እሑድ 8 ኦክቶበር 2017

††† ባሕረ ሐሳብ-(ክፍል ሦስት)†††

       እንኳን ለወርኃ ጽጌ በሰላም አደረሳችሁ ውድ ኦርቶዶክሳውያን ወንድሞች እና እኅቶች። ወርኃ ጽጌ በቤተ ክርስቲያናችን በናፍቆት ከሚጾምባቸው እና የውድ እናታችንን የድንግል በክልኤ ወላዲተ አምላክ ማርያምን የስደቷን ነገር እና ጌታችንም ገና ከሕጻንነቱ አንስቶ መከራ መቀበሉን በማሰብ የምናመሰግንባት ወቅት ናት። በቤተክርስቲያናችንም ሊቃውንቱ ከመጀመሪያው ሳምንት እሑድ “ሀለፈ ክረምት/በተክሌ አቋቋም/ ወይም ትዌድሶ መርዓት/በጎንደር አቋቋም/” በማለት ጀምረው በስስት እያመሰገኑ በመጨረሻም “ሕብረ ሐመልሚል ወጸዓድዒድ ተፈጸመ ማኅሌተ ጽጌ” በማለት የጽጌውን ወቅት ምስጋና ይጨርሳሉ።
ወርኃ ጽጌ የምንለው ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6 ያለውን  ወቅት ነው። በዚህም ወቅት በቤተክርስቲያናችን ለምስጋና የምንጠቀምባቸው የዜማ ጸዋትው ማኅሌተ ጽጌ፣ ሠቆቃወ ድንግል የመሰሉትን ነው። መልካም ወርኃ ጽጌን እየተመኘሁ ቀድመን ወደ ጀመርነው የባሕረ ሐሳብ ትምህርት እንመለስ። በባለፈው ክፍል የባሕረ ሐሳብን ከአዝማናት ተነስተን፣ መስፈርታት የሚባሉትን፣ በየተወሰነ ጊዜ እየዞሩ የሚመጡትን አዕዋዳት የሚባሉትን፣ ዓመተ ወንጌላውያንን ከነስሌቱ፣ እለተ ዮሐንስን ከነስሌቱ ተመልክተን ነበር። ለነዚህ ሁሉ እንደምሳሌ ሁኖ እንዲያገለግለን ቀድሞ የተለጠፈውን የ2010 ዓ.ም በዓላት እና አጽዋማት ማውጫ እንድትመለከቱ እያሳሰብሁ የቅዱሳኑን ምልጃ እና የእግዚአብሔርን ቸርነት ረዳት በማድረግ የዛሬውን ትምህርት እጀምራለሁ።
ወንበር  †
ወንበር ተደላድሎ ለመቀመጥ የሚያገለግል እንደሆነ ሁሉ በባሕረ ሐሳብ ትምህርትም በዓላትን እና አጽዋማትን አደላድሎ በትክክል ለማውጣት የሚያገለግለን ቀመር ወንበር ተብሎ ይጠራል። ወንበርን ለማግኘት የሚከተሉትን የስሌት አማራጮች መጠቀም እንችላለን።
1/በሊቃውንት መንገድ ሲወጣ
በዚህ መንገድ ስናወጣ የዓመተ ዓለምን የሺህ ቤት በዓቢይ ቀመር/532/ እንገድፈዋለን። ከዚያ የሚገኘውንም ቀሪ ከመቶ ቤቱ ጋር በመጨመር ከማእከላዊ ቀመር/76/ የሚበልጥ ከሆነ በማእከላዊ ቀመር/76/ መግደፍ፣ ከዚህም የሚገኘውን ቀሪ ከአሥር እና ከአንድ ቤቱ ጋር በመጨመር በንዑስ ቀመር/19/ መግደፍ፣ ከዚያም ከሚገኘው ቀሪ 1 በመቀነስ የሚገኘው ውጤት ወንበር ይሆናል።
ምሳሌ፦ የ2010ን ወንበር እንፈግ
ዓዓ= 5500 + 2010 =7510 ከዚህ በኋላ ይህን በየቤታቸው እንመድብ
7000/532 =13 ቀሪ 84 ፣    84 + 500 = 584
584/76 =7 ቀሪ 52 ፣     52 + 10 =62
62/19=3 ቀሪ 5
አዋጅ
“አሐደ አእትት ለዘመን - አንዱን ለዘመኑ ስጠው” ይህም ማለት ዘመኑን ጀመርነው እንጂ አልፈጸምነውምና አንዱን ከቀሪው ላይ እናነሳለን ማለት ነው።
5 – 1= 4 ስለዚህ የ2010 ዓም ወንበር 4 ወጣ ይባላል ማለት ነው።/እናንተ ደግሞ የ1992 እና 2011ን ወንበር ለማውጣት ሞክሩ_ መልሱን በቀጣዩ ጊዜ እንመልሳለን_ እናንተም በኮመንት መመለስ ትችላላችሁ። በመልሱ ላይ ግን ያሰላችሁበትን መንገድ ማሳየት አትዘንጉ።/
2/በቀላል መንገድ ሲወጣ
በዚህኛው መንገድ ደግሞ ዓዓ በቀጥታ በንዑስ ቀመር መግደፍ ከዚያም ከሚገኘው ቀሪ ላይ አንድን በመቀነስ ወንበርን ማግኘት ይቻላል። ስሌቱም እንደሚከተለው ነው።
ምሳሌ፦ የ2010ን ወንበር በዚህ መንገድ እንፈልግ
ዓዓ = 2010 + 5500= 7510
7510/19 = 395 ቀሪ 5፣ ከዚህ በኋላ ከ5 ላይ 1 ስንነሳ 4 ይቀራል። በ2010 ዓም 4 ወንበር ወጣ ይባላል ማለት ነው።/ከላይ በመጀመሪያው ምሳሌ የሠራስኋቸውን ዓመታት በዚህኛውም መንገድ ደግማችሁ ለማስላት ሞክሩ/

አበቅቴ †
አበቅቴ ማለት ተረፈ ዘመን ማለት ነው። ይህም በጨረቃ እና በፀሐይ ዑደት መኻከል ያለውን ልዩነት የሚናገር ነው። በልደተ አበቅቴ ወይም አበቅቴ 0 በሚሆንበት ጊዜ ጨረቃ እና ፀሐይ ዓውደ ዓመታቸውን እኩል በመስከረም መባቻ/መስከረም 1/  ይጀምራሉ። የጨረቃ አንድ ዓመት ማለት 354 እለት ከ54 ኬክሮስ ስለሆነ ከፀሐይ ቀድማ ዑደቷን ትጨርስና ደግማ ሁለተኛውን ዑደት ትጀምራለች። ከዚህ በኋላ ጨረቃ እና ፀሐይ ዳግመኛ በመስከረም 1 በአንድ መስኮት እኩል ዑደታቸውን የሚጀምሩት ከ19 ዓመታት በኋላ ነው። ይህም ጨረቃ ዑደቷን ከጨረሰችበት እለት እስከ ጳጉሜን 5 እለት ያለውን ቆጥረው ከ30 ቢበልጥ በ30 ገድፈው የሚያገኙት ቀሪ የሚቀጥለው ዓመት አበቅቴ ይሆናል።
አበቅቴ ዋነኛው ጥቅሙ ከሕፀፅ ጋር በመሆን ሌሊትን ለማውጣት ሲሆን፣ ይህንም ካህናት በአሥርቆ ጸሎት ለማሣረግ ይጠቀሙበታል። ይህን የአሥርቆ መንገድ እንደአምላከ ቅዱሳን ፈቃድ በሌላ ጊዜ በሌላ ተከታታይ ጡመራ የምንማማረው መሆኑን ለመጠቆም እወዳለሁ።
አበቅቴን ለማስላት የተለያዩ መንገዶችን መጠቀም እንችላለን።
1/ ወንበርን በጥንተ አበቅቴ/11/ በማብዛት በ30 በግደፍ እና የሚገኘውን ቀሪ መውሰድ ነው።/አስታውሱ፦ ጥንተ አበቅቴ እያልን የምንጠራው ቅዱስ ዲሜጥሮስ በማታ የገባውን ሱባኤ ቀምሮ ያገኘውን ቁጥር ይኸውም 11ን ነው/
ምሳሌ፦ የ2010 ዓም አበቅቴን ለማግኘት
ወንበር * ጥንተ አበቅቴ/30 ከዚህም የሚገኘውን  ቀሪ መውሰድ ነው።
/አስታውሱ፦በባሕረ ሐሳብ ሕግ ዋናው የምንጠወምበት ነገር የሚገኝን ቀሪ ነው።/
4 * 11/30 = 1 ቀሪ 14፣ ይህም ማለት በ2010 ዓም 14 አበቅቴ ወጣ ይባላል።
2/ በአዋጅ መሠረት አበቅቴ እና መጥቅዕ ሁለቱ ሲጨመሩ ሁልጊዜም 30 ስለሚሆኑ ቀድመን መጥቅዕን ካገኘን ከ30 ላይ መጥቅዕን በመቀነስ አበቅቴን መግኘት ይቻላል።
/አዋጅ፦ “አበቅቴ ወመጥቅዕ ክልኤሆሙ ኢየአርጉ እም ሠላሳ፣ ወኢይወርዱ እምሠላሳ፣ ወትረ ይከውኑ ሠላሳ - አበቅቴ እና መጥቅዕ ሁለቱ ተጨምረው ከሠላሳ አይበልጡም፣ ከሠላሳ አያንሱም፣ ሁልጊዜም ሠላሳ ይሆናሉ።”/
ምሳሌ፦ የ2010 ዓም መጥቅዕ 16 ነው።/እንዴት እንደመጣ በቀጣዩ ቀመር እንመለከታለን/
30 – 16 =14 ስለዚህ በ2010 ዓም 14 አበቅቴ ወጣ እንላለን ማለት ነው።
3/ የአሁኑን ዓመት አበቅቴ ካወቅን የሚቀጥለውን ዓመት አበቅቴ ለማግኘት በአሁኑ ዓመት አበቅቴ ላይ ጥንተ አበቅቴን በጨመር ከ30 ቢተርፍ በ30 በመግደፍ የሚገኘው ቀሪ የሚቀጥለው ዓመት አበቅቴ ይሆናል ማለት ነው።
ምሳሌ፦ የ2010 ዓም አበቅቴ 14 ነው። ስለዚህ የ2011ን አበቅቴ ለመፈለግ በዚህ ላይ ጥንተ አበቅቴን ጨምሮ በ30 መግደፍ ነው።
14 + 11= 25፣ ነገር ግን 25 ከ30 ስለሚያንስ እንዳለ እንወስደዋለን ማለት ነው። በዚህም መሠረት በ2011 ዓም 25 አበቅቴ ወጣ እንላለን።
4/ ከምንሠራበት ዓመት በፊት ባለው ዓመት ጨረቃ ዑደቷን ከጨረሰችበት እለት አንስተን እስከዚያው ዓመት ጳጉሜን 5 እለት ያለውን በመቁጠር በ30 ገድፈን የሚገኘው ቀሪ የምንፈልገው ዓመት አበቅቴ ይሆናል ማለት ነው።/ለበለጠ ማብራሪያ የኢትዮጵያ ታላቁ ሀብት ባሕረ ሐሳብ የሚለውን መጽሐፍ ተመልከቱ/

መጥቅዕ †
መጥቅዕ ማለት ጠቅዐ፣ ደወለ ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ደወል ማለት ነው። መጥቅዕ መባሉም ደወል ሲደወል ካህናት ምእመናን ለስብሐተ እግዚአብሔር እንዲሰበሰቡ ሁሉ፣ በመጥቅዕም ተራርቀው የነበሩ በዓላት እና አጽዋማት ይሰበሰባሉ እና ነው። መጥቅዕ ከእለታት እና ከበዓላት ተውሳክ ጋር በመጨመር በዓላትን እና አጽዋማትን የሚያስገኝ ቀመር ነው። መጥቅዕ እንደ ወንበር እና እንደ አበቅቴ ሁሉ በተለያየ መንገድ ሊሰላ ይችላል። እንደሚከተለው ነው።
  1/ ወንበርን በጥንተ መጥቅዕ/19/ በመሰብሰብ የከዚያም የሚገኘውን በ30 በመግደፍ የሚገኘው ቀሪ መጥቅዕ ይባላል። /አስታውሱ፦ ጥንተ መጥቅዕ እያልን የምንጠራው ቅዱስ ዲሜጥሮስ በቀን የገባውን ሱባኤ ቀምሮ ያገኘውን ቁጥር ይኸውም 19ን ነው/
ምሳሌ፦ የ2010 ዓም መጥቅዕን ስንፈልግ
 ወንበር * ጥንተ መጥቅዕ/30 ከዚያም የሚገኘውን ቀሪ ውሰድ
4 * 19/30 = 2 ቀሪ 16 ስለዚህም በ2010 ዓም 16 መጥቅዕ ወጣ እንላለን።
2/ አበቅቴና መጥቅዕ ድምራቸው ሁል ጊዜም 30 ስለሆነ ከ30 ላይ አበቅቴን ቢቀንሱ መጥቅዕ ይገኛል።
3/ የፈለግነውን ዓመት መጥቅዕ ለማግኘት ከፈለግነው ዓመት በፊት ያለው ዓመት መጥቅዕ ላይ ጥንተ መጥቅዕን/19/ በመጨመር ከ30 ቢተርፍ በ30 በመግደፍ የሚገኘው ቀሪ የፈለግነው ዓመት መጥቅዕ ይሆናል ማለት ነው። ይቆየን።
ይቀጥላል።
©ዘዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
መስከረም 28 – 2010 ዓ.ም
ጎንደር/ኢትዮጵያ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ