ሐሙስ 23 ኖቬምበር 2017

††† ጾመ ነቢያት በ15 ወይስ በ16 . . . †††



አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

      ውድ ኦርቶዶክሳውያን ወንድሞችና እኅቶች እንኳን ለጾመ ነቢያት በሰላም አደረሳችሁ። እግዚአብሔር አምላካችን ለሰውልጅ ገና ሲፈጥረው ጀምሮ ያስተማረው ነገር ብኖር አንዱ ጾም  ነው። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ፈጣሬ አለማት መድኃኒታችን እና ተኹላችንም መገኛ እግዚአብሔር አዳምን ፈጥሮ በገነት ካኖረው በኋላ ከእጸ በለስ በቀር ኹሉን ፈቅዶለት ነበር። እጸ በለስን ግን የፈጣሪ እና የፍጡር መለያ፣ የአዳም ፍቅር መገለጫ ትኾን ዘንድ፣ ጾምንም ያዘክር ዘንድ የሕግ ዛፍ ኹና ተሰጥታዋለች። ከምክረ እግዚአብሔር ከሕይወቱ ይልቅ አዳም ምክረ ከይሲን በመስማቱ ሲወድቅም፣ መፍቀሬ ሰብእ የኾነው አምላካችን አዳምን ያድነው ዘንድ ቃል ሲገባለት አዳም ይኽን ቃልኪዳን እስኪያገኝ ድረስ፣ ካገኘም በኋላ እየጾመ እየሰገደ እንደተጋደለ እንመለከታለን።
      ነቢያት ቅዱሳንም ይኽን ለአዳም የተሰጠውን ተስፋ በማድረግ በጾም በሱባኤ እየተጉ ይጠባበቁ ነበር። እርሱንም በተስፋ ሲጠብቁት በጾም እና በሱባኤ በመትጋት ነበር። ቅዱስ ያሬድም “ጾም ትፌውስ ቁስለ ነፍስ፣ ወታጸምም ኲሉ ዘሥጋ ፍትወታት” እንዳለው በጾም እና በጸሎት ምግባራት መጸመድ፣ ልቡናን ለመሰብሰብ ለሰቂለ ሕሊና እና ልብን ወደሰማያዊ ጉዳዮች ለመውሰድ እጅግ ወደር የሌለው ነው።በጾም ምክንያት ትኅትናን ገንዘብማድረግ ይቻላል። አምላከ ኅሩያን ቅዱሳን በቸርነቱ በረከተ አጽዋማትን ኹሉ ያድለን።
 ††† ጾመ ነቢያት በስንት ነው የሚገባው? †††
      ሕዝበ ክርስቲያኑን ብዙ ጊዜ ግራ የሚያጋባው ነገር አንዱ የጾመ ነቢያት መግቢያ እና  መውጫ መች ይኾን የሚለው ጥያቄ ነው። እንደእውነቱ ከኾነ በማስተዋል ለሚጓዝ የቤተክርስቲያን ልጅ ግራ የሚያጋባ እንዳይደለ እሙን  ነው።
ጾመ ነቢያት ወይም የገና ጾም የሚገባበት እለት የተለያየ ነው።ይኽም ማለት አንድ ጊዜ ኅዳር 15 ሲገባ አንድ ጊዜ ደግሞ ኅዳር 16 ይገባል። ይኽ የኾነበትም ምክንያት በጳጉሜን 5 እለት ወይንም በእለተ ምርያ ምክንያት ነው። ልደተ እግዚእ/የጌታችን ልደት/ ወይም የገና በዓል እለተ ምርያ የምንላት ጳጉሜን 5 እለት በዋለችበት እለት ኹልጊዜም ቢኾን ይውላል። ስለዚህም ጵጉሜን መጠኗ 5 እለታት ብቻ በኾነባቸው ዓመታት ማለትም በዘመነ ማቴዎስ፣ ማርቆስ እና ሉቃስ ላይ፣ ከነዚህ አዝማናት ቀጥለው በሚመጡት ዓመታት ማለትም በዘመነ ማርቆስ፣ ሉቃስ እና ዮሐንስ ላይ ጾመ ነቢያት የሚገባው በኅዳር 16 ይኾንና  ታኅሳስ 29 እለት ይፈሰካል ማለት ነው።
      በዘመነ ዮሐንስ ግን ጵጉሜን 6 እለታት ስለምትኾን የጾመ ነቢያትን እና የገናን በዓል እለታት አንድ አንድ እለት ወደኋላ ትስበዋለች። ይኽም ማለት በዘመነ ማቴዎስ ጾመ ነቢያት ኅዳር 15 ገብቶ ታኅሳስ 28 ይፈሰካል ማለት ነው። ቤተክርስቲያናችን የገናን ጾም እንዲህ አድርጋ ታስተምራለችና ልብ ብለን በማስተዋል ልንጓዝ ያስፈልጋል። የቅዱሳን አምላክ ማስተዋሉን አድሎን ጾሙን በረከት ረድኤት የምናገኝበት፣ ኃይለ አጋንንትን የምናደክመበት፣ መንፈስ ቅዱስ የሚቀርብበት፣ ምስጢር የሚገለጥበት እንዲኾንልን ይርዳን። አሜን።
©ዘዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
ር 14 2010 .
ጎንደር/ኢትዮጵያ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ