ዓርብ 27 ኦክቶበር 2017

††† ባሕረ ሐሳብ (አራት) †††

      በባለፈው የባሕረ ሐሳብ ትምህርት ቆይታችን ወንበርን፣ አበቅቴን እና መጥቅዕን ተመልክተን ነበር። ባለፈው ክፍል ካቆምንበት ከመጥቅዕ የቀረውን እና ሌሎቹንም እንደአምላከ ቅዱሳን ፍቃድ እንቀጥላለን፤ የሥሉስ ቅዱስ ቸርነት አይለየን።
መጥቅዕን በባለፈው ክፍል በተማማርናቸው መንገዶች ካገኘን በኋላ በዓላትን እና አጽዋማትን ለማግኘት ቀድመን መጥቅዕ የሚውልበትን እለት ማወቅ ይጠበቅብናል። ለዚህም የሚከተለውን አዋጅ ልብ ይሏል።
አዋጅ
    1/መጥቅዕ ከ14 ቢበዛ በመስከረም ንዛ፣ መጥቅዕ ከ14 ቢያንስ ከጥቅምት ዳብስ
ይህም ማለት መጥቅዕን ስንፈልግ ያገኘነው ውጤት ከ14 ቢበልጥ በዓለ መጥቅዕ በመስከረም ይውላል። መጥቅዕ ከ14 ቢያንስ ደግሞ በዓለ መጥቅዕ በጥቅምት ይውላል ማለት ነው። ይህም በቀጣይ ለምንመለከተው ቀመር ወሳኝ ነው።
     መባጃ ሐመር
      መባጃ ሐመር፥ ቃልነቱ ግእዝ ወይም ሌላ አይደለም። ፍርንዱስ ነው። ይህም ማለት የአማርኛ እና የግእዝ ቃላት ጥምረት ውጤት ነው ማለት ነው። መባጃ 'ባጀ፤ ከረመ' ካለው የአማርኛ ቃል የተገኘ ሲሆን ማክረሚያ ማለት ነው። 'ሐመር' ማለት ደግሞ በግእዝ መርከብ ማለት ነው። ስለዚህም በአጠቃላይ ትርጉሙ ማክረሚያ መርከብ ማለት ነው። ስሌቱም እንደሚከተለው ነው።
      ይህም ቀመር ነነዌን ጨምሮ ሌሎቹንም በዓላት እና አጽዋማት ለማግኘት የምንጠቀምበት ቀመር ነው። ይህም የሚሰላው መጥቅዕን በዓለ መጥቅዕ ከዋለበት እለት ተውሳክ ጋር በመደመር የምገኘው ውጤት ከ30 ቢበልጥ በ30 በመግደፍ የሚገኝ ነው።
                        መጥቅዕ + በዓለ መጥቅዕ የዋለበት እለት ተውሳክ = መባጃ ሐመር
     ተውሳክ
ተውሳክ ወሰከ፣ ጨመረ ካለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ጭማሪ ማለት ነው። ይህም ሁለት ዓይነት ሲሆን አንደኛው የእለታት ተውሳክ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ የበዓላት እና የአጽዋማት ተውሳክ ነው። እሊህን አንድ በአንድ በመጠኑ እንመለከታቸዋለን።


የእለታት ተውሳክ
      የእለታት ተውሳክ የምንላቸው ከቀዳሚት አንስቶ እስከ ዓርብ ያሉትን እለታት ተውሳካት ነው። ይኸውም ከቀዳሚት ይጀምራል። ይህም የሚገኘው በዓለ መጥቅዕ ከዋለበት እለት ሳኒታ /ማግስት/ እስከ ነነዌ ያለውን በመቁጠር በ30 በመግደፍ ነው።
       በዓለ መጥቅዕ በቀዳሚት ቢውል፣ ከዚህ እስከ ነነዌ ያለውን ቢቆጥሩት 128 ይሆናል፤ እሑድ ቢውል፣ ከዚህ እስከ ነነዌ ያለው 127 ይሆናል፤ ሰኑይ ቢውል 126፤ ሠሉስ ቢውል 125፤ ረቡዕ ቢውል 124፤ ሐሙስ ቢውል ደግሞ 123፤ ዓርብ ቢውል ደግሞ 122 ይሆናል። እሊህንም በ30 ቢገድፏቸው እያንዳንዳቸው እንደሚከተለው ይሆናሉ።
እለት         ተውሳክ
ቀዳሚት       8
እሑድ          7
ሰኑይ            9
ሠሉስ           5
ረቡዕ            4
ሐሙስ          3
ዓርብ            2  ይሆናሉ።
ለምሳሌ
የ2010 ዓምን መባጃ ሐመር እንፈልግ።
የ2010 መጥቅዕ 16 ነው። መስከረም የባተው ሰኑይ እለት ነው። ከመስከረም መባቻ እለት ሰኑይ እስከ ሳምንቱ ሰኑይ 8፣ ከሳምንቱ ሰኑይ እስከ ቀጣዩ ሳምንት ሰኑይ 15፣ በማግስቱ ሠሉስ 16 ይሆናል። መስከረም 16 የዋለው በዓለ መጥቅዕ እለቱ ሠሉስ ነው ማለት ነው። ስለዚህም በዓለ መጥቅዕ የዋለው ሠሉስ ስለሆነ ተውሳኩ 5 ይሆናል።
መጥቅዕ + በዓለ መጥቅዕ የዋለበት እለት ተውሣክ = መባጃ ሐመር
ከዚያም የተገኘውን ውጤት በ30 በመግደፍ ቀሪውን መውሰድ።
16 + 5 = 21 በ2010 ዓም 21 መባጃ ሐመር ይሆናል።
መጥቅዕ + በዓለ መጥቅዕ የዋለበት እለት ተውሣክ፣ ከዚህ የተገኘውም ከሠላሳ ቢተርፍ በ30 ገድፈህ ቀሪውን ውሰድ። የበዓለ መጥቅዕም ተውሳክ፣ ሠሉስ እለት ስለሆነ ተውሳኩ 5 ነው።
16 + 5= 21 ይህም ከ30 ያነሰ ስለሆነ እንዳለው እንወስደዋለን።
የበዓለት እና የአጽዋማት ተውሳክ
      በዓላት እና አጽዋማት የሚውሉበትን እለት ለማወቅ ከበዓላቱ እና ከአጽዋማቱ ተውሳክ ጋር መባጃ ሐመርን በመደመር ከ30 ቢበልጥ በ30 ግደፍ። የቀረውንም ውሰድ። ሌሎቹ በዓላት እና አጽዋማት በተውሳክ ሲወጡ ነነዌ ግን በደረቅ መባጃ ሐመር ትወጣለች። ምክንያቱም እርሷ ምንም ተውሳክ የላትም። ተውሳካቱም የሚከተሉት ናቸው።
ነነዌ                                0
ዐቢይ ጾም                     14
ደብረ ዘይት                   11
ሆሳዕና                           2
ስቅለት                           7
ትንሣኤ                          9
ርክበ ካህናት                   3
ዕርገት                           18
ጰራቅሊጦስ                    28
ጾመ ሐዋርያት                29
ጾመ ድኅነት                    1           ይሆናሉ።
      የበዓላት እና የአጽዋማትን ተውሳክ ለማግኘት ነነዌ ከዋለችበት እለት ሳኒታ/ማግስት/ እስከ በዓሉ ወይም ጾሙ ድረስ በመቁተር የተገኘውን በ30 በመግደፍ የሚገኘው ቀሪ የበዓሉ ወይም የጾሙ ተውሳክ ይሆናል።
አዋጅ፤
    1/ በዓለ መጥቅዕ በመስከረም ከዋለ ነነዌ በጥር ትውላለች።
    2/ በዓለ መጥቅዕ በጥቅምት ከዋለ ነነዌ በየካቲት ትውላለች።
    3/ በዓለ መጥቅዕ በመስከረም ውሎ የእለት ተውሳክ እና መጥቅዕ ሲደመሩ ከ30 ቢተርፍ በ30 ይገደፍና ነነዌ በየካቲት ትውላለች።
      ከላይ በተናገርነው መሠረትም የ2010 ዓም መባጃ ሐመር 21 ስለሆነ በዓለ መጥቅዑም በመስከረም ስለዋለ ነነዌ በደረቁ በመባጃ ሐመር ስለምትወጣ ጥር 21 ትገባለች ማለት ነው። ከዚህ በኋላ ያሉትን አጽዋማት እና በዓላትን ለማግኘት በመባጃ ሐመሩ ላይ የበዓሉን ወይም የጾሙን ተውሳክ ጨምሮ ከ30 ቢበልጥ በ30 በመግደፍ ቀሪውን መውሰድ ነው።
መባጃ ሐመር + የበዓል ወይም የጾም ተውሳክ = በዓል ወይም ጾም የሚውልበት እለት
ምሳሌ እንዲሆነንም የጀመርነውን የ2010 ዓም በዓላት እና አጽዋማት አወጣጥ እንመልከት።
      ዐቢይ ጾም፥
= 21+ 14
= 35 ይህን በ30 ቢገድፉት 1 ደርሶ 5 ይቀራል።
ስለዚህም የ2010 ዓ.ም ዐቢይ ጾም የካቲት 5 ይገባል ማለት ነው።

ደብረ ዘይት፥
= 21+ 11
= 32 ይህንም በ30 ቢገድፉት 1 ደርሶ 2 ይቀራል።
ስለዚህም የ2010 ዓ.ም ደብረ ዘይት መጋቢት 2 ይገባል ማለት ነው።

ሆሳዕና፥
=21 + 2
= 23 ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ሆሳዕና መጋቢት 23 ይውላል ማለት ነው።

ስቅለት፥
= 21 + 7
= 28 ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ስቅለት መጋቢት 28 ይውላል ማለት ነው።

ትንሳኤ፥
= 21 + 9
= 30 ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ትንሳኤ መጋቢት 30 ይውላል ማለት ነው።

ርክበ ካህናት፥ ይህ በዓል ደግሞ ኤጲስ ቆጶሳት
ለቤተክርስቲያን ጉሳይ የሚሰበሰቡበት ነው።
= 21 + 3
= 24 ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ርክበ ካህናት ሚያዝያ 24 ይውላል ማለት ነው።
ዕርገት፥
= 21 + 18
= 39 ይህን በ30 ቢገድፉት 1 ጊዜ ደርሶ 9 ይቀራል። ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ዕርገት ግንቦት 9 ይውላል ማለት ነው።

ጰራቅሊጦስ፥
= 21 + 28
=29 ይህን በ30 ቢገድፉት 1 ጊዜ ደርሶ 19 ይቀራል።
ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ጰራቅሊጦስ ግንቦት 19 ይውላል ማለት ነው።

ጾመ ሐዋርያት፥
= 21 + 29
= 50 ይህን በ30 ቢገድፉት 1 ጊዜ ደርሶ 20 ይቀራል። ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ጾመሐዋርያት ግንቦት 20 ይውላል ማለት ነው።

ጾመ ድኅነት(የዐርብ ረቡዕ ጾም)፥
= 21 + 1
= 22 ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ጾመ ድኅነት ግንቦት 22 ይውላል ማለት ነው።
(የእሥራ ምእት ወአሠርቱ ዓም በዓላት እና አጽዋማት)
      እስከዚህ ድረስ የበዓላት እና የአጽዋማት አወጣጥ የሚያሳይ ጥቂት መነሻ የሚሆኗችሁ ናቸው። ከዚህ የሚበልጥ ለመማር እና ይበልጥ ጠልቆ ለማዳበር ግን የኢትዮጵያ ታላቁ ሃብት ባሕተ ሐሳብ፣ ባሕረ ሐሳብ የተባሉትን መጻሕፍት እና ሌሎቹንም በመመልከት እንድታዳብሩት ለማሳሰብ እወዳለሁ።
      ይበልጥ ለማንበብ እንዲያስችሏችሁ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ ለመፈለግ ሞክሩ። አንዳንድ ዓመታት ላይ ወንበር አልቦ/0/ የሚሆንበት ጊዜ አለ። በዚህን ጊዜ እንዴት በዓላት እና አጽዋማትን ማግኘት ይቻላል? ይህን እና ሌሎችንም ንኩራን (የተለዩ) ጉዳዮች በቀጣዩ የማጠቃለያ ጦማር ጠብቁ። ይቆየን።
ይቀጥላል።
©ዘዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
ጥቅምት 5 2010 .

ጎንደር/ኢትዮጵያ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ