በባለፈው የባሕረ ሐሳብ ትምህርት ቆይታችን ከመጥቅዕ አንስተን የቀረውን የባሕረ ሐሳብ ክፍል
ተመልክተን ነበር። እንደአምላከ ቅዱሳን ፍቃድ እንቀጥላለን፤ የሥሉስ ቅዱስ ቸርነት አይለየን።
† ንኩራን አቅማራት †
† እሊህም ንኩራን ያልኋቸው
ከዚህ በፊት በተማማርንበት መንገድ የማናሰላቸው ዓመታት ስላሉ የእሊያን ዓመታት በዓላት እና አጽዋማት ለማውጣት የምንጠቀምባቸውን
የቀመር መንገዶች ነመጠቆም ነው። ለምሳሌ በ2005 ዓም ላይ ወንበር ከዜሮ በታች (negative) ይሆናል። ይህ ማለት በዚህ ዓመት
ላይ አበቅቴ እንደአዲስ የሚጀምርበት ዓመት ነው ማለት ነው። በ2006 ዓም ደግሞ ወንበር አልቦ(ዜሮ) ስለሚሆን በዚህ ዓመት ያለውን
አበቅቴ እና መጥቅዕ እስካሁን በተመለከትነው መንገድ መፈለግ አንችልም። እነዚህን የምንፈልግበት መንገድ የሚከተለው ነው።
† ወንበር ከዜሮ በታች
በሚመጣብን ጊዜ፣ ሁልጌም እንዲህ ያለ ዚገጥመን፣ በዚያ ዓመት አበቅቴው ዑደቱን የሚጨርስበት የመጨረሻው ዓመት ነው ማለት ነው።
ለአበቅቴ መጨረሻው ደግሞ 18 ነው። ስለዚህም በዚህ ዓመት ላይ አበቅቴውን 18 በማድረግ ማስላት እንችላለን።
o
የ2005 ዓምን በዓላት እና
አጽዋማት በዚህ መንገድ አበቅቴውን ፈልገህ፣ ከ30 ላይ
አበቅቴውን በመቀነስ መጥቅዑን ካገኘህ በኋላ በዓላት እና አጽዋማቱን አውጣ።
† በሌላ ጊዜ ደግሞ ወንበር አልቦ ወይም ባዶ ሊመጣ
ይችላል። በዚህ ዓመት ላይ ደግሞ በዓላትን ለማውጣት ብንሻ፣ ወንበር አልቦ ስለሆነብን አበቅቴና መጥቅዕን ማስላት አንችልም። እንዲህ
ያለ በገጠመን ጊዜ መስከረም 30 የዋለበት እለት ተውሳክ መባጃ ሐመር ይሆናል። መጥቅዑም 30 ተደርጎ ይወሰዳል። ከዚህ በኋላ በዓላትን
እና አጽዋማትን መውጣት እንችላለን።
o
የ2006 ዓምን በዓላት እና
አጽዋማት በዚህ መንገድ መጥቅዑን እና መባጃ ሐመሩን ፈልገህ በዓላት እና አጽዋማቱን ፈልግ።
† ስያሜ አውራኅ ወእለታት †
†
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ወራቷንም ሆነ እለታቷን ስትሰይም መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ እንጂ እንደሌላው
ዓለም የሚመለክ ጣዖትን ወይም አንድ ምድራዊ ንጉስን መሠረት አድርጋ አይደለም። ይህ ግልጽ ይሆንልን ዘንድ በመጠኑ እንመልከተው።
†
የእለታት ስያሜ በቤተክርስቲያናችን እና በምዕራቡ ዓለም †
†
የምእራቡ ዓለም እለታትን የሰየመው የሚያመልካቸውን ጣዖታት መሠረት በማድረግ ነው።ለዚህም እንደምሳሌ የሚከተለውን እንይ
o
Monday ማለት የጨረቃ ቀን ለማለት ነው። ይኸውም ጨረቃን
ስለሚያመልኩ ከዚያ መታሰቢ ያ ለማድረግ ነው።
o Sunday ማለት የፀሐይ ቀን ለማለት ነው። ይኸውም ፀሐይን ያመልኩ ስለነበር የሰየሙለት መታሰቢያ ነው።
†
የእኛ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ግን እለታትን ስትሰይም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ይዛ ነው። ለዚህም
እያንዳንዱን እለት ለምን እንደተሰየመ እና ምን ማለት እንደሆነ እንደሚከተለው
እንናገራለን።
o እሑድ ማለት አሐደ አንድ አደረገ ካለው የግእዝ ቃል
የወጣ ሲሆን ትርጉሙም አንደኛ ማለት ነው። ይኸውም ለፍጥረታት መፈጠር የመጀመሪያው እለት ስለሆነ ነው። በዚህም እለት ስምንት ፍጥረታት
ተፈጥረዋል።
o ሰኑይ ማለት ሰነየ ሁለት አደረገ ካለቅ የግእዝ ቃል የተገኘ
ነው። ለፍጥረታት መፈጠር ሁለተኛው እለት በመሆኑ ሁለተኛ ለማለት ሰኑይ ተብሏል። በዚህም እለት ውሃ ለሦስት ተከፍሏል። የተፈጠረው
ግን አንድ ፍጥረት ብቻ ነው። እርሱም ጠፈር ነው።
o ሠሉስ ማለት በአማርኛው ማግሰኞ በመባል የሚታወቀው ሲሆን ሠለሰ ሦስት አደረገ ካለው
የግእዝ ቃል ተገኝቶ ሦስተኛ የሚል ትርጉም ያለው ቃል ነው። ፍጥረታት የተፈጠሩበት ሦስተኛው እለት ስለሆነው። በዚህም እለት ሦስት
ፍጥረታት ተፈጥረዋል።
o ረቡዕ ማለት ረብዐ አራት አደረገ ካለው የግእዝ ቃል የተገኘ
ነው። ትርጉሙም አራተኛ ማለት ነው። ይኸውም ለፍጥረት መፈጠር አራተኛ የሆነ እለት ማለት ነው። በዚህም እለት ሥኦስት የብርሃን
ፍጥረታት ተፈጥረዋል።
o ሐሙስ ማለት ሐመሰ አምስት አደረገ ከሚል የግእዝ ቃል
የተገኘ ሲሆን አምስተኛ ማለት ነው።ይኸውም ለፍጥረታት መፈጠር አምስተኛ እለት ማለት ነው። በዚህም ሦስት ፍጥረታት ተፈጥረዋል።
o ዓርብ ማለት ዓርበ ተካተተ ካለው ቃል የተገኘ ሲሆን መካተቻ
ማለት ነው። ፍጥረታት ተፈጥረው የተካተቱበት እለት ስለሆነ ማለትም ፍጥረት ተፈጥረው የተጨረሱት በዚህ እለት ነው።
o ቀዳሚት ማለት የመጀመሪያዋ ማለት ሲሆን የመጀመሪያዋ መባሏም
ለሰንበትነት ነው። ይህም ማለት እግዚአብሔር ፍጥረታትን ከፈጠረ በኋላ ያረፈባት እለት ናትና ነው። ስለዚህም የመጀመሪያይቱ ሰንበት
ለማለት ቀዳሚት አላት። ሁለተኛይቱ ሰንበት እሑድ ናትና።
† የአውራኅን ስያሜ እና ሌሎችንም ከዚህ የሰፉትን
ነገሮች ከሚከተሉት እና ከሌሎችም መጻሕፍት በማንበብ ታሰፉት ዘንድ
እጠቁማለሁ። የቅዱሳኑ ምልጃ እና ቃልኪዳን፣ የእማምላክ አማላጅነት የእግዚአብሔር ቸርነት አይለየን።
† የሚነበቡ መጻሕፍት
o የኢትዮጵያ ታላቁ ሀብት ባሕረ ሐሳብ
o ባሕረ ሐሳብ
o የዘመን አቆጣጠር እና ሌሎችም።
ተፈጸመ ነገረ ባሕረ ሐሳብ በሰላመ እግዚአብሔር
አሜን።
©ዘዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
ጥቅምት 12– 2010 ዓ.ም
ጎንደር/ኢትዮጵያ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ