እንኳን #ለቅድስት_ሐና_የአምላካችን_አያት (በሥጋ) እና #ለቅዱስ_ጳኲሚስ፣ #ለቅዱስ_ሚናስ_ሰማዕት ለሌሎቹም ንዑዳን ክቡራን ክብረ በዓላት በሰላም አደረሳችሁ።
የኅዳር ፲፩ ዝክረ ቅዱሳን።
በዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
----------------------------------------------------------------
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
¶ አመ ፲፩ ለኅዳር በዛቲ ዕለት፥ ተዝካረ ዕረፍታ #ለቅድስት_ወብፅዕት_ሐና እማ ለእግዝእትነ ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ።
✍️፩-ኅዳር ፲፩ በዚህች ዕለት አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እናቷ የኾነች #የተመሰገነች_የቅድስት_ሐና የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው።
+ ይህችውም ቅድስት በኢየሩሳሌም አገር ከሌዊ ወገን ከካህኑ አሮን ትውልድ የሌዊ የሚልኪ ልጅ የኾነ ማጣት ( 'ጣ' ጠብቆ ይነበብ) ልጁ ናት። ለዚህም ለደግ ሠው ማጣት ሦስት ልጆች አሉት። የታላቂቱ ስም ማርያም ነው። ኹለተኛይቱም ሶፍያ ሲኾን ሦስተኛዪቱ ደግሞ ስሟ ሐና ነው። ማርያም የተባለችው ለባል ድረዋት፣ እመቤታችንን ልጇን ከወለደች በኋላ በስደቷ ወራት ኹሉ ስታገለግላት የነበረችውን ቅድስት እናታችንን ሰሎሜን ወለደች። በትውፊት እንደሚነገረውም ይህች የማጣ'ት ልክ ማርያም፣ የእመቤታችን ጠባቂዋ እንዲሆን የተመረጠው የአረጋዊ ዮሴፍ ሚስት ስትኾን ከቅድስት ሰሎሜ ሌላ ወንዶች ልጆችንም ለቅዱስ ዮሴፍ ወልዳለታለች። ዮሳ፣ ያዕቆብ እና ይሁዳ የሚባሉ ናቸው። ዮሳም በስደት እመቤታችንን ልጇን እንዳይገሉባት ኃይለ አንበሳ ተሰጥቶት የብዙ ቀናቱን መንገድ ፈጥኖ ተጉዞ ወታደሮቹን ቀድሞ የወታደሮቹን መቅረብ የተናገረው ነው። እርሱንም ጌታችን እስከ ምጽአቴ ድረስ ይህችን ድንጋይ ተንተራስ ብሎ አሳርፎታል። ቅዱስ ያዕቆብም ከሰባ ኹለቱ አርድእት ወገን ሲኾን በዘመነ ሐዋርያት በኢየሩሳሌም የመጀመሪያው ኤጲስ ቆጶስ ነበር። ይሁዳ ደግሞ በቅዱስ መጽሐፍ አንዲት ምዕራፍ ያላትን ግሩም መልእክት የጻፈልን ሐዋርያዊ አባት ነው።
+ ሶፍያም ደግሞ ለባል ድረዋት ለታላቁ የሙሽራው ወዳጅ የተባለውን፣ በኤልያስ መንፈስ የሚኼደውን መምህር ወመገሥጽ ባሕታዊ ወሰማዕት ሐዋርያ ወነቢይ ማር ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን የወለደችውን ቅድስት ኤልሳቤጥን ወለደች። ቅድስት ሐና ብፅዕት ደግሞ ከአይሁድ ወገን የከበረውንና ደጉን ቅዱስ ኢያቄምን አጋቧትና የሰማይና የምድር ንግሥት የኾነችውን እመቤታችንን ብቻ ወለዱ።
+ እውነት ላስተዋለው ሰው እንደምን ድንቅ ነው። እንዲህ ያለውን ለሰማይ ለምድር የሚከብድ ስጦታ ንጽሕ ጠብቀው ባይኾንና ቅድስት ሐና እና ቅዱስ ኢያቄም እግዚአብሔርን በእጅጉ የሚያስደስት ምግባር ባይኖራቸው የሔዋን ዕዳ ከፋይ፣ የደቂቀ አዳም ኹሉ ተስፋ፣ በኃጢአት ያጣነውን ንጽሕናና ድንግልና በንጽሓ በመኖር የካሰችልንን እመቤታችንን እንደምን ሊወልዱ ቻሉ? እንደምንስ ደግሞ የአምላካችን አያቶች ሊባሉ ቻሉ?! እፁብ ድንቅ ነው በእውነት። እንግዲህ ልብ ብለን የምናስተውል ከኾነ ከዚህ የምንረዳው ቅድስት ሐና እንደምን ባለ ደስ በሚያሰኝ ገድል ተጸምዳ ትኖር እንደነበር ነው። በሥውር የምትሠራውን የቅድስት ሐናን ገድሏንም እንዳናስተውለው አናውቀውም። ዳሩ ግን ከሴቶች እርሷ እጅጉን ልዕልት እንደኾነች እናውቃለን። እንግዲህ ከሴቶችን ኹሉ እጅጉን የሚበልጥ ትሩፋትና ገድል ባይኖራት እንደምን የአምላካችን አያቱ ልትባል በቃች? ስለርሱ በጥልቅ ለመናገር ግን ከኃጢአታችንም የተነሳ ተሠውሮናልና ታላቅነቷን ግን ሳንጠራጠር በማድነቅ እናመሰግናታለን።
+ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በጸሎቷ ይማረን፣ በቅድስት ጸሎቷ የሚገኝ በረከትም እጽፍ ድርብ ይሁንልን ለዘላለሙ አሜን።
ሰላም ለኪ ለጸሎተ ኲሉ ምዕራጋ
ከመ አስካለ ወይን ዲበ ሐረጋ
ሐና ብፅዕት ተፈስሒ እንበለ ንትጋ
እስመ ረከብኪ ሞገሰ ወአድማዕኪ ጸጋ
እምሔውተ አምላክ ትኩኒ በሥጋ።
✍️፪-ዳግመኛም በዚህች ዕለት ኹለተኛ #የአርኬላዖስ_ሰማዕት #የአበ_ምኔት_ኤልሳዕ ዳግመኛም #የመነኰስ_ጳኲሚስና #የሰማዕት_ማር_ቅዱስ_ሚናስ መታሰቢያቸው ነው። በረከታቸውም በዝታ ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ሰላም ለአርኬላዖስ ሰማዕት
ወኤልሳዕ አበ ምኔት
ወምስሌክሙ ጳኲሚስ ኅቢረ ሥርዓት
ጸልዩ በእንቲአየ ክቡራን ኖሎት
እስመ እመንሱት ያድኅን ጸሎት።
ሰላም ለከ ፈጻሜ ሕማማት በኃሠሣ
ዐቢየ ሃይማኖት ሚናስ እምውሉደ ቅድስት ከኒሳ
ወሰላመ እብላ እንዘ እዌድሳ
ለእምከ አውራንያ እንተ አዕረቅዋ ልብሳ
ወዘቀሠፍዋ ዘባና ወዘርሣ።
(ምንጭ፥ ስንክሣር ዘወርኃ ኅዳር)
----------------------------------------------------------------
ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው በእንተ ቅድስት ወብፅዕት ሐና ወቅዱስ አርኬላዖስ ወቅዱስ ኤልሳዕ አበምኔት ወበእንተ ቅዱስ ጳኲሚስ ወቅዱስ ማር ሚናስ ዐቢይ ሰማዕት ወበእንተ ኲሎሙ ቅዱሳን እለኮነ ተዝካረ በዓሎሙ በይእቲ እለት መሐረነ ለነ ለአባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ አሜን።
እግዚኦ ተዘከር ኪዳን ዘወሀብኮሙ ለቅዱሳን አግብርቲከ ወአእማቲከ እለ አስመሩ ኪያከ፣ ወሶበ ተዘከርከ ዘንተ ተዘከር ከመ መሬት ንሕነ አባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ፣ ኢታርእየነ ሙስናሃ ለቅድስት ሀገሪትነ ኢትዮጵያ ወለቅድስት ቤተ ክርስቲያን። ኢታጥፍአነ ተዘኪረከ ዘትካት፣ ፍጡነ ይርከበነ ሳህልከ እግዚኦ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ