል የዋሂት ርግበ ኤፍራታ ባለ ድንቅ መዐዛዋ የእሴይ አበባ ድንግል ልጇን ይዛ የሰው ልጆችን ስደት በሰው ልጆች ተገብ'ታ ተሰደደች። የሔዋንን ቁስል ቆሰለች፤ የሔዋንን ጥማት ከልጇ ከወዳጇ ጋር ተጠማች። በእውነት ያለሐሰት ይህን'ስ ላሰበው ሰው ሕሊናን የሚያናውጽ ምንኛ ከባድ ነው። ምስኪኗ የዋህ የሆነችው የ፲፭ ዓመቷ ሕጻን ድንግል ዳግሚት ሔዋን ሁና የሔዋንን ስደት ተሰደደች። በእውነት ይህን ርኅራኄዋን የቀመሰ እርሷን ሳያመሰግን መቦዘን የሚቻለው አንጀቱስ የሚችልለት ማን አለ?!
+ በስደቷ ጊዜም ሔዋን በሠራችው ሥራ መሰደብ የሚገባትን ስድብ ተሰድባለች፤ ሔዋን መጠማት የሚገባትን ጥማት፣ መራብ የሚገባትን ረሐብ፣ መጨነቅ የሚገባትን ጭንቀት፣ ማልቀስ የሚገባትን ልቅሶም ሁሉ በርሷ ተገብ'ታ ፈጽማለች።
ቤዛዊተ ዓለምና ሕማመ መስቀሉ
+ መስቀሉንም ስናስብ ወላዲተ አምላክን ነጥለን ማሰብ ከቶ እንዴት ይቻለናል? ከእግረ መስቀሉ እስኪደርሱ ድረስ ልጇ ከተያዘበት እለት አንስቶ የተጨነቀችውን ጭንቀት፣ ያዘነችውን ሐዘን፣ ያለቀሰችውን ልቅሶ ጥቂት ጊዜ ሰጥተን ብናስበው ያስጨንቃል። ርኅርኅተ ሕሊና እመብርሃን ልጇ ፍጹም ካሣን ሊክስ ወደ እዚህ ዓለም መጥቶ መከራን ሲቀበል በነገረ ድኅነት ውስጥ እንዴት ፍጹም ካሣን እንደካሰ ልብ በሉ።
+ ሔዋን ያጣችውን ድንግልና በድንግል እመቤታችን መለሰላት። ዳግሚት ሔዋን እመብርሃንን የድኅነተ ዓለም ሥራው ላይ እንዴት እንዳሳተፋት ልብ አድርጉ። ዓለሙ ሁሉ እርሱን ፈጣሬ ዓለማትን ለማስተናገድ እምቢኝ ባለበት ጊዜ፣ ዓለሙ እሺ በጄ ብሎ ቢፈቅድም እንኳ የነበረበት ዕዳ በደል እግዚአብሔርን ለመቀበል ያልበቃ በሆነበት ጊዜ በዓለሙ ሁሉ ፈንታ ራሷን ለልዑል ማደሪያነት የሰጠች፣ ንጽሕናዋም እግዚአብሔርን ማርኮ ከሰማይ ወደ ምድር እስኪያመጣው ድረስ ምዕዝት ሁና የተገኘች ከሷ በቀር ማን፡ነበር?!
+ ለይኩን ብርሃን ብሎ ዓለማትን በብርሃን ጎርፍ ብሩህ ያደረገው፡ፀሐየ ጽድቅን ይኩነኒ ብላ የፀነሰች ከርሷ በቀርስ፡ማን ነው?! ሉቃ፩
👉ሌላኛው ቤዛ ማለት ዋስ ጠበቃ ማለት እንደሆነ ተመልክተናል። "ወትቀውም ንግሥት በየማንከ" ያለው ልበ አምላክ ለምን ይሆን? ንግሥቲቱ በቀኙ የወርቅ መጎናጸፊያ ተጎናጽፋ የቆመች ምን ብላ ይሆን?
+ መቆም በቤተብክርስቲያናችን በብዙ መንገድ ይፈታል። ቆመ፡ብሎ ፈረደ፣ ቆመ ብሎ አማለደ ይላል። በዚህ ዐውድ ትቆማለች የተባለላት እመብርሃን ለምልጃ መሆኑን ልብ ይሏል። የዶኪማስን ቤት ስናስብ፣ በሠርጉ ላይ የወይን ጠጁ ባለቀ ጊዜ ርኅርኅተ ሕሊና ልጇን ወዳጇን የወይን ጠጅ 'ኮ የላቸውም ብላ ስትለምነው ልጇም "አንቺ ሴት ካንቺ ምናለ፥ ጊዜዬ ገና አልደረሰም" በማለት ሲመልስላት ሄዳ አስተናጋጆቹን "የሚላችሁን አድርጉ" አለቻቸው። ለምን ይሆን እንዲህ ያለቻቸው? ከልጇ ጋር ባይግባቡ ኑሮ እርሱም ባይቀበላት የሚላችሁን አድርጉ ልትል እንዴት ቻለች?! ዮሐ፪
+ የእናት ልመና ፊት አያስመልስ አንገት አያስቀልስ ይላሉ አበው። ምልጃዋን ልጇ ወዶ ፈቅዶ የሚቀበልላት የአምላክ እናት ወላዲተ አምላክ ቤዛዊተ ዓለም ናት። ለዚህም፡ነው እንዲያውም ማር ቅዱስ ያሬድ ሊቅ በሚያስደንቅ ቃል "ለኪ ይደሉ ከመ ትኩኒ መድኃኒቶሙ ለመሃይምናም ሕዝብኪ፥ ለምእመናን ወገኖችሽ መድኃኒታቸው ልትባይ ይገባሻል" አለ። ምክንያቱንም ሲነግረን "ወታስተሥርዪ ኃጢአተ ሕዝብኪ ተበውሃ ለኪ እም አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ - የሰው ልጆችን ኃጢአት ታስተሠርዪ ዘንድ ከአብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን ተሰጦሻልና" በማለት ያስረዳናል። ስለዚህም ዘወትር ስንጸልይ "ሰአሊ ለነ ቅድስት፥ ወልድኪ ሣህሎ ይክፍለነ ሰአሊ ለነ ቅድስት" እያልን እንማጸናታለን።
እንግዲህ ልብ አድርጉ በመጽሐፍ ስንኳን ወላዲተ አምላክ ይቅርና ሀብት ንብረት ቤዛ ተብሎ የለ? ይህን ሁሉ የሆነችልን እመቤት፣ የሕይወትን ውሃ አፍልቃ ከጥም ያረካችን ምንጭን ቤዛዊተ ዓለም ማለት ታዲያ ምኑ ላይ ነው ጥፋቱ?!ወላዲተ አምላክን ቤዛዊተ ዓለም ስንል ያለምንም መሳቀቅና በድፍረት እጅግ ደስ እያለን የምንለው ለዚህ ብቻም አይደለም። ለበዓሉ ማዘከሪያ እንዲሆን ጥቂት ተናገርን እንጂ።
ቤዛዊተ ዓለም የተባልሽ እመብርሃን ከልጅሽ ከወዳጅሽ ይቅርታን ለምኝልን። አሜን።
ይቆየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር።
©ዘዲያቆን መልአኩ ይፍሩ ዘውሉደ ብርሃን
ኅዳር ፮፥ ፳፻ወ፲፩ ዓ.ም
ሲቹዋን ቸንዱ፣ ቻይና
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ