††† ባሕረ ሐሳብ-(ክፍል ሁለት)†††
የተዋሕዶ ልጆች በባለፈው ቆይታችን የባሕረ ሐሳብን ምንነት እና የት መጣ እንዲሁም
ማን ደረሰው የሚሉትን ተመልክተናል። ለዛሬ ደግሞ ካቆምንበት በመቀጠል እንማማራለን። የቅዱስ ድሜጥሮስ አምላክ ምስጢሩን ይግለጥልን።
† አዝማናት †
†
አዝማናት የምንላቸው ሦስት ናቸው።
እሊህም ዓመተ ፍዳ/ኩነኔ/፣ ዓመተ ምሕረት እና ዓመተ ዓለም ናቸው።
o
ዓመተ ፍዳ፥ የምንለው ከአዳም በደል
እስከ ክርስቶስ በሥጋዌ መገለጥ ድረስ ያለውን የመከራ እና የጭንቅ ዘመን ነው። ይኸውም በቤተክርስቲያን ታሪክ ምሁራን በአራት ይከፈላል።
የመጀመሪያው ከአዳም እስከ ሙሴ ያለው ዘመነ አበው ይባላል፡ ደጋጉ ቅዱሳን አበው/the righteous holly patriarchs/ የተነሱበት ዘመን ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ዘመነ መሳፍንት የሚባለው ነው፡ ይኸውም ከሙሴ እስከ
ሳዖል ያለው ዘመን ነው። ሦስተኛው ደግሞ ከሳዖልም ጀምሮ ዘመን ዘመነ ነገሥት ይባላል። እነ ቅዱስ ዳዊትን የመሳሰሉ ነገሥታት የተነሱበት
ዘመን ነው። አራተኛው ዘመን ደግሞ እስከ ቅዱስ ዮሐንስ ዘመን ያለው ዘመን ዘመነ ካህናት ይባላል። ጌታችንና ፈጣሪያችን ንጉሣችን
ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደውም በዚህኛው ዘመን ነው።
o
ዓመተ ምሕረት፥ የምንለው ደግሞ ከተወዳጁ
ቤዛችን እና ሕይወታችን በሥጋዌ መገለጥ አንስቶ እስከ ዓለም ፍጻሜ ያለው ዘመን ነው። ይህም በውስጡ በቤተክርስቲያን ታሪክ ምሁራን
የተከፋፈሉ አዝማናት ያሉ ሲሆን ከነዚህም መኻከል ዘመነ ሐዋርያት፣ ዘመነ ተላውያነ ሐዋርያት፣ ዘመነ ሊቃውንት፣ ዘመነ ሰማእታት
የሚባሉት ይገኙበታል።
o
ዓመተ ዓለም፥የምንለው ደግሞ የዓለምን
መላ እድሜ የሚናገር ዘመን ነው። ይኸውም ከላይ የተመለከትናቸው ሁለት አዝማናት ሲጨመሩ የሚገኘው ውጤት ነው።
ዓመተ ፍዳ + ዓመተ ምሕረት= ዓመተ ዓለም
† መስፈርታት †
†
በዓለሙ የጊዜ መለኪያ ተብለው ሴኮንድ፣
ደቂቃ፣ ሰዓት እየተባለ እንደሚቆጠረው ሁሉ ቤተ ክርስቲያናችንም የራስዋ የሆነ ዘመናትን እስከ ቅጽበት ድረስ እንኳን የምትሰፍርባቸው
መስፈርታት አሏት። እሊህም እለት፣ ኬክሮስ፣ ካልኢት፣ ሣልሲት፣ ራብኢት፣ ኃምሲ እና ሣድሲት የሚባሉት ናቸው።
t
በአጠቃላይ ስድስት መስፈርታት ያሉ
ሲሆን እሊህም ያላቸው ግንኙነት እንደሚከተለው ነው።
ኬክሮስ- 60 ኬክሮስ=1 እለት ነው
ካልኢት- 60 ካልዒት=1 ኬክሮስ ነው
ሣልሲት- 60 ሣልሲት=1 ካልዒት ነው
ራብዒት- 60 ራብዒት=1 ሥልሲት ነው
ኃምሲት- 60 ኃምሲት=1 ራብዒት ነው
ሳድሲት- 60 ሳድሲት=1 ኃምሲት ነው /ጳጉሜን ከተሰኘው
ጦማር/
†
እኒህም መስፈርታት አዝማናቱን በትክክል
ለመለካት የሚያገለግሉን ናቸው።
† አዕዋዳት †
†
ዐውድ ማለት ዙሪያ፣ ክበብ፣ ከበር
እስከ በር ካመት እስካመት ያለ፣ ለተወሰነ ክበብ ሁሉ የሚነገር ነው።በብዙ ቁጥር ሲነገር አዕዋዳት ይባላል።/ኪ.ወ.ክ/
†
ዓመተ ዓለም መቁጠሪያ መስፈሪያ የሚሆኑ
ሰባት አዕዋዳት አሉ። እነርሱም ዐውደ እለት፣ ዐውደ ወርኅ፣ ዐውደ ዓመት፣ ዐውደ አበቅቴ፣ ዐውደ ፀሐይ፣ ዐውደ ማኅተም እና ዐውደ
ቀመር ናቸው።
1/ዐውደ እለት፥ ከእለተ እሑድ ጀምሮ እስከ ቀዳሚት ባሉት ሰባት እለታት እየተመላለሱ ዐውደ ወርኅን ያስገኛሉ።
2/ዐውደ ወርኅ፥ በፀሐይ ዘወትር በ30 እለት በመመላለስ ዐውደ ዓመትን ያስገኛል። በጨረቃ ደግሞ አንድ ግዜ
29 አንድ ግዜ ደግሞ 30 እለት ይሆናል። ይኸውም ፦ 1ኛ/ መስከረም 2ኛ/ ጥቅምት 3ኛ/ ኅዳር 4ኛ/ ታኅሳስ 5ኛ/ ጥር 6ኛ/
የካቲት 7ኛ/ መጋቢት 8ኛ/ ሚያዝያ 9ኛ/ ግንቦት 10ኛ/ ሰኔ 11ኛ/ ሐምሌ 12ኛ ነሐሴ 13ኛ ጳጉሜን ናቸው።
3/ዐውደ ዓመት፥ ይኽም በፀሐይ 365 እለት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልኢት ሲሆን በጨረቃ ደግሞ 354 እለት
ከ22 ኬክሮስ ነው። ከፀሐይ ወሮች አጽፈ ወርኅ ከጨረቃ ወሮች ደግሞ ሕጸጽ ይገኛሉ።
ዐውደ ጳጉሜን በማለት
የሚጠራ በየአራት አመቱ የሚዘዋወረውን የጳጉሜን ስድስት መሆን የሚያሳይ ዑደር ቢኖርም አበይት የምንላቸው ግን ከላይ የተናገርናቸው
ናቸው።
4/ዐውደ አበቅቴ፥ ይኸውም በ19 ዓመት አንድ ጊዜ እየዞረ የሚከሰት ሲሆን ሁነቱም ፀሐይ እና ጨረቃ ልክ እንደተፈጠሩ
ሁነው በአንድ መስኮት ተራክቦ የሚያደርጉበት ነው። ይህም ማለት በ19 ዓመት አንድ ጊዜ ዐውደ ዓመታቸውን እኩል መስከረም 1 ይጀምራሉ
ማለት ነው።
5/ዐውደ ፀሐይ፥ ይህ ደግሞ በየ28 ዓመት አንዴ እየዞረ የሚመጣ ነው። በዚህም ዐውድ፣ ወንጌላዊ እና እለት
ይገናኛሉ። ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ሲሆን እለቱ ደግሞ ረቡዕ ነው።
6/ዐውደ ማኅተም፥ ማኅተም ማለት አኅተመ ዘጋ፣ ፈጸመ ካለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን በዚህም አገባብ መጨረሻ
የሚል ትርጉም ይሰጠናል።ይህ ዐውድ በ76 ዓመት አንድ ጊዜ እየዞረ የሚመጣ ነው። በዚህም ዐውድ፣ አበቅቴ እና ወንጌላዊ ይገናኛሉ።
አበቅቴው 18 ሲሆን የአበቅቴዎች ሁሉ ፍጻሜ እንደሆነ፣ ወንጌላዊውም ቅዱስ ዮሐንስ ለወንጌላውያን መጨረሻ ነው።
7/ዐውደ ቀመር/አቢይ
ቀመር/፥ ይህ ዐውደ ደግሞ በየ532 ዓመት አንድ ጊዜ የሚዖድ ሲሆን በዚህ ዐውድ ደግሞ እለት፣
አበቅቴ እና ወንጌላዊ ይገናኙበታል። እለቱ ሰኑይ፣ አበቅቴው 18 እና ወንጌላዊው ደግሞ ዮሐንስ ነው። አውዱ በዘመነ ማቴዎስ እለተ
ሠሉስ ላይ አንድ ብሎ ይጀምር እና ከ532 ዓመታት በኋላ እለተ ሰኑይ ላይ በዘመነ ዮሐንስ ይፈጽማል።
† ዓመተ ወንጌላውያን †
†
ይህ ቀመር ዓመተ ዓለምን በዓውደ ጳጉሜን በመግደፍ የሚገኘውን
ቀሪ በመውሰድ የሚገኝ ነው። ይኸውም ማለት ቀሪው፦
1 ቢሆን ዓመቱ ዓመተ ማቴዎስ ይሆናል
2 ቢሆን ዓመቱ ዓመተ ማርቆስ ይሆናል
3 ቢሆን ዓመቱ ዓመተ ሉቃስ ይሆናል
0 ቢሆን/ያለቀሪ ቢካፈል/ ዓመቱ ዓመተ ዮሐንስ ይሆናል ማለት ነው። ከዚህ በኋላ ግን ለአራት ስትካፈል የተገኘችው ድርሻ
መጠነ ራብዕት ትባላለች። ትርጉሙም ለአራት ተካፍሎ የተገኘ ድርሻ እንደማለት
ነው። ይህንም እለተ ዮሐንስን ስንፈልግ የምንጠቀምበት ነው።
† እለተ ዮሐንስ†
†
ይህ ቀመር ደግሞ መስከረም 1 እለት የሚውልበትን እለት የምናውቅበት ቀመር ነው። ይህንም ለማግኘት መጠነ ራብእትን ከዓመተ
ዓለም ጋር በጨመር በ7 መግደፍ ከዚያም የሚገኘውን ቀሪ መውሰድ ነው። ይኸውም ተካፍሎ የሚገኘው ቀሪ፦
1 ቢሆን እለቱ ሠሉስ ይሆናል
2 ቢሆን እለቱ ረቡዕ ይሆናል
3 ቢሆን እለቱ ሐሙስ ይሆናል
4 ቢሆን እለቱ አርብ ይሆናል
5 ቢሆን እለቱ ቀዳሚት ይሆናል
6 ቢሆን እለቱ እሐድ ይሆናል
0 ቢሆን/ያለቀሪ ቢካፈል/ እለቱ ሰኑይ ይሆናል ማለት ነው።
†
እለተ ዮሐንስ የምጀምረው ከሠሉስ ነው። ምክንያቱም ጥንታትን ስንነጋገር ጥንተ እለት ሠሉስ መሆኑን ተናግረናል። መስከረም
1 እለት እለተ ዮሐንስ መባሉም ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በብሉይ ኪዳን እና በሐዲስ ኪዳን መሸጋገሪያ ላይ የተገኘ ነቢይ ወሰማዕት
ነው፤ መስከረም 1 እለትም የአዲስዘመን መቀበያ የዘመን መሸጋገሪያ ስለሆነ እለት ዮሐንስ ይባላል።
ይቆየን።
ምንጭ፦ ባሕረ ሐሳብ በአለቃ ያሬድ ፈንታ
-የኢትዮጵያ ታላቁ ሀብት ባሕረ ሐሳብ
ይቀጥላል።
©ዘዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
መስከረም 22 – 2010 ዓ.ም
ጎንደር/ኢትዮጵያ
ይቀጥላል።
©ዘዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
መስከረም 22 – 2010 ዓ.ም
ጎንደር/ኢትዮጵያ
እግዚአብሔር ይስጥልን። ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
ምላሽ ይስጡሰርዝ