በዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
ውድ የሥላሴ ልጆች፣ የሥላሴን የቸርነቱን ፏፏቴ የምሕረቱንም ውቂያኖስ ለማየት እና በዚያም ሰጥሞ በፍቅር ለመቅረት የምንሻስ ከሆን ፍጡራንን ለምን ፈጠረ ብለን እንጠይቅ። መልሱን ስንፈልግ ቸርነቱ ጋር እንደርሳለንና። ሥላሴ ፍጡራንን ሊፈጥር የሳበው ፍቅሩ እና ቸርነቱ እንጂ ምንም ምን ሌላ አይደለምና።
+ መላእክት የምንላቸው ከሀያ ሁለቱ ሰናያን ፍጡራነ እግዚአብሔር መኻከል አንደኞቹ ናቸው። ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሊቁ በመጽሐፈ አክሲማሮስ እንደሚነግረን፣ ሥላሴ ቅድመ ዓለም በባህርዩ ምስጉን ሁኖ ሲኖር ክብሩ በርሱ ብቻ እንደቀረ ዐይቶ ፍጡራንን ይፈጥር ዘንድ አሰበ። አስቦም አልቀረ በሦስተ መንገድ እና በስድስት እለታት ሀያ ሁለት ወገን አድርጎ ቁጥር የማይገኝላቸውን ፍጡራን ፈጠረ።
የፈጠረባቸውም ሦስት መንገዶች እሊህ ናቸው፥
1/ በሀልዮ (በማሰብ)፥ በዚህ መንገድ የፈጠረው ሰባት ፍጥረት ሲሆን ይህን መንገድ የፈጠረበት ሰማዕያን የሆኑት ፍጡራን መላእክት እስኪገኙ ድረስ ነበር።
2/ በነቢብ (በመናገር)፥ ይህን መንገድ ደግሞ አሥራ አራት ፍጡራንን ፍርጥሮበታል። ይኸውም ከላይ ባለ'ው መንገድ ሰማዕያን ለባውያን የሆኑ ፍጡራን (መላእክት) ተገኝተዋልና በነቢብ መፍጠር ጀመረ።
3/ በገቢር (በመሥራት)፥ በዚህ መንገድ የተፈጠረው ልዩው ፍጡር አንድ ፍጡር ብቻ ነው።
በእሊህ ሦስት መንገዶች ከተፈጡሩት ፍጡራን ወገን ለባውያን (reasonable beings) የሆኑት እና ሥላሴን አመስግነው ከክብረ ሥላሴ ለመውረስ የተፈጠሩት ሁለት ፍጡራን ብቻ ናቸው። እነርሱም መላእክት እና የሥላሴ አርአያ የተሰጠው የሰው ልጅ ናቸው። የሰው ልጅን ጉዳይ ከዚህ አቆይተን ስለመላእክት እንነጋገር።
¶ መልአክ፥ በግእዙ "ለአከ- ላከ" ካለው ግሥ የተገኘ ሲሆን መልእክተኛ ማለት ነው። ይኸውም የፍጡራንን (የሰው ልጆችን ልመና) ቅድመ መንበረ ሥላሴ የሚያሳርጉ፣ የሥላሴን የምሕረትና የቸርነት ስጦታ ወደ ፍጡራን የሚያደርሱ ናቸው።
መላእክት የተፈጠሩት በእለተ እሑድ ሲሆን የተፈጠሩትም ከእሳትና ከነፋስ ነው። ይህም ሲባል አክሲማሮስ እንደሚነገረን ግብራቸውን ማለትም እንደእሳት ረቂቅ እንደነፋስ ፈጣን ለማለት እንጂ ከባህርየ ሥጋ ተፈጥረውስ ቢሆን መፍረስ መበስበስ ባገኛቸው ነበር። ቄርሎስ ዘኢትዮጵያ የተባለው ሊቅ "ዘይሬስዮሙ ለመላእክቲሁ #መንፈሰ ወለእለ ይትለአክዎ #ነደ እሳት- መላእክቱን #መንፈስ (እምደነፋስ ቀሊላን ረቂቃን) የሚላኩትንም #የእሳት ነበልባል የሚያደርጋቸው " እንዳለው በሰአታቱ። ስለዚህም እም ኀበ አልቦ ኀበ ቦ (ካለመኖር ወደ መኖር) አምጥቶ ፈጥሯቸዋል። ሲፈጥራቸው አስቀድሞ መኖሪያቸው ሰማያትን አዘጋጅቶ ነው። ስለዚህ ጉዳይ ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ እንደሚለን ሥላሴ ሰማያትን አስቀድሞ መፍጠሩ፥
ሀ/ መላእክትን አስቀድሞ ፈጥሮ ቢሆን "እርሱ ሲመሠረት እኛ ሌላውን ሠራን፥ እሱ ሲመሠረት አብረን መሠረትን" ባሉ ነበርና ይህችን ድኩም ሕሊና ከመላእክት ለማጥፋት ቀድሞ ሰማያትን ፈጠረ። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ አቡሃ ለሐሰት የተባለ እኩይ ዲያብሎስ ከሰማያት በኋላ ተፈጥሮም እንኳን "እኔ ፈጣሪ ነኝ" ብሏልና።
ለ/ ዳግመኛም ዛሬ አንድ እንግዳ የሚጠራ ሰው ለእንግዳው የሚሆነውን ማደሪያ ሳያዘጋጅ እንዳይጠራው፣ እንዲሁ ሁሉ ሥላሴም የመላእክትን ማደሪያቸውን መኖሪያቸውን አዘጋጅቶ መላእክቱን መፍጠሩ እንዴት የተገባ እንደሆነ ልብ እንበል።
+ #መላእክት ተፈጥሯቸው እንዲህ ሁኖ ሲፈጠሩ፥ በአጠቃላይ መቶ ነገደ መላእክት እና አሥር ሊቃነ መላእክት ሁነው ነበር። እሊህንም ሦስቱን ሰማያት #ኢዮር፣ #ራማ እና #ኤረርን ከአሥር ከተማ አድርጎ ከፍሎ በዚያ አስቀምጧቸዋል።
+ አሥር አሥሩን ነገደ መላእክት አንድ አንድ አለቃ እየሾመ በየከተማው አኑሯቸዋል። የነገደ መላእክቱ ስምም ከላይ ወደ ታች ይህ ነው።
° አጋእዝት፥ አለቃቸው ሳጥናኤል(ነበረ)
° ኪሩቤል፥ አለቃቸው ኪሩብ ሲሆን በዐይን የተሸለሙ የካህናት አምሳል የሆኑ ነገደ መላእክት ናቸው።
° ሱራፌል፥ አለቃቸው ሱራፊ ሲባል ስድስት አክናፍ እና ስድስ እጆች ያሏቸው ነገደ መላእክት እሊህ ናቸው።
° ኃይላት፥ አለቃቸው #መልአከ ኃይል #መልአከ ምክር #መጋቤ ብሉይ ቅዱስ ሚካኤል ነው። ሰይፍን የሚይዙ ሊቃነ መላእክት እሊህ ናቸው። እሊህን አራቱን ሊቃነ፡መላእክት እና አርባውን ነገድ በኢዮር ሰማይ ላይ ኢዮርን አራት ከተማ አድርጎ ከላይ ወደታች አኖራቸው።
° አርባብ፥ አለቃቸው መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብኤል ሲሆን የሥላሴ አጋፋሪ፣ እልፍኝ አስከልካዮች ይላቸዋል አክሲማሮስ።
°መናብርት፥ የእነዚህ አለቃቸው ቅዱስ ሩፋኤል ሲሆን አክሲማሮስ እንደሚነግረን ሀያ አራቱን ካህናተ ሰማይ የተመረጡት ከእነዚህ ነገደ መላእክት ነው።
° ስልጣናት፥ አለቃቸው መልአከ ጥበብ ከሣቴ ምስጢራት መራሔ ብርሃናት የሆነው ቅዱስ ዑራኤል ሲሆን እሊህን የሥላሴ ነጋሪት መችዎች ለስባሔ የሚያነቁ ይላቸዋል። እሊህን ሦስቱን ሊቃነ መላእክት እና ሠላሳውን ነገደ መላእክት በራማ ሰማይ ላይ ራማን ከሦስት ከተማ አድርጎ ከፍሎ በዚያ አኑሯቸዋል።
° መኳንንት፥ እሊህ ደግሞ አለቃቸው መልአኩ ሰዳክያል (ሰዳካኤል) ይባላል።
° ሊቃናት፥ አለቃቸው መልአኩ ሰላትያል (ሰላታኤል) ይባላል።
° መላእክት፥ አለቃቸው መልአኩ አናንያል (አናንኤል) ይባላል። እዚህ ጋር "መላእክት" ብለን የተናገርነው የነገዱ ስም መሆኑን ልብ ይሏል።
+ እኒህ ረቂቃን ፍጡራን የተለያየ ዓይነት፣ የተለያየ ተፈጥሮ አላቸው። ይኸውም ማለት በክንፋቸው ሀገራትን አኅጉራትን የሚሸፍኑ፣ ቁመታቸው ከጠፈር እስከ በርባሮስ (መሠረተ ምድር) ድረስ የሚደርሱም አሉ። ልዩ ልዩ ዓይነት ናቸው።
+ ሌላኛው ነገር፣ መላእክት ለተልእኮ ካልሆነ በቀር ሥላሴ ካስቀመጣቸው ቦታ በፍጹም አይወጡም። በዚህም ተልእኳቸው ምክንያት በተለያየ ጊዜ ወደ ሰው ልጆች ተልከው በሠሩት ስራ የሚዘከሩ መላእክት አሉ። ለምሳሌም ያህል ብናነሳ ወደ ታላቁ የእግዚአብሔር አፍ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እንሂድ።
- መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ወደ ጦቢትና ቤተሰቦቹ ተልኮ እንደነበረ እና ስላደረገላቸው ድንቆች በመጽሐፈ ጦቢት እንመለከታለን
- መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል በተለያየ ጊዜ እስራኤልን ሲመራቸው፣ ወደ ዳንኤል ሲላክ፣ ወደ ጌድዮን ወደ ሌሎቹም ሲላክ እናነባለን።
- መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ሠለስቱ ደቂቅን ለማዳን፣ ዘካርያስን ለማብሠር፣ ከሁሉም፡በላይ ደግሞ የሰው ልጆች ስንናፍቀው የነበረውን ደስታ ለማብሠር ወደ አዛኝቷ የማሂት ርግብ ተልኮ ሲሄድ እንመለከታለን።
+ በተፈጥሯቸው መላእክት አያገቡም አይጋቡም። ምክንያቱም ጾታም የላቸው። አንድ ጊዜ እልፍ አእላፋት ወትእልፊተ አእላፋት ተደርገው መቁጠር በማይቻለን መጠን አብዝቶ ፈጥሯቸዋል። እርሱ ግን እያንዳንዳቸውን በስማቸዋ ያውቃቸዋል። እጹብ ድንቅ፡ነው።
ይቆየን።
©ዘዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
ከዲያቆን መልአኩ ይፍሩ ዘውሉደ ብርሃን የመልአኩ ቅዱስ ሚካኤልን የሲመት ክብረ በዓል በማስመልከት ተጻፈ።
ኅዳር ፲፪፣ ፳፻ወ፲፩ ዓ.ም
ሲቹዋን ቸንዱ፣ ቻይና