ቅዳሜ 4 ኖቬምበር 2017

የቅዱስ ቆጵረስ እና የቅዱስ ፔታርፔሞቲስ የጋድሎ (ክፍል ሦስት)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

(ምንጭ፦The paradise of the holly fathers by St. Athanasius, volume 1
ትርጉም፦ ዲያቆን መልአኩ ይፍሩ ዘውሉደ ብርሃን)

የተዋሕዶ እንቊ ልጆች እንደምን አላችሁ። በቸርነቱ ጠብቆ እና በመግቦቱ ምንም ሳያጓድልብን ያኖረን አምላከ ቅዱሳን ይመስገን። በዛሬው እለት አስደናቂውን የቅዱስ ፔታርፔሞቲስ እና የቅዱስ ቆጵረስን ተጋድሎ ታሪክ ካቆምንበት እንቀጥላለን። ቀድኤተ እግዚአብሔር እና የቅዱሳኑ ምልጃ አይለየን።

            እርሱም መለሰ እንዲህ ባለው ኹኔታ አለብስሃለሁ፤ ከዚያም ይበቃኛል እስክትነኝ ድረስ በከፈን እሸፍንሃለሁ(እገንዝሃለሁ)። ያም ደቀ መዝሙር አረፈና የፔታርፔሞቲስ ቃልም ተፈጸመ። እግዚአብሔርንም በመፍራት በመልካም መንገድ ከገነዘው በኋላ በዙሪያቸው በተሰበሰቡት ሁሉ ፊት ድምጹን ከፍ አድርጎ ሆይ፣ በመልካም ኹኔታ (እንደምትሻው) ገንዤኻለሁ ወይንስ የሚገድልህ ነገር አለ? በማለት ጠየቀው። የሞተውም ሰው ሁሉም እየሰሙት እንዲህ በማለት ድምጹን አሰምቶ ተናገረ(ድምጹን ያሰማው ከሰማይ መሆኑን፣ የምንናፍቃት ገነት በእንውነት ያለሐሰት እንዳለች እኛም ሕያዋን እንደሆን ልብ ይሏል) አባቴ ሆ ይ፣ ቃልህን ፈጽመሃል፤ እንደሚገባ አድርገህልኛል። በዚያ በተሰበሰቡት ኹሉም ዘንድ ድንቅ ሆነባቸው እና እግዚአብሔርንም አመሰገኑ። ይህም ቅዱስ ሰው እንደልማዱ ወደ በረሓ ሄደ፤ ልክ ከጥፋት እንደሚያመልጥ ሰው፣ በየእለቱም ራሱን በጸሎቱ እና በተጋድሎው ይገዛ ዘንድ ወደ በረሓው ሄደ።

ከነዚህም ነገሮች ኹሉ በኋላ ከበረሓው ወጣና የታመሙትን ደቀ መዛሙርቱን ሊያገለግላቸው ተለይቶ (ከበረሓው ወጥቶ) ሄደ፤ ከነዚያም አንደኛው ደቀ መዝሙሩ ለመሞት ቀርቦ ነበር፤ የሚሞትበት እለት እንደቀረበ ይኽን ነገር እንደሚኾን እግዚአብሔር ገልጦለት ነበር። (ክፉ ነገር እንደሚሆን፣ እንደሚከሰት አስቧልና) ዳግመኛም ጨለማ እንዳይደርስባችሁ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማም የሚመላለስ ወዴት እንዲሄድ አያውቅም።(ዮሐ 12 ፡ 35) የተባለው የጌታችንን ቃል ይፈጽም ዘንድ ከመሸ ወደ መንደሩ ይገባ ዘንድ አልፈቀደም። ቀኑ እየመሸ ጀንበርም እያዘቀዘቀች መኾኑን በተመለከተ ጊዜ (ፀሓይን) ወደ መንደሩ እስክገባ ድረስ በመንገድሽ ላይ ቁመሽ ጥቂት ጊዜ ቆዪኝ በማለት አዘዛት። ፀሓይም ፔታርፔሞቲስ ወደ መንደሩ እስኪደርስ ድረስ ወደ ምእራብም ሳትጠልቅ፣ ወደ ምሥራቅም ሳትመለስ በዚያው ቦታ ጸንታ ቆመች።

ይህ ክስተትም በመንደሩ ባሉት ኹሉ ዘንድ ታውቆ ነበርና ኹሉም ሮጠው ከዚያ ቦታ ቆመው ለዘዥም ጊዜ አፍጥጠው ሲመለከቱ ቆዩ። ፔታርፔሞቲስንም ከበረሓው ሲመጣ በተመለከቱት ጊዜ ‘የዚህች የፀሓይ ወደማደሪያዋ አለመጥለቅ ምልክቱ ምንድር ነው በማለት ጠየቁት። እርሱም መልሶ ‘የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል እምነት ቢኖራችሁ ከዚህ የበለጡ እና የሚያስደንቁ ተአምራትን ታደርጋላችሁ(ማቴ 17 ፡ 20) ያለውም የጌታችንን ቃል አታስታውሱምን? አላቸው። ይኽንንም ነገር በሰሙ ጊዜ ታላቅ ፍርሐትና ድንጋጤ በነርሱ ላይ ኾነ፤ እናም ይኽን ያደረገውና ፀሓይን እንዳትጠልቅ ያደረጋት እርሱ እንደኾነ ወዲያውኑ ዐወቁ። ከነርሱም ብዙዎቹ ከርሱ ጋር ቆዩና የርሱ ደቀ መዛሙርት ኾኑ።

ከዚህም በኋላ ወደ አንደኛው ታሞ ወደነበረው ደቀ መዝሙሩ ቤት ሄደና ደቀ መዝሙሩን ሙቶ አገኘው። ያ የሞተ ሰው ወደ ተቀመጠበት ሥፍራ ተጠጋና ጸለየ፤ ከዚያም ሳመውና ሆይ፣ አሁን ወደ እግዚአብሔር ተለይተህ ትኼድ ዘንድ ትወዳለህ ወይንስ በሕይወት በዚህ አካልህ መቆ የትን ትሻለህ? በማለት አናገረው። የሞተውም ተነስቶ ተቀመጠና ‘ከክርስስ ጋር እኾን ዘንድ ይኽን አካል ትቼ እንድኼድ ይሻለኛል፤ በዚህ አካል መቆየትን አልሻምና በማለት መለሰለት። ያም ቅዱስ ሰው ‘በሰላም እረፍ ልጄ፤ ወደርሱም ትኼድ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ስለእኔ ለምን አለው። ወዲያውኑም ቅዱሱ ሰው ይህን እንደተናገረ ሰውየው በመቀበሪያው ላይ ዐረፈ። በዚያም በቆሙት ኹሉ ዘንድ ታላቅ ፍርሐት ኾነ፤ ‘በእውት ይህስ ሰው የእግዚአብሔር ሰው ነው በማለትም ተናገሩ። ቅዱሱም ሰው በጥንቃቄ ካለበሰው(ከገነዘው) በኋላ፣ ምሽቱን ኹሉ በትጋትና በንቃት ከርሱ ጎን ኾኖ መዝሙራትን እየዘመረ እና እየጸለየ ከቆየ በኋላ በመልካም ኹኔታ ቀበረው።

ከዚያም ፔታርፔሞቲስ ሌላውን የታመመ ወንድም ሊጠይቅ ሄደ። . . .  
(ቅዱስ ፔታርፔሞቲስ ምን ሊያደርግ ይሆን የሄደው? ከዚያ ደግሞ ወደየት ይሄድ ይሆን? በቀጣዩ ጦማር እንመለከታለን። ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።) ወስብሐት ለእግዚአብሔር። ይቆየን።
                                                                                    ©ዘዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
               ጥቅምት 25/ 2010 ዓ.

                                                                                    ጎንደር/ ኢትዮጵያ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ