እሑድ 15 ኖቬምበር 2020

የኅዳር ፯ ዝክረ ቅዱሳ

እንኳን #ለማር_ቅዱስ_ጊዮርጊስ_ዘልዳ እና #ለቅዱስ_አባ_ናህርው፣ #ለቅዱስ_ሚናስ_ኤጲስ_ቆጶስ_ዘሀገረ_ተመይ ለሌሎቹም ንዑዳን ክቡራን ክብረ በዓላት በሰላም አደረሳችሁ።

የኅዳር ፯ ዝክረ ቅዱሳን። 

በዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
----------------------------------------------------------------

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

¶ አመ ፯ ለኅዳር በዛቲ ዕለት፥ ኮነ ሰማዕተ #ቅዱስ_ጊዮርጊስ_እስክንድርያዊ።

✍️፩-ኅዳር ፯ በዚህች ዕለት #የእስክንድርያው_ቅዱስ_ጊዮርጊስ በሰማዕትነት አረፈ።

  + ይህም ቅዱስ አባቱ በእስክንድርያ በንግድ የሚኖር ሲኾን ልጅ አልነበረው። በዚህችም እለት በኾነቸው በቅዱስ ጊዮርጊስ ልዳዊ ክብረ በዓል ልጅ እንዲሰጠው ከአምላኩ ያማልደው ዘንድ ማር ቅዱስ ጊዮርጊስ ልዳዊን ተማጸነው። ልመናውንም ሰምቶ ልጅ ሰጣቸውና ስሙን በዚህ ልዳዊ ሰማዕት ስም ጊዮርጊስ አሉት። የዚህም እናቱ ለእስክንድርያው አስተዳድስሪ ለአርማንዮስ እኅቱ ናት፣ በኋላም እናንትና አባቱ ሲያርፉ ከእናቱ ወንድም ጋራ ኖረ። ሃያ አምስት ዓመት ዕድሜ በኾነውም ጊዜ ለድኆች የሚራራ ምጽዋትን የሚያዘወትር ደግ ኾነ። ወደ ቤተ ክርስቲያንም ዘወትር ይገሠግስ ነበር። 

  + ለመኰንኑም አንዲት ሴት ልጅ ነበረቸው። እርሷም እየተዘዋወሩ መጎብኘትን ትወድ ነበርና አንድ እለት በደብረ ቊስቋም ስትዘዋወር በዚያ አካባቢ መነኰሳቱ ጣዕም ባለው ምስጋና ሲያመሰግኑ በዚያ ልቡናዋ ተመሰጠ። ኋላም ቅዱስ ጊዮርጊስን ስትጠይቀው እርሱ ተረጎመና አስተማራት። በልቡናዋም አመነች። ወደ አባትዋም ስትመለስ በክብር ባለቤት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አመነች። አባትዋም ሊያባብላት ብዙ ቢሞክር አልሳካለት አለ። በኋላም አሠቃይቶ በመጨረሻም ራሷን በሰይፍ አስቆረጣት።  ቆይቶም ሰዎች ይህን ያደረገውና የልጅቷን ልቡና የለወጠው ያስተማራት ቅዱስ ጊዮርጊስ መኾኑን ነገሩት። እርሱም አስቀርቦ አሠቃየው። ደግሞም ወደ እንጽና አገር ላከውና በዚያ አሠቃይተው ራሱን በሰይፍ ቆረጡት። በኋላም ሳሙኤል የሚባል ዲያቆን ቅድስት ሥጋውን ወደ መኑፍ አገር ወሰደው። የአርማንዮስም ሚስት ባወቀች ጊዜ አስመጣችውና ከልጅዋ ሥጋ ጋር በአንድነት በእስክንድርያ አገር አደረገችው። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በሰማዕቱ ጸሎት ይማረን፣ በረከቱም በዝታ ትደርብን ለዘላለሙ አሜን።

ሰላም ዕብል ሥቃየከ ዕጹበ
ጊዮርጊስ ዘኮንከ ስመ ሊቀ ሰማዕት ውሁበ
መኰንን አብድ ዘኢየአምር ጥበበ
በጊዜ ኮንከ ስምዐ ወለትምህርተ ክርስቶስ አበ
ርእሰ ወለቱ አምተረ ወርእሰከ ካዕበ።

✍️፪-ዳግመኛም በዚህች ዕለት ከግብጽ አገር ከፍዩም መንደር #ቅዱስ_አባ_ናህርው በሰማዕትነት አረፈ።

  + ይህ ቅዱስ እግዚአብሔርን እጅግ የሚፈራው ነው። በእስክንድርያም አገር የሚሠቃዩ የሰማዕታትን ዜና በሰማ ጊዜ ክብር ይግባውና ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለስሙ ሰማዕት ሊኾን ወደደ። እንዲሁ ደግሞ በራእይ ወደ አንጾኪያ ኺደህ ሰማዕት ትኾን ዘንድ አለህ አለው። ወደዚያ እንዴት መድረስ እችላለሁ ብሎ በሚያስብ ጊዜ ቸሩ አምላካችን ለስሙ ስግደት ይኹንና መልአኩን ቅዱስ ሚካኤልን ላከለትና እርሱ በክንፎቹ ተሸክሞ አንጾኪያ አደረሰው። በዲዮቅልጥያኖስም ፊት ቆሞ በእግዚአብሔር ስም ታመነ። ንጉሡም ስሙንና አገሩን ከጠተቀው በኋላ ለጣዖት እንዲሠዋ ሊያግባባው ቢሞክርም አልሞነለትም። የገባለትንም ቃል ኹሉ አቃለለበት። ኋላም ንጉሡ ጽኑዕ ሥቃይን እንዳላሠቃይህ የምልህን ድማ ቢለውም እርሱ ለሃይማኖቱ ጨክኗልና ክፉ ምክሩንም ኾነ ማስፈራራቱም አልሰማውም።

  + በኋላም ቅዱስ ናህርውን በብዙ ዓይነት ሥቃይ እንዲያሠቃዩት ንጉሡ አዘዘ። ለአንበሶች ጣሉት እነርሱ ግን ምንም አልነኩትም። ከእሳትም ጨመሩት እሳቱም ከቶ አልነካውም። ቀጥለውም በወጭት አድርገው ቀቀሉት፣ በደህና ወጣ። ንጉሡም ማሠቃየትን በሠለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡት አዘዘ። ይህም ቅዱስ አባት አባ ናህርው በአንጾኪያ ሰማዕት መኾኑም የአንጾኪያ ሰማዕታት ኹነው በእስክንድርያ ሰማዕት በመኾናቸው በነርሱ ፈንታ ነው። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ሰላም ሰላም ለብእሲ ፍንው
በክንፈ ሚካኤል ዐውደ ዲዮቅልጥናኖስ ዕልው
ለዝ ሰማዕት አባ ናህርው
ጤገን ሥእነ አውዕዮቶ ዘአፍልህዎ በሐው
ወኢነከይዎ አናብስት ዘበድው።

✍️፫-ዳግመኛም በዚህች ዕለት  ከገምኑዲ አውራጃ የሀገረ ተመይ ኤጲስ ቆጶስ #የአባ_ሚናስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ኾነ።

  + የዚህም ቅዱስ ወላጆች ደጎች እግዚአብሔርን የሚፈሩ ዜናቸውም በቅዱዳን አባቶች ዘንድ እስከተሰማ ድረስ በጾማቸው በጸሎታቸው በገድል በመጸመዳቸው ልክ እንደመነኰሳት #የመነኰሳትን_ሥራ_የሚሠሩ ናቸው። እነርሱም ይህን ልጃቸውን ካለፈቃዱ ሚስትን አጋቡት። ሙሽራይቱም ወፋለችበት ጫጉላ ገባና ከእርሷ ጋራ በንጽሕና በድንግልና ለመኖር ተድማሙ። ኹለቱም በጽንዕ ገድል ይጋደሉ ጀመር። ከዚህም በኋላ ቅዱስ ሚናስ የምንኲስናን ልብስ ሊለብስ ወዶ ሚስቱን በዚህ ዓለም እያለን የምንኲስናን ሥራ ልንሠራ እንደምን ይቻለናል አለ። ከዚያም ከልብሳቸው ውስጥ ማቅ በመልበስ በእግዚአብሔር መንፈስ የተደረሱ ቅዱሳት መጻሕፍትንም በማንበብና ለጸሎት በመትጋት ሌሊቱን ኹሉ ይቆሙ ነበርና ከዚህም በኋላ ሰላምታ ሰጥታ በል ደህና ኹን ብላ ወደ ገዳም እንዲኼድ ሸኘችው። እርሱም ወደ አባ እንጦንስ ገዳም ኼደና ከወላጆቹ ሊርቅ ወዶአልና እነርሱም ወደ ሚስቱ ሊመልሱት ብዙ ቢደክሙም ሊያገኙት አልቻሉም። እግዚአብሔርም እንዳያገኙት ሠውሮታልና። እርሱም በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳዳት የኾነው አባ ሚካኤል ከእርሱ ጋር በምንኲስና ነበር። ከዚህም በኋላ ኹለቱ ብሩሃን ከዋክብት #አባ_አብርሃምና #አባ_ገዓርጊ በነበሩበት ወራት ወጥቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ኼደ። ለእኒህም ቅዱሳን ልጅ ኾናቸውና በገድል ላይ ገድልን እየጨመረ በምንኲስናው ገድሉን ቀጠለ። ከነርሱም ትምህርታቸውንና የገድል ጎዳናቸውን በብዙ ይማራል፣ ከብዙዎች በተጋድሎውና ለእግዚአብሔር በመገዛቱ ከፍ ከፍ አለ። አባ ገዓርጊና አባ አብርሃም ሌሎቹም አበው ከገድሉ የተነሳ ደስ ይሰኙበትና ያደንቁ ነበር። ሰይጣን ግን በርሱ ቀንቶበት በታላቅ አመታት መታው (ደበደበው) ኹለት ወርም በምድር ላይ ወድቆ ኖረ። ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባለ ጤና አድርጎ አስነሳው።

  + ኤጲስ ቆጶስም እንዲኾን የክብር ባለቤት ቸሩ ጌታችን መርጦታልና የሊቀ ጳጳሳቱ መልእክተኞች መጡ። እርሱም ከአበው መነኰሳት ሊለይ በመኾኑ እጅግ ኀዘን ገባው። ቅዱሳኑም ይህ የእግዚአብሔር ሥራ ነውና አትዘን አሉት። እርሱም ራሱ ለእግዚአብሔር ታእዛዝ ራሱን ዝቅ አድርጎ በጽኑዕ የሚገዛ ኾነ። ሊቀ ጳጳሳቱም በተመይ አገር ላይ ኤጲስ ቆጶስነት ሾመው። ሀብተ ፈውስም ተሰጥቶት በሽተኞችን የሚፈውሳቸው ሆነ፣ በሽታ ያለባቸውም ኹሉ ወደርሱ ይመጣሉ እርሱም ክብር ይግባውና ወደ እግዚአብሔር በምጸለይ ይፈውሳቸዋል።

  + ኹለተኛውም ይርተሠወረውን የማወቅ ሀብተ ጸጋ እግዚአብሔር ሰጠው። ከደግነቱና ከጸጋው የተነሳ ብዙዎች ኤጲስ ቆጶሳት ወደርሱ እየመጡ ከርሱ በታች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ይገዙለት ነበር። እርሱ በሲመታቸው ጊዜ እጁን ጭኖባቸዋልና #እለእስክንድሮስ #ቆዝሞስ #ቴዎድሮስና #ሚካኤል ለሚባሉ ሊቃነ ጳጳሳት አባት ኾነ። የሚያርፍበትንም ቀን በመንፈስ ቅዱስ ባወቀ ጊዜ ሕዝቡን ሰብስቦ በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ አስተማራቸው፣ አዘዛቸው። ለጌታችንም አደራ ሰጣቸው። ከዚህም በኋላ ወደ ወደደው ወደ እግዚአብሔር ኼደ። እያዘኑም በክብር እርሱ ካዘዛቸው ቦታ አኖሩት። ለእግዚአብሔር

ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በጸሎቱ ይማረን፣ በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ሰላም ለከ ሚናስ ኅሩይ
ኤጲስ ቆጵስ ዘሀገረ ተመይ
በእንተ ዘአንጻሕከ ሥጋከ ወልቡናከ እምጌጋይ
ከመ ታእምር ኲሎ ውስተ ልበ ሰብእ ዘይትሔለይ
መጽሔተ አእምሮ ነሣእከ እምልዑል ሰማይ።

✍️፬-ዳግመኛም በዚህች ዕለት  የልዳ ሀገር የኾነው #ሊቀ_ሰማዕታት #ማር_ቅዱስ_ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበትና ድንቅ ተአምርም ያደረገበት መታሰቢያው ነው።

  + ይህም የኾነው ድንቅ ተአምራት የሚደረግባት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ነበረችና ክፉው ከሀዲ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ሊያፈርሳት ፈለገና መኰንኑን ላከው። መኰንኑ አውህዮስም ከቤተ ክርስቶያኒቱ ገብቶ ብዙዎችን በድፍረት ሲገለባብጥ ከሥዕለ አድኅኖው ዘንድ የነበረውን በብርጭቆ የተሠራ መቅረዝ ቢነካው ወርዶ ራሱን በጥብጦ ጣለው። እርሱ ክፉ አሟሟትን ሲሞት አገልጋዮቹ ወስደው ወደ ባሕር ጣሉትና በኃፍረት ወደ አገራቸው ተመለሱ። ንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስም በዚህ ተመሳጭቶ ራሴ አፈርሰዋለሁ ብሎ ቦመጣ የቤተ ክርስቲያኑ ደወል መሃል አናቱን በጥብጦ ጣለው። አንድም የታዘዘ መልአክ መጥቶ ዓይኑን አተፋው፣ ታውሮም ለሰባት ዓመታት ቁራሽ እየለመነ ከኖረ በኋላ፣ ጌታችን የቤተ መንግሥቱን ሰዎች አስነሳበትና በክፉ አሟሟት ሞተ። ጻድቁ ቈስጠንጢኖስም ነገሠ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በቅፉስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን፣ በረከቱም በዝታ ትደርብን ለዘላለሙ አሜን።

ሰላም እብል ለዘአርአየ ትእምርቶ
በልዳ ሀገር በጊዜ ቀደሱ ቢቶ
ጊዮርጊስ መዋዒ ቃለ ጽራህየ በኢያስትቶ
ከመ እስሐብ ፀረ ነፍስየ ይመጥወኒ ቅናቶ
ወለደርብዮቱ ፍጹመ ስሑለ ኲናቶ።

✍️፭-ዳግመኛም በዚህች ዕለት #ዘኖቢስና እናቱ #ዘኖቢያ በሰማዕትነት አረፉ።

  + እኒህም ቅዱሳን ተበይስ ከምትባል አገር ከታላላቆቿ ናቸው። ክርስቲያንም በመኾናቸው በንጉሡ ፊት ከሠሷቸው። ንጉሡም አስቀርቦ አገራቸውንና የሃይማኖታቸውን ነገር መረመራቸው። እነርሱም በኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚያምኑ መሰከሩ። መንኰንኑም ይህን ሲሰማ ተቆጣ፣ ልብሳቸውንም ገፍፈው በአደባባይ በጠጉርቅቸው ሰቅለው እንዲደበድቧቸው አዘዘ። ቢጸልዩ ማሠሪያቸው ተፈትቶላቸው የብርሃን ልብሶችን ለብሰው ተገኙ። ሕዝቡም ይህን ድንቅ ተመልክተው ጌታችን የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስን አመሰገኑት።

  + መኰንኑ ግን ተቆጥቶ እርስ በርስ እንዲተያዩ አድርጎ በመስቀል ሠቀላቸው፣ በእግዚብሔርም ቸርነት ምንም ምን ሳይኾኑ፣ እንዲያውም የእግዚአብሔርን ቃል ሲያስተምሩ መኰንኑ አገኛቸው። ሕዝቡም አይተው እና እየጮኹ በአንድ ቃል አመሰገኑ። ኹለተኛም በስጣቸው የብረት ችንካሮች ያሉባቸውን ኹለት ወንበሮችን እንዲያዘጋጁ አዘዘና በዚያ ላይ አስቀምጠዋቸው በእሳት ምድጃ ውስጥ ጨመሯቸው። ከዚያም ግን በደህና ወጡ። መኰንኑም የውሽባ ቤቱን ጠባቂ ቅዱሳኑን እሳት አንድዶ በውስጡ እንዲጨምራቸው ነገረው። ከዚሃም በደህና ቢወጡ መኰንኑ የሚያደርጋቸውን ነገር ግራ ቢገባው እንዲገድሏቸውና አቃጥለው በነፋስ ውስት እንዲበትኗቸው አዘዘ። በገደሏቸውም ጊዜ ነጐድጓድና መብረቅና ንውጽውጽታ ዝናምም ኾነ።  ብዙዎች ኃምሥ አራት ያህል ሰዎች ሞቱ። በሌሊትም ምእመናን መጥትወ በስውር ወሰዷቸው። በማግስቱም መኰንኑ ሲመጣ በሥጋቸው የኾውን ተአምር ነገሩትና በጌታችን አምኖ ክርስቲያናዊ ኾነ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እናንም በጸሎታቸው ይማረን፣ በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ሰላም ለዘኖብያ ወለዘኖቢስ በኲራ
እለ ተወክፉ ምንዳቤ ወተዓገሡ መከራ
አመ በእሳት ፈቀደ ለነፍሶሙ ያጽዕራ
መኰንነ ሀገር አስተርአየ ማዕከለ ብዙኃን ሐራ
ዐቃቤ ብለኔ ከዊኖ እንዘ ይፀውር ኮራ።

ሰላም እብል ሰማዕታተ ብዙኃነ
ምስለ ዘኖቢስ ወዘኖቢያ ዘአስተኃፈሩ ሰይጣነ
ፈጺሞሙ ስምዐ በጊዜ ለብሱ ግዕዛነ
ሶበ ነጐድጓድ ወመብረቅ ኮነ
ምስለ ሐራሁ መኰንን አምነ።

✍️፮-ዳግመኛም በዚህች ዕለት  ቅዱሥን #ሐዲስ_መርቆሬዎስና ወንድሙ #ዮሐንስ በሰማዕትነት አረፉ።

ሰላም ለመርቆሬዎስ ዘተጋደለ ፈድፋደ
ወለዮሐንስ ምስሌሁ ለአርዑተ ሥቃይ ዘተጸምደ
አመ ወረውዎሙ ሐራ ድኅረ መተሩ ክሣደ
እሳት ውዑይ በድኖሙ ኢያንደደ
እስመ ረከብዎሙ ድኁናነ እምከዊን ሐመደ።

ሰላም እብል ክልኤተ አስካለ
እምሐረገ ወይን ዘበዐፀደ መርዔት በቈለ
አንከሩ ጉባኤ ዘክልኤሆሙ ኃይለ
ድኅረ ተመትረ ሰሚዖሙ እምርእሰ ዮሐንስ ቃለ
ወእምርእሰ መርቆሬዎስ ነጺሮሙ በክሣዱ ስቁለ።

(ምንጭ፥ ስንክሣር ዘወርኃ ኅዳር)
----------------------------------------------------------------
ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው በእንተ ቅዱስ ጊዮርጊስ እስክንድርያዊ ወበእንተ ቅዱሳን ዘኖቢያ ወዘኖቢስ ወበእንተ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሐዲስ ወቅዱስ ዮሐንስ እኁሁ፣ በእንተ ቅዱስ ሚናስ ሊቀ ጳጳሳት ወበእንተ ኲሎሙ ቅዱሳን እለኮነ ተዝካረ በዓሎሙ በይእቲ እለት መሐረነ ለነ ለአባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ አሜን። 

እግዚኦ ተዘከር ኪዳን ዘወሀብኮሙ ለቅዱሳን አግብርቲከ ወአእማቲከ እለ አስመሩ ኪያከ፣ ወሶበ ተዘከርከ ዘንተ ተዘከር ከመ መሬት ንሕነ አባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ፣ ኢታርእየነ ሙስናሃ ለቅድስት ሀገሪትነ ኢትዮጵያ ወለቅድስት ቤተ ክርስቲያን።  ኢታጥፍአነ ተዘኪረከ ዘትካት፣ ፍጡነ ይርከበነ ሳህልከ እግዚኦ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ