እሑድ 11 ኖቬምበር 2018

🙏የጽድቅ ሥራ ከባድ ነውን?🙏

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

         (መልስ ከመጽሐፈ ገነተ አበው ቅዱሳን
          Paradise of the holy fathers )
/ትርጉም፥ ዲያቆን መልአኩ ይፍሩ/
+ + +                + + + +              + + +

    👉ተወዳጆቼ፣ ራሳችንን አንድ ጊዜ ላስገዛንለት ምግባር ቀናኢያን(zealous) እንሁንና ለመጓዝ በጀመርነው መንገድም ወደ ፍጻሜው (ለመድረስ) እንሂድ፤ እናም የሎጥን ሚስት ልንመስላት አይገባምና ከእኛ መኻከል ማንም ሰው በኋላው ያለውን (ወደ ኋላው) አይመልከት። /ዘፍ ፲፱፥፳፮/ የጽድቅን መንገድ ትምህርት ከተቀበለ በኋላ ወደ ኋላው ለሚመለስ ሰው፣ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ቀላል አይሆንለትም፤ ወደ ኋላው የሚመለሰው ያ ሰው የተመለሰው በምንም ዓይነት መንገድ ቢሆን፣ ባደረገው ነገር ይጸጸታል እናም ልክ ውሻ ወደ ትፋቱ እንዲመለስ ሁሉ እሱም ወደዚህ ዓለም ንብረቶች ይመለሳል።/ምሳ፳፮፥፪፤ ፪ጴጥ፪፥፳፪/ ደግሞም ሰማያዊ ሸክም ከባድ እንደሆነ (እያሰባችሁ) አትፍሩ፤ ለሚፈልጉት የጌታችን ሸክም ልዝብ እና ቀሊል ነውና።/ማቴ፲፩፥፴/ ስለዚህ መሻቱ ካለን ሁሉም ነገር ቀላል ነው።
     👉የዚህ ዓለም ልጆች፣ በትምህርቱ ምንም ዓይነት የቅድስና መንገድ የማይገኝበትን (የሌለበትን) እና በምስጋናውም ምንም ዓይነት የሕይወት ረብ ጥቅም የሌለበትን ርካሽ ጥበብ ይማሩ ዘንድ በባሕሩ ላይ ይጓዛሉ፤ ከባድ ወደ ሆኑ ሀገራትም ስንኳ ጉዞ ያደርጋሉ። ነገር ግን እኛ (እንደነርሱ) ስለመንግሥተ ሰማያት ብለን ጉዞ እንድናዘጋጅና በባሕር ላይም እንድንሄድ አልተፈለገብንም፤ ጌታችን አስቀድሞ እንዲህ ብሎ በመናገር አውጆልናልና። "መንገሥተ ሰማያት በመኻከላችሁ ናት" /ሉቃ ፲፯፥፳፩/ ስለዚህ ወዳጆቼ፣ ሕይወት በእኛ ውስጥ ነውና ያለችው ሕይወታችንን ማግኘትም በእጃችን ነው፤ የሚገለገለውም በራሳችን ነው። ነፍስ በባህርይዋ የለባዊነት ባለቤት ናትና ሕይወታችን ምን እንደሆነ ዕውቀቱ አላት፤ ይህም በአፈጣጠሩ ጠባይ ምክንያት ለወደደው (ለፈቀደው) ነገር ሁሉ (ዝንባሌ ያለው) ፍጹም የተዘጋጀ ነው። ስለዚህ የነዌ ልጅ ኢያሱ፣ ሕዝቡን እንዲህ በማለት አዘዘ"በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ፊት ልባችሁን አዘጋጁ" /ኢያ ፳፭፥፳፫/ እንዲሁም ዮሐንስ "መንገዱን አስተካክሉ" /ሉቃ፫፥፬/። አሁን መጽሐፉ ነፍስን ስለማዘጋጀት ሲደነግግም የመጀመሪያው ተፈጥሮአዊ ጠባይዋን በርሷ ውስጥ ጸንቶ እንዲቆይ ከመሻት ነው፤ ነገር ግን ከዚህ ወጥታ ልኳን አልፋ ብትሄድ ልክ እንደክፉው (እንደሰይጣን) የተለየች ውግዝት (የታመመች ድውይት የተፈረደባት ጊግይት) ትሆናለች። ስለዚህም ጉዳዩ ለእኛ ከባድ አይደለም።
ይቆየን።
+ + +               + + + +               + + +
የቅዱሳን አበው በረከት ይደርብን።

©ዘዲያቆን መልአኩ ዘውሉደ ብርሃን
ኅዳር፪/፳፻ወ፲፩ዓ.ም
ሲችዋን ቸንዱ/ ቻይና

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ