ማክሰኞ 14 ኖቬምበር 2017

የቅዱስ ቆጵረስ እና የቅዱስ ፔታርፔሞቲስ ተጋድሎ (ክፍል አምስት)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

(ምንጭ፦The paradise of the holly fathers by St. Athanasius, volume 1
ትርጉም፦ ዲያቆን መልአኩ ይፍሩ ዘውሉደ ብርሃን)

ውድ የተዋሕዶ ልጆች እንደምን አላችሁ። በተወጋው ጎኑ በፈሰሰው ንጹሕ ደሙ ከመርገመ አዳም ነጻ ያደረገን፣ ተወዳጅ እናቱን ከመስቀል ሥር በቅዱሱ ደቀ መዝሙሩ በአቡ ቀለምሲስ ቅዱስ ዮሐንስ አማካይነት ወላዲተ አምላክን እናታችን አድርጎ የሰጠን የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን። የቅዱስ ቆጵረስን እና የቅዱስ ፔታርፔሞቲስን ተጋድሎ ካቆምንበት እንቀጥላለን። የቅዱሳኑ ኹሉ ጸሎት እና የእግዚአብሔር ቸርነት የእናት ዓለም አማላጅነት አይለየን። አሜን።

            ይህ ቅዱስ ሰው ቀጵረስ ስለ ቅዱስ ፔታርፔሞቲስ እሊህን ነገሮ ች እየነገረን ሳለ እንዲህ አለን እኔም ወጣት ሳለሁ የዚያን ድንቅ ዛፍ ፍሬ በደቀ መዛሙርቱ (በቅዱስ ፔታርፔሞቲስ ደቀ መዛሙርት) እጅ ተመልክቻለሁ፤ ሳምዃቸውና በእኔ ዘንድ ከቀረው መዓዛም የተነሳ አደነቅሁ። ዛፉም ከዚያ በኋላ ለብዙዎች (የቅዱስ ፔታርፔሞቲስ ቃል፣ ንግግር እውነት መኾኑን) ለማሳየት ለምስክርነት ለብዙ ዘመናት በደቀ መዛሙርቱ ዘንድ ቆይቷል። ከመጠን በላይ ታላቅ ነበርና እንዲህ ያለ ድንቅ ባሕርይ ነበረው፤ ማንኛውም የታመመ ሰው ባሸተተው ጊዜ ወዲያውኑ ከደዌው ይፈወስ ነበር።

ወደ በረሓው ለመጀመሪያ ጊዜ እንደኼደ፣ ምንም ምን ዓይነት ምግብ ልአምስት ሳምንታት ሳይቀምስ በቆየ ጊዜ በዚያ በረሓ አንድ ምግብ እና ውሃ የያዘ ሰው አግኝቶ ከዚያም ለምኖ በልቶ፣ ጠጥቶ ከርሱ ተለይቶ እንደኼደ ይናገሩ ነበር። በሌላም ጊዜ ክፉው (ድያብሎስ) ከፈርኦን (ከግብጽ ንጉሥ) ሀብት ኹሉ የሚበልጥ(በመጠን) ጥቂት ወርቅን አሳየው፤ (ፔታርፔሞቲስ ግን)ያንን ወርቅ ያሳየውን መለሰና እንዲህ አለው፥አን እና  የአንተ ወርቅም ኹሉ ወደ ሲኦል ግቡ         
   
እነርሱም እንደተናገሩት እሊህ እና ይኽን የመሰሉ ሌሎችም ድንቅ ነገሮች በአባ ፔታርፔሞቲስ ተደርገዋል። “(ቢጻፍ ) ዓለም እንኳን ሊበቃው (ሊይዘው) የማይቻለውን ሊሎችንም ብዙ ነገሮች በእኛ ፊት ተናገሩ። እኒህ አበው እንደነገሩንም ”ፔታርፔሞቲስ እንዲህ አለን ታናሽ የኾነው ሰዎች ትንሽ የኾኑትን ነገሮች በራሳችንም ላይ ጭምር ማድረግ የምንችለውን ማለትም፣ ሽባውን እና ዐይነ ሥውሩን ማዳናችንን ሐኪሞችም እንኳን በጥበባቸው የሚያደርጉት ነውና ታዲያ በምን ነገር ታላቅነት አለን?(መታበይ እንደማይገባ ሲናገር ነው።) “ ታላቁ ቆጵረስም እኒህን እየነገረን ለእኛ እያካፈለን ሳለ ከእኛ መኻከል አንደኛው (ወንድም) አንቀላፋ፤ ይኽም ሰው ያ ቅዱስ ሰው የሚነግረንን ነገር ኹሉ አላመነም ነበር። አንቀላፍቶም ሳለ ድንቅ የኾነ መጽሐፍን ተመለከተ፤ መጽሐፉም በዚህ አረጋዊ(በቆጵረስ) ጉልበት ላይ ነበር። (መላው የመጽሐፉም ክፍል) በወርቅ ተጽፎ ነበር። ከዚያም በላይ አንድ አረጋዊ ቆሞ እጅግ በሚገስጽ ኹኔታ “እንዲህ በእንቅልፍ የወደቅኸው፣ ሲባል የነገረውን ኹሉ በደንብ አልሰማህምን?” በማለት ተናገረው።ያም ሰው በፍጥነት ከእንቅልፉ ተነሳና የተመለከተውን ኹሉ በግሪክኛ ቋንቋ ነገረን።

ይኽ ወንድማችን ይኽን ነገር እየነግረን ሳለ፣ አንድ የመንደሩ ሰው በአሽዋ የተሞላ (ከረጢት) በትክሻው ተሸክሞ (ከዚያ ወንድም ፊት ለፊት) ቁሞ ነበር። እኛም ለምን ከዚያ እንደቆመ፣ ይህን የርሱን ትረካ እስኪያልቅ ለምን እንደጠበቀ፣ ምን እንደሚሻ እና አሽዋውንም ለምን እንደተሸከመው እንዲነግረን ለመነው። ከዚያም አባ ቆጵረስ መለሰና እንዲህ አለን “ ልጆቼ፣ ይኽ ራሳችንን ለማስታበይ አይምሰላችሁ፤ ዳሩ ግን የአበውን ገድል በእናንተ ፊት እናውጅ ዘንድ የተገባ እለኾነ ነው(ይኽን የምነግራችሁ)። ስለዚህም በልቡናችን (በአእምሯችን) ምስጋናን (ከንቱ ውዳሴን) ተቀብለን (ሰማያዊ) ሽልማታችንን እንዳናጣ። በዚህ ፈንታ ግን፣ ወደ እኛ (እኛን ለማየት) ከሩቅ ቦታ ስለመጣችሁ ስለናንተ ደስታ እና ከቃልኪዳንነቱም የተነሳ ከዚህ ጥቅም(ረብ) አምከለክላችሁም(እንነግራችኋለን)። እግዚአብሔር በእጆቻችን ኹሉ ያደረገውን በእናንተ በወንድሞቻችን ፊት እንገልጥላችኋለን። በአንድ ወቅት በእኛ አካባቢ(በአቅራቢያው ያለው መንደር) መሬት ምንም አያበቅልም ነበር። በዘሩ ውስጥ (እህል የሚያበላሽ) ነቀዝ ፈርቶበት ነበርነ፣ መኸራቸውን ያበላሽባቸው ስለነበር የመንደሩ ነዋሪዎች የዘሩትን ያህል እንኳን ለማግኘት እጅግ ብዙ ድካም ይደክሙ ነበር። ከነዚህም አባ ወራዎች መኻከል በእኛ (ተምረው) የተለወጡ ነበሩና መጥተው ስለመኸራቸው እንድንጸልይላቸው ጠየቁን። እኛም ንተ በእግዚአብሔር ላይ እምነት ካላችሁ፣ ይኽ የበረሓ አሸዋ እንኳን ፍሬን ይሰጣችኋል በማለት ነገርናቸው። ከዚያም ያለምንም መጠራጠር፣ ከእግራችን በታች የተረገጥነውን አሽዋ እያነሱ በደረታቸው ከሞሉ በኋላ እንድንጸልይላቸው ጠየቁን። እኛም እንደእምነታቸው እንዲኾንላቸው ለጸለይንላቸው በኋላ ኼደው ከስንዴው ጋር ቀላቅለው በእርሻው ላይ ዘሩት፤ ወዲያውም በግብጽ ሌሎች የእርሻ  መሬቶች ኹሉ እንኳን ከሚገኘው የሚበልጥ እጅግ የበዛ ፍሬን (ምርትን) ሰጣቸው። ይህም ለነርሱ ልማድ ኹኖ በየዓመቱ አሽዋ እያመጡ (እንዲባረክላቸው) ያደርጋሉ። ”

ዳግመኛም ብዙ ወንድሞች በዚያ ተሰብስበው ሳለ ጌታችን ለእኛ ያዘጋጀልንን አንድ ድንቅ ነገር  ነገርን። እንዲህም አለ” በአንድ ወቅት. . .

(ቅዱስ ቆጵረስ ምን ሊነግራቸው ይኾን ደግሞ? ከዚህስ በኋላ ምን ይከሰት ይኾን? ከነቅዱስ አትናቴዎስ ጋር በመኾን ቀጣዩን የቅዱሳኑን ገድል ክፍል በቀጣዩ ጦማር እንመለከታለን።ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።) ወስብሐት ለእግዚአብሔር። ይቆየን።
                                                                                    ©ዘዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
ሕዳር 2/ 2010 ዓ.
                                                                                    ጎንደር/ ኢትዮጵያ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ