በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
(በዲያቆን መልአኩ ይፍሩ ዘውሉደ ብርሃን)
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች የእግዚአብሔር ሰላም በያላችሁበት ይብዛላችhu።
ለዛሬ ስለደቀመዝሙርነት በጥቂቱ እንነጋገራለን።

ደቀ መዝሙር ማለት መምህሩ በኼደበት የሚኼድ፣ በዋለበት ውሎ ባደረበት የሚያድር፣ በመምህሩ ምክርና ትእዛዝ የሚመ’ራ፣ መምህሩን ለመታዘዝና ለማገልገል የተጋ እና የነቃ ነው። ደቀመዝሙር ሁልጊዜም ቢኾን ለማገልገል
የተጋ እና የነቃ ትሑት የኾነ፣ ለመምህሩም ያለውን ፍቅር በሥራ (በመታዘዝ እና ይኽን በመሰለው ኹሉ) የሚገልጽ ነው። ስለደቀመዝሙርነት
እና ስለደቀ መዝሙር ምንነት በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ክፍሎች በቅዱሳኑ ሕይወት ተቀምጦ እናገኘዋለን።
ለምሳሌም ያህል ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ ኤልሳዕን
ደቀመዝሙሩ አድርጎ እንደጠራው እንመለከታለን።
“ ከዚያም ሄደ፥ የሣፋጥንም ልጅ ኤልሳዕን በአሥራ ሁለት ጥማድ በሬዎች ሲያርስ፥ እርሱም ከአሥራ
ሁለተኛው ጋር ሆኖ አገኘው። ኤልያስም ወደ እርሱ አልፎ መጐናጸፊያውን ጣለበት። በሬዎቹንም ተወ፥ ከኤልያስም በኋላ ሮጦ። አባቴንና
እናቴን እስማቸው ዘንድ፥ እባክህ፥ ተወኝ፥ ከዚያም በኋላ እከተልሃለሁ አለው። እርሱም፦ ሂድና ተመለስ ምን አድርጌልሃለሁ? አለው።
ከእርሱም ዘንድ ተመልሶ ሁለቱን በሬዎች ወስዶ አረዳቸው፥ ሥጋቸውንም በበሬዎቹ ዕቃ ቀቀለው፥ ለሕዝቡም ሰጣቸው፥ በሉም እርሱም ተነሥቶ
ኤልያስን ተከትሎ ሄደ፥ ያገለግለውም ነበር። ”/1ኛ ነገ 19፡19-21/
ለነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኤልሳዕም ግያዝ የሚጋል
ደቀ መዝሙር እንደነበረው ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል። ግያዝም ኤልሳዕ በላከው ቦታ ኹሉ እየተላከ፣ ያዘዘውንም እያደረገ ያገለግለው
እንደነበር እንመለከታለን። ሐዲስ ክዳንም ላይ ስንመጣ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን በዋለበት እየዋሉ፣ካደረበት እያደሩ፣ እየታዘዙት
ቃሉንም እየሰሙ አብረውት ከርሱ ሳይለዩ እንደቆዩ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል።
እነርሱም ጌታችን ካረገ በኋላ እንኳን በነበራቸው ሕይወት የመምህራቸው ደቀመዛሙርት መኾናቸውን አሕዛብ እንኳን እስኪመሰክሩላቸው
ድረስ የተገለጠ ምግባር ነበራቸው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ቅዱስ ጢሞቴዎስን ጨምሮ ደቀመዛሙርት ነበሩት።
ታዲያ እንዲህ የምንናገርለት ደቀመዝሙርነት እንደምን
ያለ ሰብእናን የተላበሰ ይኾን? ምን ዓይነት ነገር ያለበት ይኾን? እውነተኛ ደቀመዝሙርስ መለያው ምንድነው? ይኽን እና ሌኦችንም
የሚነሱብንን ጥያቄዎች በሚከተለው መልስ እናገኝባቸዋለን።
እውነተኛ ደቀመዝሙር ኹልጊዜም፦
v የጌታውን(የመምህሩን) ቤት እና ተማሪዎችአክብሮ የሚያስከብር፣ ጠብቆ የሚያስጠብቅ ነው።
o ደቀ መዝሙር ኹጊዜም ቢኾን የሚኖርባትን
የመምህሩን ቤት በቃልም በግብርም ማስጠበቅ ይገባዋል። ያቺን ቤት መምህሩ እዚያ ያለችበት ቦታ ላይ ለማድረስ እና ለማቅናት እጅግ
ብዙ ዋጋ የከፈለባት ናት። በተለይም በሀገራችን ያለውን የቆሎ ትምህርት የአብነት ትምህርት ስንመለከት፣ መምህራኑ ከእድሜያቸው ጀምሮ
ያንን ጉባኤ ቤት ለማቆም እና ተማሪዎችን ለማስተማር እጅግ ብዙ ዋጋ
ይከፍላሉ። ከአላውያን የሚደርስባቸውም እንግልት እና ግፍ የሚነገር አይደለም። በዘመነ ሰማእታት አዲስ የሚከረሰተኑ(ክርስቲያን የሚኾኑ)
ምእመናንን በግልጽ ሲያስተምር የሚገኝ የቤተክርስቲያን መምህር ይገደል ስለነበር እና የሚማሩትንም ክርስቲያኖች ስለክርስትና ሳያውቁ እንዳይቀሩ ሲባል በዋሻ፣በካታኮምፕ ውስጥ ያስተምሯቸው ነበር።
o የክርስቶስ ደቀመዛሙርት ለመኾን የምንሻ
ከኾን፣ የርሱን የመምህራችንን ቤት ዳግመኛም የቅዱሳን ሊቃውን ት ቤት የኾነችውን ቅድስት ቤተክርስቲያንን ልንጠብቃት ያሻል። እርሷን ለመመስረት ሲል የቤተ ክርስቲያን ራስ ኢየሱስ
ክርስቶስ የከፈለውን የመከራ መስቀል ዋጋ እያሰብን አክብረን እንደቅዱሳኑ ልናስከብራት ያስፈልጋል። ቅዱሳን መራራ ሞትን እንኳን
እንዲታገሱ ያደረጋቸው የመምህራቸውን ቤት ቤተክርስቲያንን አንድም ሕንጻ ሥላሴ የኾነውን ሰውነታቸውን ላለማስደፈር፣ አክብረው በማስከበር
ነው።
“በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን
ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” /ሐዋ
20፡28/
o ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን ስለወደዳት
ለራሱ እንኳን ሳይሳሳ ደሙን ከፍሎ እንደወደዳት በሥራ ገለጸ። እኛ ደግሞ እንዲህ የተጠነቀቀላትን ቤት እንዴት ልንጠነቀቅላት እንዲገባ ልብ ይሏል።
o ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ነገረ ሥጋዌን
ባስተማረበት ትምህርቱ ላይ ሲናገር፣ የክርስቶስ በሥጋ መገለጥ ልዩ ስለኾነ ቸርነቱን በማሰብ ልንደነቅ ያስችል ይኾናል እንጂ እንዴት
ይኾናል ብሎ ሊያስክድ እንደማይችል አሕዛብን እና አይሁድን እየገሠጸ ያስረዳል። የተገለጠው አዳኙ አኹን በተለየ መንገድ ሥጋን ተዋሕዶ
ተገለጠ እንጂ ቀድሞውንም ከመገለጡ በፊት በትልቆቹም በትንሾቹም ፍጡራን በውስጥ በአፍአ ይኖር የነበረ ነው። ስለዚህ ይኽ ድንቅ አምላክ የኛንም ሰውነት ማደሪያው አድርጎ በውድ
ዋጋ በንጹሕ ደም ገዝቶታልና ይህን የቅዱሱን ቤት አክብረን ማስከበር፣
ጠብቀን ማስጠበቅ ይገባናል።
o ይኽን ቤተመቅደስም ለማስጠበቅ የምንጠቀምባቸውን
መንገዶች ቅዱስ መጽሐፍ እንደነገረን እንዲህ መዘርዘር እንችላለን።
§ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ የቅዱሳንን
ሕይወት በመመልከት ራስን በዚያ ማነጽ ይገባል
§ ኃጢአትን በመናዘዝ ራስን ከሸክም ነጻ
በማድረግ ለቅዱሱ ማደሪያ የኾነውን ቤተመቅደስ በጎ መዓዛን እንዲኖረው፣ እንደእጸ ሕይወት የማይሰለች የሚናፈቅ፣ መልካም መዓዛ እንዲኖረው
ለማድረግ እየጣርን ቅዱሳኑን እና ራሱን ቅዱሱን እንድረዱን መጠየቅ ይገባናል።
§ ከቅዱስ ምሥጢር ኹልጊዜም ልንለይ አይገባም።
ቅዱስ ምስጢርን መሳተፍ ጌታችን በቅዱስ ወንጌል እንደነገረን፣ ቅዱሱ በቤቱ ገብቶ ከእኛ ጋር እራት እንዲበላ እና ሰላምን እንዲሰጠን
ሕይወትን እንዲሰጠን ያደርጋልና ይኽን ልናስብበት እና ልንተጋበት ይገባል።
ይቆየን !
በቀጣዮቹ ክፍሎች ሌሎቹን ነገሮች እናነሳቸዋለን።አምላከ ቅዱሳን ጾሙን የበረከት
እና የንስሐ፣ ወደርሱም የምንቀርብበት ያድርግልን።
ዘዲያቆን
መልአኩ ይፍሩ©
ኅዳር 19/ 2010 ዓ.ም
ጎንደር/ ኢትዮጵያ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ