እንኳን #ለቅዱሳን_አእላፍ_መላእክት እና #ለቅዱስ_ተስከናፍር_መኰንነ_ሮሜ፣ #ለቅዱስ_ዘካርያስ_ሊቀ_ጳጳሳት ለሌሎቹም ንዑዳን ክቡራን ክብረ በዓላት በሰላም አደረሳችሁ።
የኅዳር ፲፫ ዝክረ ቅዱሳን።
በዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
----------------------------------------------------------------
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
¶ አመ ፲፫ ለኅዳር በዛቲ ዕለት፥ አዘዙነ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን ከመ ንግበር ተዝካረ በዓሎሙ #ለአእላፍ_ቅዱሳን_መላእክት።
✍️፩-ኅዳር ፲፫ በዚህች ዕለት #የአእላፍ_ቅዱሳን_መላእክትን የበዓላቸውን መታሰቢያ እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘዙን።
+ ውድ የሥላሴ ልጆች፣ የሥላሴን የቸርነቱን ፏፏቴ የምሕረቱንም ውቂያኖስ ለማየት እና በዚያም ሰጥሞ በፍቅር ለመቅረት የምንሻስ ከሆን ፍጡራንን ለምን ፈጠረ ብለን እንጠይቅ። መልሱን ስንፈልግ ቸርነቱ ጋር እንደርሳለንና። ሥላሴ ፍጡራንን ሊፈጥር የሳበው ፍቅሩ እና ቸርነቱ እንጂ ምንም ምን ሌላ አይደለምና።
+ መላእክት የምንላቸው ከሀያ ሁለቱ ሠናያን ፍጡራነ እግዚአብሔር መኻከል አንደኞቹ ናቸው። ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሊቁ በመጽሐፈ አክሲማሮስ እንደሚነግረን፣ ሥላሴ ቅድመ ዓለም በባህርዩ ምስጉን ሁኖ ሲኖር ክብሩ በርሱ ብቻ እንደቀረ ዐይቶ ፍጡራንን ይፈጥር ዘንድ አሰበ። አስቦም አልቀረ በሦስተ መንገድ እና በስድስት እለታት ሀያ ሁለት ወገን አድርጎ ቁጥር የማይገኝላቸውን ፍጡራን ፈጠረ።
የፈጠረባቸውም ሦስት መንገዶች እሊህ ናቸው፥
1/ በሀልዮ (በማሰብ)፥ በዚህ መንገድ የፈጠረው ሰባት ፍጥረት ሲሆን ይህን መንገድ የፈጠረበት ሰማዕያን የሆኑት ፍጡራን መላእክት እስኪገኙ ድረስ ነበር።
2/ በነቢብ (በመናገር)፥ ይህን መንገድ ደግሞ አሥራ አራት ፍጡራንን ፍርጥሮበታል። ይኸውም ከላይ ባለ'ው መንገድ ሰማዕያን ለባውያን የሆኑ ፍጡራን (መላእክት) ተገኝተዋልና በነቢብ መፍጠር ጀመረ።
3/ በገቢር (በመሥራት)፥ በዚህ መንገድ የተፈጠረው ልዩው ፍጡር አንድ ፍጡር ብቻ ነው።
በእሊህ ሦስት መንገዶች ከተፈጡሩት ፍጡራን ወገን ለባውያን (reasonable beings) የሆኑት እና ሥላሴን አመስግነው ከክብረ ሥላሴ ለመውረስ የተፈጠሩት ሁለት ፍጡራን ብቻ ናቸው። እነርሱም መላእክት እና የሥላሴ አርአያ የተሰጠው የሰው ልጅ ናቸው። የሰው ልጅን ጉዳይ ከዚህ አቆይተን ስለመላእክት እንነጋገር።
¶ መልአክ፥ በግእዙ "ለአከ- ላከ" ካለው ግሥ የተገኘ ሲሆን መልእክተኛ ማለት ነው። ይኸውም የፍጡራንን (የሰው ልጆችን ልመና) ቅድመ መንበረ ሥላሴ የሚያሳርጉ፣ የሥላሴን የምሕረትና የቸርነት ስጦታ ወደ ፍጡራን የሚያደርሱ ናቸው።
መላእክት የተፈጠሩት በእለተ እሑድ ሲሆን የተፈጠሩትም ከእሳትና ከነፋስ ነው። ይህም ሲባል አክሲማሮስ እንደሚነገረን ግብራቸውን ማለትም እንደእሳት ረቂቅ እንደነፋስ ፈጣን ለማለት እንጂ ከባህርየ ሥጋ ተፈጥረውስ ቢሆን መፍረስ መበስበስ ባገኛቸው ነበር። ቄርሎስ ዘኢትዮጵያ የተባለው ሊቅ "ዘይሬስዮሙ ለመላእክቲሁ #መንፈሰ ወለእለ ይትለአክዎ #ነደ እሳት- መላእክቱን #መንፈስ (እምደነፋስ ቀሊላን ረቂቃን) የሚላኩትንም #የእሳት ነበልባል የሚያደርጋቸው " እንዳለው በሰአታቱ። ስለዚህም እም ኀበ አልቦ ኀበ ቦ (ካለመኖር ወደ መኖር) አምጥቶ ፈጥሯቸዋል። ሲፈጥራቸው አስቀድሞ መኖሪያቸው ሰማያትን አዘጋጅቶ ነው። ስለዚህ ጉዳይ ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ እንደሚለን ሥላሴ ሰማያትን አስቀድሞ መፍጠሩ፥
ሀ/ መላእክትን አስቀድሞ ፈጥሮ ቢሆን "እርሱ ሲመሠረት እኛ ሌላውን ሠራን፥ እሱ ሲመሠረት አብረን መሠረትን" ባሉ ነበርና ይህችን ድኩም ሕሊና ከመላእክት ለማጥፋት ቀድሞ ሰማያትን ፈጠረ። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ አቡሃ ለሐሰት የተባለ እኩይ ዲያብሎስ ከሰማያት በኋላ ተፈጥሮም እንኳን "እኔ ፈጣሪ ነኝ" ብሏልና።
ለ/ ዳግመኛም ዛሬ አንድ እንግዳ የሚጠራ ሰው ለእንግዳው የሚሆነውን ማደሪያ ሳያዘጋጅ እንዳይጠራው፣ እንዲሁ ሁሉ ሥላሴም የመላእክትን ማደሪያቸውን መኖሪያቸውን አዘጋጅቶ መላእክቱን መፍጠሩ እንዴት የተገባ እንደሆነ ልብ እንበል።
+ #መላእክት ተፈጥሯቸው እንዲህ ሁኖ ሲፈጠሩ፥ በአጠቃላይ መቶ ነገደ መላእክት እና አሥር ሊቃነ መላእክት ሁነው ነበር። እሊህንም ሦስቱን ሰማያት #ኢዮር፣ #ራማ እና #ኤረርን ከአሥር ከተማ አድርጎ ከፍሎ በዚያ አስቀምጧቸዋል።
+ አሥር አሥሩን ነገደ መላእክት አንድ አንድ አለቃ እየሾመ በየከተማው አኑሯቸዋል። የነገደ መላእክቱ ስምም ከላይ ወደ ታች ይህ ነው።
° አጋእዝት፥ አለቃቸው ሳጥናኤል(ነበረ)
° ኪሩቤል፥ አለቃቸው ኪሩብ ሲሆን በዐይን የተሸለሙ የካህናት አምሳል የሆኑ ነገደ መላእክት ናቸው።
° ሱራፌል፥ አለቃቸው ሱራፊ ሲባል ስድስት አክናፍ እና ስድስ እጆች ያሏቸው ነገደ መላእክት እሊህ ናቸው።
° ኃይላት፥ አለቃቸው #መልአከ ኃይል #መልአከ ምክር #መጋቤ ብሉይ ቅዱስ ሚካኤል ነው። ሰይፍን የሚይዙ ሊቃነ መላእክት እሊህ ናቸው። እሊህን አራቱን ሊቃነ፡መላእክት እና አርባውን ነገድ በኢዮር ሰማይ ላይ ኢዮርን አራት ከተማ አድርጎ ከላይ ወደታች አኖራቸው።
° አርባብ፥ አለቃቸው መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብኤል ሲሆን የሥላሴ አጋፋሪ፣ እልፍኝ አስከልካዮች ይላቸዋል አክሲማሮስ።
°መናብርት፥ የእነዚህ አለቃቸው ቅዱስ ሩፋኤል ሲሆን አክሲማሮስ እንደሚነግረን ሀያ አራቱን ካህናተ ሰማይ የተመረጡት ከእነዚህ ነገደ መላእክት ነው።
° ስልጣናት፥ አለቃቸው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሱርያል ሲሆን እሊህን የሥላሴ ነጋሪት መችዎች ለስባሔ የሚያነቁ ይላቸዋል። እሊህን ሦስቱን ሊቃነ መላእክት እና ሠላሳውን ነገደ መላእክት በራማ ሰማይ ላይ ራማን ከሦስት ከተማ አድርጎ ከፍሎ በዚያ አኑሯቸዋል።
° መኳንንት፥ እሊህ ደግሞ አለቃቸው መልአኩ ሰዳክያል (ሰዳካኤል) ይባላል።
° ሊቃናት፥ አለቃቸው መልአኩ ሰላትያል (ሰላታኤል) ይባላል።
° መላእክት፥ አለቃቸው መልአኩ አናንያል (አናንኤል) ይባላል። እዚህ ጋር "መላእክት" ብለን የተናገርነው የነገዱ ስም መሆኑን ልብ ይሏል።
+ እኒህ ረቂቃን ፍጡራን የተለያየ ዓይነት፣ የተለያየ ተፈጥሮ አላቸው። ይኸውም ማለት በክንፋቸው ሀገራትን አኅጉራትን የሚሸፍኑ፣ ቁመታቸው ከጠፈር እስከ በርባሮስ (መሠረተ ምድር) ድረስ የሚደርሱም አሉ። ልዩ ልዩ ዓይነት ናቸው።
+ ሌላኛው ነገር፣ መላእክት ለተልእኮ ካልሆነ በቀር ሥላሴ ካስቀመጣቸው ቦታ በፍጹም አይወጡም። በዚህም ተልእኳቸው ምክንያት በተለያየ ጊዜ ወደ ሰው ልጆች ተልከው በሠሩት ስራ የሚዘከሩ መላእክት አሉ። ለምሳሌም ያህል ብናነሳ ወደ ታላቁ የእግዚአብሔር አፍ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እንሂድ፥
- መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ወደ ጦቢትና ቤተሰቦቹ ተልኮ እንደነበረ እና ስላደረገላቸው ድንቆች በመጽሐፈ ጦቢት እንመለከታለን
- መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል በተለያየ ጊዜ እስራኤልን ሲመራቸው፣ ወደ ዳንኤል ሲላክ፣ ወደ ጌድዮን ወደ ሌሎቹም ሲላክ እናነባለን።
- መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ሠለስቱ ደቂቅን ለማዳን፣ ዘካርያስን ለማብሠር፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሰው ልጆች ስንናፍቀው የነበረውን ደስታ ለማብሠር ወደ አዛኝቷ የማሂት ርግብ ተልኮ ሲሄድ እንመለከታለን።
+ በተፈጥሯቸው መላእክት አያገቡም አይጋቡም። ምክንያቱም ጾታም የላቸው። አንድ ጊዜ እልፍ አእላፋት ወትእልፊተ አእላፋት ተደርገው መቁጠር በማይቻለን መጠን አብዝቶ ፈጥሯቸዋል።
እርሱ ግን እያንዳንዳቸውን በስማቸዋ ያውቃቸዋል። እጹብ ድንቅ ነው። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በአእላፍ ቅዱሳን መላእክት ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
ሰላምንለክሙ ዘኮንክሙ ሶቤ
እግዚአብሔር በዕለተ ይቤ
አእላፈ አእላፋት ሠራዊት እለ ሱራፌል ወእለ ኪሩቤ
እምሐሩረ መርቄ ወእምቊረ ብዙኅ ምንዳቤ
አክናፊክሙ ይኩናነ ግልባቤ።
✍️፪-ዳግመኛም በዚህች ዕለት #ዐሥራ_ሦስት_ወንበዴዎች ስለርሱ በእርሱ ሃይማኖት ከዓለም የተለዩ የከበረ ባፐጸጋ #ቅዱስ_አስከናፍር አረፈ።
+ ይህም ቅዱስ ከሮሜ መኳንንት አንዱ ሲኾን ምጽዋትን እጅግ ይወዳት የነበረ ደግ ሰው ነው። እርሱም ለድኆችና ለምስኪናን ምጽዋትን የሚሰጥና እንግዶችን ተቀብሎ የሚያስተናግድ ይልቁንም መነኰሳት ቤቱን የሚባርኩለት ደግ ሰው ነው። ይህንም ዜናውን የሰሙ በአገሩ የታወቁ የሚዘርፉ ዐሥራ ሦስት ሽፍቶች ወደርሱ ለመኼድና ያለውንም ኹሉ ለመዝረፍ እርሱንም ለመጉዳት ተማከሩ። ኋላም ሾተላቸውን ስለው የምንኲስና ልብስና ቆባቸውን ደፍተው ወደርሱ ኼዱ፣ እርሱም ከደጃፉ እንዳያቸው ደስ ተሰኝቶ አስተናገዳቸው። እግራቸውንም አጠባቸው። እነርሱንም ዐሥራ ኹለቱን ቅዱሳን ሐዋርያት እንደኾኑ፣ አንዱን ደግሞ ጌታችን እንደኾነ አስቧልና ያንን የእግራቸውን እጣቢ ሠላሳ አምስት ዓመታት ከአልጋ ሳይነሳ መጻጉዕ ኹኖ ለነበረው ልጁ ቢሰጠው በዚያ ድኖ ከአልጋው ተነሳ።
+ ይህንም ሲመለከቱ እኒያ ዐሥራ ሦስት ሽፍቶች ደነግውጡ። እርሱም ወደነሱ ቀረበና ከእናንተ መኻከል ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የኾነው ይትኛው እንደኾነ ንገሩኝና ልስገድለት አላቸው። የዚህም ተአምር ዜና በአገሩ ተሰምቶ ብዙዎች ሰዎች እየመጡ የነርሱንም ድውያን ወገኖች እንዲያድኑላቸው ይማጸኗቸው ጀመር። እነርሱም የደበቁትን ሾተላቸውን ይዘው አወጡና እኛስ ሽፍቶች ነበርን ልንዘርፍህና ልንገድልህ ነበር አመጣጣችን፣ አሁን ግን ቸሩ አምላክ በሃይማኖትህ ጽናት ምሮናል ብለው ሾተላቸውን ጥለው ከእርሱ ጥቂት ምሥር ወሰዱና የሃያ አምስት ቀናት የእግር መንገድ ተጉዘው ከበረሃ ገቡ። በዚያም የያዙትን ምሥር አዘሩትና ከዚያ በየቀኑ ሦስት ሦስት ምሥር እየፈለጉ እየተመገቡ ለሠላሳ ዓመታት በጽኑዕ ገድል ተጸምደው ኖሩ።
+ በኋላም አንድ ከሀዲ ንጉሥ ክርስቲያኖችን የሚያሳድድ ተነሣና እሊህን ዐሥራ ሦስቱን ሽፍታ የነበሩ ሰዎች አግኝቶ ገደላቸው። እነርሱም የሰማዕትነትን እና የጽድቅን አክሊል ተቀዳጁ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በእሊህ ቅዱሳንና በቅዱስ አስከናፍር ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
ሰላም ለአስከናፍር መንሥኤ መፃጒዕ እምዐራት
ፀበለ ፈያት ነዚሆ በሃይማኖት
ወሰላም ካዕበ ለእሉ ፈያት
እለ ተጋደሉ መጠነ ሠላሳ ዓመት
ሶበ ነጸርዋ ለዛቲ ትእምርት።
✍️፫-ዳግመኛም በዚህች ዕለት የሀገረ እንጽና ኤጲስ ቆጶስ የከበረ አባት #አባ_ጢሞቴዎስ አረፈ።
+ ይህም ቅዱስ አባት ከታናሽነቱ አንስቶ ልቡ ንጹሕ የኾነ ጻድቅ ሰው ነው። ታላቅ ተጋድሎንም የሚጋደል ነው። የእንጽና አገር መንኰንንም በሃይማኖቱ ምክንያት ጽኑዕ ሥቃያትን እያሠቃየ ወደ እሥር ቤት ይመልሰዋል። በየጊዜውም እንዲህ ያደርግበት ነበር። ከእርሱም ጋራ አብረው የታሠሩ ብዙ ሰማዕታት ነበሩ። እርሱም እሊያን ሰማዕታት እየገድላቸአ ቁጥራቸው እስኪያንስ ድረስ የብዙ ሰማዕታትን ንጹሕ ደም አፈሰሰ። እያሠቃየም ገደላቸው።
+ ከሀዲው ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስን ቸሩ ጌታችን ባጠፋው ጊዜ ታላቁ ጻድቅ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ነገሠ። እርሱም ለአቢያተ ክርስቲያናትና ለምእመናን ነጻነትን አወጀ። በዚህም ምክንያት ይህ ደግ አባት ቅዱስ ጢሞቴዎስም ከእሥር ተፈታ። ከተፈታም በኋላ ለዚያ ሲያሰቃየው ለነበረው ክፉ መኰንን ከጥዋት እስከ ማታ አጽንቶ የሚጸልይለት ኾነ። ይህንም ነገሩን ሰዎች ኺደው ለመኰንኑ በነገሩት ጊዜ፣ እኔስ እንደዚያ አሠቃይቸው ሲረግመኝ የሚኖር ነበር የመሰለኝ፣ እንዲህም ኹኖ ስለኔ ይጸልያልን ብሎ ልቡ በጣም ተነካና አባ ጢሞቴዎስን አስመጣው። የክርስትናንም ሕጓን ያስተምረው ዘንድ ለመነው። አባ ጢሞቴዎስም በሚገባ ቅዱሳን መጻሕፍትን እየተረጎመ አስተማረውና መኰንኑ አመነ። የልጅነትንም ጥምቀት አተመቀው።
+ ከዚህም በኋላ መኰንኑ ክብሩን ቤቱን ትቶ መንኲሶ በገድል ተጸምዶ መኖር ጀመረ። ከአባ ጢሞቴዎስም መንጋዎች ተቆጠረ። አባ ጢሞቴዎስም በቀረ ዘመኑ ኹሉ መንጋዎቹን እያስተማረ በቀናች ሃይማኖትም እያጸናቸው ኑሮ በሰላም በፍቅር በአንድነት አረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ የዚህም አባት በረከት ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ሰላም ለጢሞቴዎስ በገጸ ሰብእ ዘአምኖ
ለእግዚአብሔር አምላክ አድኅኖ
እንዘ ይብል ጸለየ ወሰአለ ለዘኰነኖ
እግዚኦ እግዚኦ ለአበሳሁ ክድኖ
እስመ ለሕይወትየ መርሐ መንገሌከ ኮኖ።
✍️፬-ዳግመኛም በዚህች ዕለት የሀገረ እስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት #አባ_ዘካርያስ አረፈ።
+ ይህም ቅዱስ አባት ከእስክንድርያ ሰዎች ወገን ሲኾን በቤተ ክርስቲያን ንብረት ኹሉ ላይ መጋቢነትና ቅስና ተሾመ። ንጹሕና ድንግልም ነው። በጠባዩም የዋህ ቅን የኾነ በዕድሜውም የሸመገለ ነው። ሊቀ ጳጳሳቱ አባ ፊላታዎስ ባረፈ ጊዜ ኤጲስ ቆጶሳት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ቀጣዩን ሊቀ ጳጳሳት ለመሾም ተሰበሰቡ። የአባ ፊላታዎስም ማረፍ በተሰማ ጊዜ አንድ ሰው ከንጉሡ የሹመት ደብዳቤ አጽፎ መማለጃም ይዞ እየመጣ እንደኾነ ሰሙ። በዚህም እንዴት የቅዱሳን ሐዋርያት ሥርዓት ይጣሳል ብለው አዝነው ጸሎት ያዙ። ከዚህም በኋላ ይህን አባ ዘካርያስን ከቤተ መቅደስ ጫፍ ላይ በመሰላል ሲወርድ በእንስራ ሆምጣጤ ይዞ ሳለ አድጦት ከጫፍ እስከ ታጭ ድረስ ወርዶ ወደቀ። ነገር ግን እንስራው ሳይሰበር ሆምጣጤውም ሳይፈስ ቀረ። ፈጥኖም ተነስቶ ኼደ። ይህንም ተመልክተአ ምልክት አድርገው ይህን ደግ አባት ሊሾሙት መንፈስ ቅዱስ መራቸው።
+ በርሱም ተስማምተው በእስክንድርያ ኹሉ ላይ ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት። ከሹመቱም በኋላ ግን ብዙ ኀዘንና መከራ ተቀብሏል። ከነርሱም አንደኛው፣ አንድ መነኰስ ከአባ መቃርስ ገዳም መጥቶ ኤጲስ ቆጶስነት ሹመኝ አለው። አባ ዘካርያስም መልሶ የቸሩ እግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን፣ አንተም ተመልሰህ በገዳምህ በበጎ ገድል ቆይ አለው። ያም መነኰስ ይህችን በጎ ምክር እንደሰማ ተቆጥቶ ወደ ንጉሡ ይኼድና በከንቱ አባ ዘካርያስን ይከሠዋል። ንጉሡም ይዞ አባ ዘካርያስን ማሠቃየት ይጀምርና ለተራቡ አንበሶት ይሰጠዋል። አንበሶቹ ግን አልነኩትም። የአንበሶቹ ጠባቂ ተንኮል የሠራበት መስሎት ይመልስና የላሕም ደም ቀብቶ ዳግመኛ ከተተው አሁንም ምንም አልነኩትም በዚህም ተደንቆ ይዞ ወደ እሥር ቤት ከተተው። ደግሞ ደግሞም እያወጣ ሃይማኖትህን ተው ያለዚያ አሠቃይሃለሁ እገድልሃለሁ ይለዋል፣ አባ ዘካርያስ ግን ምንም ምን አይፈራውም። ኹለተኛም ብዙ ሃብት ገንዘብ እሰጥሃለሁ አለው። አባ ዘካርያስም በዓለም ያለውን ኹሉ ብትሰጠኝም እኔ ሃይማኖቴን አልተውም አለው። ንጉሡም ጥቂት ጊዜ ካሠረው በኋላ ለቀቀው። እርሱም ወደ አባ መቃርስ ገዳም ኼደና በዚያ ቆየ።
+ ክርስቲያኖችም ለዘጠኝ ዓመት በጽኑዕ ሥቃያት ሲሠቃዩ ከቆዩ በኋላ እግዚአብሔር ምሕረት አወረደና ንጉሡም የጠፉት አቢያተ ክርስቲያናት ዳግም እንዲሠሩ ፈቀደ። አባ ዘካርያስም ብዙ አቢያተ ክርስቲያናትን ዳግም አነጸ። ቸሩ እግዚአብሔር አምላክም በእጆቹ ብዙ ገቢረ ተአምራትን አደረገ። ከነዚህም ኹለቱን ብናነሳ፣ አንድ በለምጽ የተመታ ኤጲስ ቆጶስ ነበር። በአባ ዘካርያስ ጸሎትና በዚያም ኤጲ
ስ ቆጶስ ጸሎት ከለምጹ አንጽቶ አድኖታል። በሌላም ጊዜ እንዲሁ አንድ ድቀት ያገኘው ዲያቆን ነበር። እር
ሱም ከአባ ዘካርያስ እግር ተደፍቶ እያለቀሰ የኾነውን ነገረው። አባ ዘካርያስም ከጨለማ ቤት ዘጋበትና በሦስት በሦስት ቀን ጥቂት ምግብ እየመዘነ ይሰጠዋል። በአርባኛውም ቀን ከለምጹ ፈጽሞ ነጻና ዳነ። እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ወደቤቱ ኼደ። ይህም አባት እንዲህ ቸሩን አምላክ አገልግሎ በሰላም አረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
ሰላም ለዘካርያስ ሊቀ ጳጳሳት ዘየሠይመ
እምድኅረ ፊላታዎስ ኖመ
በእንተ ሃይማኖት ርትዕት እንዘ ይትጋደል ፍጹመ
አናብስት ስእኑ በሊዖቶ ሶበ ወገርዎ ፍጽመ
እንዘ ይቀብዑ እንተ ላሕም ደመ።
(ምንጭ፥ ስንክሣር ዘወርኃ ኅዳር፣ መጽሐፈ አክሲማሮስ)
----------------------------------------------------------------
ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው በእንተ ቅዱሳን አእላፍ ትጉሃን መላእክት ወበእንተ ቅዱስ አስከናፍር ወቅዱሳን ዐሠርቱ ወሠለስቱ ፈያትውያን ወበእንተ ቅዱስ ጢሞቴዎስ ኤጲስ ቆጶስ ወቅዱስ ዘካርያስ ሊቀ ጳጳሳት ወበእንተ ኲሎሙ ቅዱሳን እለኮነ ተዝካረ በዓሎሙ በይእቲ እለት መሐረነ ለነ ለአባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ አሜን።
እግዚኦ ተዘከር ኪዳን ዘወሀብኮሙ ለቅዱሳን አግብርቲከ ወአእማቲከ እለ አስመሩ ኪያከ፣ ወሶበ ተዘከርከ ዘንተ ተዘከር ከመ መሬት ንሕነ አባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ፣ ኢታርእየነ ሙስናሃ ለቅድስት ሀገሪትነ ኢትዮጵያ ወለቅድስት ቤተ ክርስቲያን። ኢታጥፍአነ ተዘኪረከ ዘትካት፣ ፍጡነ ይርከበነ ሳህልከ እግዚኦ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።
t.me @deaconmelakuyifru