እንኳን #ለቅዱስ_ፊልክስ እና #በዓለ_ቊስቋም፣ ለሌሎቹም ንዑዳን ክቡራን ክብረ በዓላት በሰላም አደረሳችሁ።
የኅዳር ፮ ዝክረ ቅዱሳን።
በዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
----------------------------------------------------------------
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
¶ አመ ፮ ለኅዳር በዛቲ ዕለት፥ ቦአ እግዚእንው ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት ውስተ #ደብረ_ቊስቋም ምስለ እግዝእትነ ቅድስት ድንግል ማርያም ወዮሴፍ አረጋዊ ወሰሎሜ በጊዜ ተመይጦቶሙ እምስደት ወአዕረፉ እምፃማ ፍኖት።
✍️፩-ኅዳር ፮ በዚህች ዕለት ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከአረጋዊ ዮሴፍና ከሰሎምከ ጋር ከስደት በሚመለሱ ጊዜ ወደ #ደብረ_ቊስቋም ገባ፣ በመንገድ ጒዞ ካገኛቸውም ድካም አረፉ።
+ ዳግመኛም በኋላ ዘመን በዚህ በደብረ ቊስቋም ቅዱሳን ሐዋርያቶቹን ሰበሰባቸው፣ ታቦትንና ቤተ ክርስቲያንንም አክብሮ የቊርባን መሥዋዕትንም ሠርቶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለወገኖቹ ሰጣቸው። ለዚህም የእስክንድርያ አገር ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱሳን አባቶቻችን ቄርሎስና ቴዎፍሎስ ምስክሮችን ሆኑ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በረከቷ ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።
ሰላም ለአእጋሪከ ውስተ ደብረ ቊስቋም እለ ጌሣ
ሕፃነ ማርያም ክርስቶስ አመ ጐየይከ ደወለ ንሒሳ
ወአመ በጽሐ ህየ እንዘ ይነሥእ ኃይለ አንበሳ
እንተ ሠመርከ በኅድዓት ለነፍሱ ታፍልሳ
ሰላም ሰላም ለወልደ ዮሴፍ ዮሳ።
✍️፪-ዳግመኛም በዚህች ዕለት የሮሜ አገር ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_አባት_ፊልክስ አረፈ።
+ ይህም ቅዱስ ወላጆቹ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው። የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት አስተማሩት፣ የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት አባ አንስጣስዮስም ዲቁና ሾመው። ኋላም የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ዮስጦስም የዚህን ቅዱስ በጎ ጠባዩንና የጽድቁን የትሩፋቱን ደግነት ተመልክቶ ቅስና ሾመው። እርሱም በአገልግሎቱ የተመሰገነ ደግ አባት ነበርና ከርሱ በፊት የነበረው ሊቀ ጳጳሳት አባ ዲዮናስዮስ በአረፈ ጊዜ ይህን አባት መረጡይ፣ በእግዚአብሔርም ፈቃድ በሮሜ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት። እርሱም የቸሩን አምላክ መንጋዎች በበጎ አጠባበቅ ጠበቃቸው።
+ ትሩስ ቄሣርም ሲሞት፣ ከርሱ በኋላ ቴዎድሮስ ቄሣር ነገሠ። እርሱም ክርስቲያኖችን ያስጨንቅና ያሠቃይ ጀመር። ብዙዎችም ከእጁ ሰማዕትነትን ተቀበሉ። ይህም ደግ አባት ከዚህ ክፉ ከሀዲ ንጉሥ ብዙ ኀዘንና መከራ ተቀብሏል። ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቢያመለክት ይህ ንጉሥ በኹለተኛው ዘመነ መንግሥቱ ሞተም ከርሱም በኋላ ሌላ ከሀዲ ክፉ የኾነ ዲዮቅልጥያኖስ ነገሠ። እርሱም ክርስቲያኖችን በእጅጉ ያሳድዳቸውና ያሠቃያቸው ነበር። ይህም አባ ፊልክስ የክርስቲያኖችን ሥቃይ እንዳያይ ክብር ይግባውና ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ቸሩ አምላክም ጸሎቱን ሰማውና በዲዮቅልጥያኖስ በመጀመሪያው ዘመነ መንግሥቱ አረፈ።
+ ይህም አባት ብዙዎች ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደርሷል፣ ከእርሳቸውም ስለውግዘትና ስለቀናች ሃይማኖት የተመላለሱበት አለ፣ እሊህም ለክርስቲያን ወገን እጅግ የሚጠቅሙ በጎዎች ናቸው። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በጸሎቱ ይማረን፣ በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ሰላም ለፊልክስ ሊቀ ጳጳሳት ዘተኀርየ
ሶበ ፈከረ ሐዲሰ ወአጰንገለ ብሉየ
ኲነኔ ክርስቲያን ኢይርአይ በከመ ጸለየ
ወእምቅድመ ይምክር ላዕሌሁ ዲዮቅልጥያኖስ እኩየ
ሐዋዘ ሰከበ ወኖመ ጥዑየ።
✍️፫-ዳግመኛም በዚህች ዕለት #የአባ_ፍሞስ #የለንዲዎስ #የይላጥስ #የማርትሮስ #የኢላስዎስ #የቆርናልዮስ #የሱኪሮስ #የናውኔኖስ #የሊባዲቆ #የሲላስዮስና #የሰማዕት_ኤስድሮስ ማኅበር የኾኑት የሁለት መቶ ሰባ ኹለት ሰማዕታት መታሰቢያቸው ነው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን፣ በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።
(ምንጭ፥ ስንክሣር ዘወርኃ ኅዳር)
----------------------------------------------------------------
ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው በእንተ ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ ለቅድትስ ሰሎሜ ለቅዱስ ዮሳ ለቅዱስ ፊልክስ ሊቀ ጳጳሳት ወበእንተ ኲሎሙ ቅዱሳን እለኮነ ተዝካረ በዓሎሙ በይእቲ እለት መሐረነ ለነ ለአባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ አሜን።
እግዚኦ ተዘከር ኪዳን ዘወሀብኮሙ ለቅዱሳን አግብርቲከ ወአእማቲከ እለ አስመሩ ኪያከ፣ ወሶበ ተዘከርከ ዘንተ ተዘከር ከመ መሬት ንሕነ አባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ፣ ኢታርእየነ ሙስናሃ ለቅድስት ሀገሪትነ ኢትዮጵያ ወለቅድስት ቤተ ክርስቲያን። ኢታጥፍአነ ተዘኪረከ ዘትካት፣ ፍጡነ ይርከበነ ሳህልከ እግዚኦ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ