እንኳን #ለቅዱስ_አቡናፍር_ገዳማዊ እና #ለቅዱስ_አባ_ዳንኤል #ወቅዱስ_አባ_አኖሬዎስ (ጻድቅ ንጉሥ)፣ ለሌሎቹም ንዑዳን ክቡራን ክብረ በዓላት በሰላም አደረሳችሁ።
የኅዳር ፲፮ ዝክረ ቅዱሳን።
በዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
----------------------------------------------------------------
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
¶ አመ ፲፮ ለኅዳር በዛቲ ዕለት፥ ቅዳሴሃ ለቤተ ክርስቲያን #ዘቅዱስ_ወቡሩክ_አቡናፈ_ገዳማዊ በአፍአ ሀገረ ምስር።
✍️፩-ኅዳር ፲፮ በዚህች ዕለት የከበረና የተመሰገነ #የገዳማዊ_አቡናፍር ከምስር ከተማ ውጭ የተሠራች ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ነው።
ለሰላም ለቅዳሴ ቤትከ በአፍአ ሀገር ዘምስር
እንተ ሐነፅዋ ኬነውት ወጠበብተ ምክር
አቡናፍር አቡየ ሠውረኒ አመ ዕለተ ፍዳ ወፃዕር
በዘከደነከ እምሐሩር ወቊር
እምነ ርእስከ ወጽሕምከ ዘወረደ ጸጒር።
✍️፪-ዳግመኛም በዚህች ዕለት የእስክንድርያ ሀገር አርባ ስምንተኛ ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_አባት_አባ_ዮሐንስ አረፈ።
+ ይህ ቅዱስ የቆጵሮስ ሀገር ሰው ነው። እጅግ ባለጸጋ ነው። አባቱ አገረ ገዥ ነበርና ሚስትም አግብቶ ልጆችን ወለደ፣ ከዚህም በኋላ ሚስቱም ልጆቹም ሞቱ። ይህም ሲኾን ገንዘቡን ኹሉ ለድኆችና ለችግረኞች ሰጠ፣ መጸወተ። እርሱም መንኲሶ በታላቅ ገድል የተጠመደ ሆኖ በጎ ሥራዎችን ትሩፋትን ጨምሮ በመሥራት እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው።
+ በጎ ትሩፋቱን ገድሉንም በተመለከቱ ጊዜ ኤጲስ ቆጶሳት ደስ ተሰኙበትና ይዘው ያለፈቃዱ በግድ በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙትና በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር ላይ አስቀመጡት። የከበረ ወንጌልን አነበበ፣ በሹመቱና በክህነቱም ብርሃን ተገለጸ፣ ብዙዎች ድንቆች የሆኑ ተአምራትንም አደረገ። ለድኆችና ለችግረኞች ሁልጊዜ ያለማቋረጥ የሚሹትን የሚሰጣቸው ሆነ ስለዚህም የሚራራ ዮሐንስ ( #ዮሐንስ_መሐሪ ) ተብሎ ተጠራ። በአይሁድና በአረማውያን ዘንድ የሚያስፈራ ሆነ፣ በመጽሐፈ ገድሉም እንደተጻፈ እጅግ ይፈሩትና ያከብሩት ነበርና መንጋዎቹንም በበጎ አጠባበቅ ጠበቃቸው፣ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን፣ በረከቱም እጽፍ ኹና በእኛ ትደርብን፣ ለዘላለሙ አሜን።
ሰላም እብል ሊቀ ጳጳሳት ማሪ
ኃጢአተ ሕዝብ ዘይሰሪ
እንዘ ይዘሩ ንዋዮ በተሰፍዎ ዐስብ ደኃሪ
እስመ ኢፈቀደ ተረፈ ነዳያን ያጥሪ
ወበእንተዝ ተሰምየ ዮሐንስ መሐሪ።
✍️፫-ዳግመኛም በዚህች ዕለት #ቅዱስ_ኪስጦስ በመኰንኑ እጅ በሰማዕትነት አረፈ።
ሰላም ለከ ሰማዕት ኪስጦስ
በእደ መኰንን መክሲሞስ
ቅሡፈ አባል በኲነኔ ወምቱረ ርእስ
ኀድፈኒ በጸሎትከ ውስተ ዛኅን ወመርስ
አመ ላዕሌየ ያመዓብል ባእስ።
✍️፬-ዳግመኛም በዚህች ዕለት በሮሜ አገር በመኰንን እስክንድሮስ እጅ #ቅድስት_ጣጡስ በሰማዕትነት አረፈች።
+ ይዘውም ወደ መኰንኑ ባቀረቧት ጊዜ ለአማልክት ሠዊ አላት፣ እርሷም ከፈጠረኝ ከጌታዬ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር አልሠዋም ብላ መለሰች። መኰንኑም የፊቷን መሸፈኛ እንዲገልጡ አዘዘ፣ ውበቷ ሊነገር እጅግ የሚያስደንቅ ነበርና ንጉሡ ልቡ እስኪጠፋ ድረስ ኾነ። (እንዲህች ያሉትንና የነቅድስት አርሴማን፣ የነቅድስት አርዋን እና የሌሎቹንም ቅዱሳት ስነ ላህይ በምን ይናገሩታል? ድንቅ ነው!) ለእኅቶቻችን ደግሞ አንዱ ጣዖት የሚሆንባቸውና ከመንግሥተ እግዚአብሔር እየለየ ለክፋት ሠራዊት ግብር እንዲያድሩ የሚያደርጋቸው ነገር ሥነ ላህይ ነው። እንዲህች ያሉት ድንቅ ሰማዕታት ግን ይህንም እንኳ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ መሥዋዕት አድርገው በማቅረብ የቅድስና አክሊልን ይቀበሉበታል።
+ መኰንኑም ሥነ ላህይዋን እንደተመለከተ እባክሽ ይልቅስ ይህን ዕብደትሽን ትተሽ ለአማልክት ሠዊና ንግሥቴ ላድርግሽ አላት፣
ክብር ይግባውና እኔስ ከክርስቶስ መንጋዎች ወገን ነኝ፣ ከርሱም በቀር ለማንም አልሠዋም፣ ባይሆን የአማልክትህን ኃይላቸውን አይ ዘንድ ፍቀድልን አለችው። ፈቀደላትና ወስደው ከቤተ ጣዖቱ ቢያስገቧት ዐይኖቿን ቸሩ ጌታችን ኃይሉን እንዲገልጥ በመማጸን ወደላይ አነሳቻቸው። በኋላም በዚያ ጣዖት ያደረ ጋኔን መጮህ ጀመረ፣ ጣዖታቱም ኹሉ ወድቀው ተሰባበሩ፣ በዚያም አድሮ ሲያስት የቆየው ጋኔን ጣጡስ ሆይ እኔ ከአንቺ ምን አለኝ፣ ከደህና ማደሪያዬ አሳደድሽኝ፣ ንጉሡም ይህን አይቶ ተቆጣና አሥረው በግምባርዋ ደፍተው በበትሮች እንዲደበድቧት በአለንጋዎችም እንዲገርፏት አዘዘ። ከሥጋዋም በወተት አምሳል ነጭ ደም ፈሰሰ። ወደ እግዚአብሔርም በለመነች ጊዜ የሚደበድቧትን የእግዚአብሔር መላእክት ሲያሠቃዩዋቸው ተመለከተች፣ ቅድስት ጣጡስን ግን ሥቃያቸው የማይነካት ሆነ።
+ ኹለተኛም ለተራበ አንበሳ ሰጧት፣ አንበሳው ግን መጥቶ በክብር ከፊቷ ሰገደላትና የእግሮቿንም ትቢያ ላሰ። ከሰማይም እኔ፡ከአንቺ ጋር ነኝና ንጽሕት ጣጡስ ሆይ ደስ ይበልሽ የሚል ቃል መጣ። ንጉሡም ከክፉ ነገር የደረሰባት ምንም ምን እንደሌለ ተመልክቶ ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ። በዚህችም ዕለት የሰማዕትነትን የድል አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለች፣ በሌሊትም የሮሜ ጳጳስት መጥቶ በከበሩ ልብሶች ገነዛት፣ በወርቅና በብር ከተለበጠ የእብነ በረድ ሣጥን ውስጥም ጨመራትና በአማረ ቦታ በክብር አኖራት። ከሥጋዋም ቸሩ እግዚአብሔር ብዙ ድንቆችን ገለጠ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛም በዚህች ሰማዕት ጸሎት ይማረን፣ በረከቷም እጽፍ ኹና ትደርብን ለዘላለሙ አሜን።
ሰላም ለጣጡስ ሥርጉተ አፍኣ ወውስጥ
በምግባር ፍጹም ውርበሃይማኖት ሥሉጥ
አመ ኮነት ሰማዕተ እንበለ ተምያጥ
አሕምሞ ሥጋሃ ኢክህሉ አስዋጥ
ወጸበለ እግራ ለሐሱ አናብስት መሠጥ።
✍️፭-ዳግመኛም በዚህች ዕለት የመነኰስ #አባ_ዳንኤል_ገዳማዊ እባ #የጻድቁ_ንጉሥ_አኖሬዎስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው።
+ይህም አባ ዳንኤል የተባለው ጻድቅ፣ ታላቅ ገድለኛ ሲኾን እንጀራን ዓሣንም ቢሆን ማርንም ዘይትንም ቢሆን ከብቻው ቅጠል በቀር ሳይቀምስ አርባ ዓመት ተኩል በአስቄጥስ ገዳም ኖረ። ከብዙ ዘመንም በኋላ መነኰሳትን የሚፈትን የመመካት ጾር መጣበት። ይህ ፈተና አንድ ጊዜ ታላቁን ቅዱስ አባ መቃርስን በፈተነው ጊዜ ሰውን የሚወድ ቸሩ አምላካችን አባ መቃርስን ወደ ከተማ እንዲኼድና የወንድማማች ሚስቶችን ኹነው ልጆቻቸውን እያሳደጉ በከተማ ከሚኖሩት ኹለት ገድለኛ እናቶች እንዲማርና ጾሩ እንዲጠፋለት አድርጓል። አሁንም ይህ ታላቅ ቅዱስ አባ ዳንኤል የመጣበትን ጾር ቢመለከት መልአከ እግዚአብሔር ተገለጠና ወንድሜ፣ ቸሩ አምላካችን ክርስቶስ እንዲህ ያለውን የመመካት ከትሕትናና ከፍቅር በቀር አይወድምና ተው አለው። አባ ዳንኤልም ጌታዬ ይህን እንድተውና ጦሩም እንዲጠፋልኝ ከኔ የሚበልጥ ጻድቅ አሳየኝ አለው። መልአኩም በሮሜ የነገሠ ንጉሥ ኹኖ ሳለ ነገር ግን በገድሉ ጽኑዕ ታጋይ ተጋዳይ መነኰስ የሆነውን የጻድቁን አኖሬዎስን ነገር ነገረው። አባ ዳንኤልም ይህን ሲሰማ በምድር ላይ ተደፋና በራሱ ላይ አመድ ነስንሶ አለቀሰ
በኃላም ይህን ገድለኛ ንጉሥ ሊያየው ወደደና ጸለየ።
+ ብርህት ደመናም መጣችለትና ተጭኖ ወደ ሮሜው ንጉሥ ዘንድ ኼደ። እንደደረሰም አገልጋዩን ጠርቶ እባክህ ወንድሜ ንጉሡን ማግኘት እሻለሁና የሚያገናኘኝን መኰንን አገናኘኝ አለው። እርሱም እኔ ባስገባህስ አትገባምን? አለው። እግዚአብሔር ይባርክህ ልጄ አስገባኝ አለው። አባቴ ሆይ ግን ምድራዊ የሆነ ሟች ፈራሽ ንጉሥን ስለምን ማየትን ወደድህ አለው፣ እርሱም ቸሩ ጌታዬ ስላዘዘኝ እ
ንጂ ነው አለው። በኋላም ቆየን ለጌታዬ የሚሻውን ገዝቼ ልምጣ ብሎ ወጣና ጥቂት ጨው አምባሻና እና መጻጻ ገዝቶ መጣ። ይህንም ይዞ አብማሻ ጨው መጻጻና የጎመን ቅጠልም ገዝቶ ወደ ጌታው ወደ ንጉሡ እና ወደ ንጉሡ መምህር አባ አውሎጊስ ዘንድ ገባ፣ አባ ዳንኤልንም በውጭ ተወው። ንጉሡም ረዳቱን አንተ አላዋቂ ነህን? ስለምን አባ ዳንኤልን በአፍአ ተውኸው አለውና ከመምህሩ ከአውሎጊስ ጋራ ወጣ። ለአባ ዳንኤልም ሰገዱለት። ሰላምታም ተሰጣጥተው ወደ ቤተ መንግሥት አስገቡትና በአንድነት ተቀመጡ።
+ ዘጠኝ ሰዓትም በሆነ ጊዜ ለማዕድ ሲሰየሙ አባ ዳንኤል እንዳይታመም ፈርቶ ጌቶቼ እንጀራን ባለመብላቴ በእኔ ላይ አታጒረምርሙ፣ እንዳልታመም ፈርቼ ነው አላቸው። ጸሎትንም ጸለዩ፣ ከዚህም በኋላ ንጉሥ አኖሬዎስ አባ ዳንኤልን ስለአመጣጡ መረመረው፣ አባ ዳንኤልም የሚቻልህስ ከሆነ ከንጉሡ ዘንድ አስገባኝ፣ በጌታ ክርስቶስ ትእዛዝ መጥቻለህይና አለው፣ ነገ አስገባሃለሁ አለው። በማግስቱም አኖሬዎስ ዐይን የሚበዘብዝ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፣ አባ ዳንኤልንም አስገቡት በአየውም ጊዜ ፈርቶ ተንቀጠቀጠ፣ ረዳቱም መፍራቱን አይቶ ወደ ማደሪያው መለሰው። ንጉሡም ችሎቱን ሲጨርስ ልብሰ መንግሥቱን ጨርሶ ልብሰ ምንኲስናውን ለብሶ ወደ አባ ዳንኤል መጣ፣ እርሱም ወንድሜ ሆይ በልቤ ያለውን ነግሬው ወደ ቦታዬ እመለስ ዘንድ ወደ ንጉሡ ለምን አላስገባኸኝም አለው። አኖሬዎስም አባቴ ሆይ አልገ አልገባህምን? ለዚህች ምድር ንጉሥ ብለው የሰየሙኝ እኔ ነኝ አለው፣ አባ ዳንኤልን በሰማ ጊዜ ከእግሩ በታች ሰገደለትና አኗኗሩን ሁሉ ይነግረ ዘንድ በጌታችን ስም አማጸነው። አኖሬዎስም በጅግ ሥራው ፈክሞ ከሚያገኘው በቀር (ይህም ሰሌን መታታት ነው) ሳይበላ ሳይለብስ አርባ ዓመታት እንደሆነው፣ የሚተርፈውንም ለድኆች እንደሚሸጥ ምግቡም እንጀራና ጨው ቅጠል መጻጻም እንደሆነ፣ የማንንም ገንዘብ ለመቀማት እንዳልደፈረ ድንግልናውንም መጠበቁን ነገረው።
+ አባ ዳንኤልም ከእግሩ በታች ሰገደለትና አባቴ በአንተ ላይ ስለተመካሁ ይቅር በለኝ አለው። ከዚህም በኋላ አባ ዳንኤል ፈጽሞ እያዘነ ወደ ቦታው ተመለሰ። ከኹለት ወራትም በኋላ ጻድቁ ንጉሥ አኖሬዎስ ከመምህሩ ተማክሮ መንግስቱን ጥሎ ወደ አባ ዳንኤል ኼደ። መልአከ እግዚአብሔርም ተሸክሚ አደረሰው። እነርሱም በአንድነት ሲጋደሉ በፍቅር ኑረው በዚህች ቅድስት እለት በአንድነት አረፉ። እንዲሁም መምህሩ አውሎጊስና ረዳቱ በዚያች ዕለት በአንድነት አረፉ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በቅድስት ጸሎቱ ይማረን፣ በረከቱም እጽፍ ኹና በኹላችን ትደርብን ለዘላለሙ አሜን።
ስውላም ለአኖሬዎስ እንዘ ባዕል ዘአትጸነሰ
ወለዳንኤል ሱታፉ አስኬማ መላእክት ዘለብሰ
እንበይነ አንጽሑ ሥጋ ወእንበይነ ቀደሱ ነፍሰ
እምበዓት መነኰሰ ወእምነ መንበር ንጉሠ
እግዚአብሔር ዮም ኅቡረ አፍለሰ።
ሰላም ለአውሎጊስ ለአኖሬዎስ መምህሩ
ወሰላም ለረድኡ ዘሠናይ ዝክሩ
በዋሕድ ልብ እንዘ ይትፋቀሩ
በውስተ ዓለም ከመ አሐተኔ ነበሩ
በመንግሥተ ሰማይ ዮም ኅቡረ ኀደሩ።
✍️፮-ዳግመኛም በዚህች ዕለት በሐይቅ ዳር እንዳለ ጽጌረዳ መዐዛው የሚጥም #የፊቅጦር መታሰቢያው ነው። በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ሰላም ለከ ነቃዌ መጻሕፍት ማዕነቅ
ለማርያም ድንግል በርእሰ ደብተራ ምጡቅ
ፊቅጦር ምዑዝ እምጽጌ ረዳ ዘሐይቅ
አእሩግ ተፈሥሑ በትምህርተ ዚአከ ጽድቅ
ወበተግሣጽከ ተሐሥዩ ደቂቅ።
(ምንጭ፥ ስንክሣር ዘወርኃ ኅዳር)
----------------------------------------------------------------
ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው በእንተ ቅዱስ አቡናፍር ጻድቅ ገዳማዊ ወበእንተ ቅዱስ ዳንኤል ገዳማዊ ወአኖሬዎስ ጻድቅ ንጉሠ ሮሜ ወበእንተ ቅድስት ጣጡስ ሰማዕት ወቅዱስ ፊቅጦር ምዑዝ ወበእንተ ኲሎሙ ቅዱሳን እለኮነ ተዝካረ በዓሎሙ በይእቲ እለት መሐረነ ለነ ለአባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ አሜን።
እግዚኦ ተዘከር ኪዳን ዘወሀብኮሙ ለቅዱሳን አግብርቲከ ወአእማቲከ እለ አስመሩ ኪያከ፣ ወሶበ ተዘከርከ ዘንተ ተዘከር ከመ መሬት ንሕነ አባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ፣ ኢታርእየነ ሙስናሃ ለቅድስት ሀገሪትነ ኢትዮጵያ ወለቅድስት ቤተ ክርስቲያን። ኢታጥፍአነ ተዘኪረከ ዘትካት፣ ፍጡነ ይርከበነ ሳህልከ እግዚኦ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ