ኢትዮጵያ ሀገራችን እጅግ ከምትኮራባቸው ሀብቷ መሀከል አንዱ ነገር የዘመን አቆጣጠሯ እንደሆነ ይታወቃል። ይህም የአሥራ ሦስት ወራት ባለቤት እና በዓላትን በራሷ በትክክለኛው ቀመር እንድታከብር አድርጓታል። የዚህን የአቆጣጠሯን ትክክለኛነት ከቦታው ስንደርስ እንናገራለን። በዚህ ተከታታይ ጦማርም ስለባሕረ ሐሳብ ምንነት፣ ስለስሌቱ፣ እንዲሁም የኛን የዘመን አቆጣጠር ከምን እንደመጣ እና ስለ ትክክለኛነቱ እንማማራለን። በዚህም በዓላትን እና አጽዋማትን ለማውጣት ያህል እንዲረዳን እንጂ ከስፋትና ጥልቀቱ የተነሳ እጅግ ጠልቀን አንነጋገርም። የቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት እና የእግዚአብሔር ቸርነት አይለየን።
የባሕረ ሐሳብ ምንነት †
ባሕረ ሓሳብ ማለት ከሁለት ጥምር ቃላት የተገኘ ሕብረ ቃል ሲሆን ትርጉሙም፤
ባሕር ማለት ዘመን ማለት ነው። “በመዳልው ደለወ ዓለመ ወበመሥፈርት ሰፈራ ለባሕር” እንዲል።
ሐሳብ ማለት ደግሞ ቁጥር ማለት ነው። ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ብፁዓን እለ ተኀድገ ሎሙ ኃጢአቶሙ ወእለ ኢሐሰበ ሎሙ ኲሎ ጌጋዮሙ - ኃጢአታቸው የተተወላቸው በደላቸውንም ያልቆጠረባቸው ንዑዳን ናቸው ” /መዝ 31፡1/በማለት እንደተናገረው ሐሳብ ማለት ቁጥር የሚል ትርጉም ይይዛል።
ባሕረ ሐሳብን ማን ደረሰው †
ባሕረ ሀሳብን ለማወቅ ብዙ አበው የተመኙ እና የደከሙ ቢሆንም የተገለጸው ግን ለእስክንድርያ 12ኛ ሊቀ ጳጳስ ለነበረው ለቅዱስ ድሜጥሮስ ነበር። እርሱም ልክ እንደቅዱስ ሕርያቆስ የቤተክርስቲያን ዕውቀት ያልነበረው ዳሩ ግን መስተገብረ ምድር /ገበሬ/ ነበር። የርሱ አባት እና አጎቱ በዘመነ ሰማዕታት ከኢየሩሳሌም ተሰደው ከባዕድ ሀገር ይኖሩ ነበር። የድሜጥሮስ አባት እንደራኒቆስ ሲባል አጎቱ ደግሞ አስተራኒቆስ ይባላል። ለአስተራኒቆስም ልእልተ ወይን የተባለች መልከመልካም ልጅ ነበረችው። የእረፍቱ ጊዜ ሲደርስም /በዚያ ስፍራ ከነርሱበቀር ሌላው ሁሉ አሕዛብ ነበርና/ “ልጄን ለአሕዛብ እንዳትድራት ብሎት ሞተ”።
ሁለቱም ለአቅመ አዳም ወሔዋን ሲደርሱ እንደራኒቆስ የወንድሙን አደራ በማስታወስ “ለአሕዛብ አጋብቼ ሕንፃ ሃይማኖት ከሚፈርስ ሕንፃ ሥጋ ቢፈርስ ይሻላል” በማለት ልእልተ ወይንን እና ቅዱስ ድሜጥሮስን ያጋቧቸዋል። በሠርጋቸውም እለት ማታ ሥርዓተ መርአት ወመርአዊ እንዲፈጽሙ ከጫጉላ ሲተዉአቸው እነርሱ ግን የወንድማማች ልጆች ስለሆኑ ሩካቤ ለመፈጸም ባለመፈለጋቸው በሐዘን ተውጠው ያለቅሱ ጀመር።
ልእልተ ወይንም “ይህን የሠራህ እኔን ንቀህ ነው ወይስ ተዛምዷችንን” አለችው። እርሱም የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም እንጂ እርሷንም ሆነ ዝምድናቸውን ንቆ አለመሆኑን ነገራት። ከዚህ በኋላ ሁለቱም ተስማምተው እንደባል እና ሚስት መስለው እየኖሩ ነገር ግን በሩካቤ ሳይተዋወቁ እንዲኖሩ ወሰኑ። በንጽሕናም ሲኖሩ መልአከ እግዚአብሔር አንድ ክንፉን ለልእተ ወይን አንድ ክንፉን ለድሜጥሮስ አልብሷቸው ይተኙ እና ጠዋት በርግብ አምሳል በመስኮት ሲወጣ ይታያቸው ነበር።
እንዲህም ባለ የንጽህና ጉዞ 48 ዓመታትን አብረው ከኖሩ በኋላ የእስክንድርያው 11ኛ ሊቀ ጳጳስ ዮልያኖስ የእረፍቱ ጊዜ ደርሶ ነበር እና ከርሱ ቀጥሎ የሚሾመው ማን እንደሆነ ለመንገር ሕዝቡን በቤተክርስቲያን ጠራ። ቅዱስ ድሜጥሮስም ወደእርሻው በገባ ግዜ ያለ ጊዜዋ የደረሰች የወይን ፍሬ አገኘ እና ያችን ለሊቀ ጳጳሱ ይዞ ሄደ። ለጳጳሱም በሰጠው ጊዜ ከርሱ ቀጥሎ እንደሚሾም በሱባኤ ስለተገለጠለት ቅብዓ ሜሮን ቀብቶ ሥርዓተ ጵጵስናን ፈጽሞለታል። ይህ ሲሆን ግን ቅዱስ ድሜጥሮስ አላወቀም ነበር።/የኢትዮጵያ ታላቁ ሀብት ባሕረ ሀሳብ/
ከጥቂት ቀናትም በኋላ ሊቀ ጳጳሱ ሲያርፍ ከርሱ ቀጥሎ ሊቀ ጳጳስ የሚሆነው ቅዱስ ድሜጥሮስ እንደሆነ ነግሯቸው ነበርና መንበር ብቻውን አያድርም በማለት ሂደው በመንበረ ማርቆስ ላይ ሊቀ ጳጳስ እንደሚሆን ነገሩት። እርሱ ግን “እኔ በአንድ በኩል ማይ’ም ገበሬ ነኝ፣ በዚያውም ላይ ሕጋዊ ነኝ። እንዴት በንጹሑ በማርቆስ መንበር ላይ እቀመጣለሁ” ቢላቸውም እነርሱ ግን ግድ አሉትና አስቀመጡት።
ለድሜጥሮስም ቅዳሴ እና መጻህፍት ተገልጠውለት ሕዝቡን ያስተምራቸው ጀመር። ከንጽሕናውም የተነሳ የሕዝቡ ሁሉ ኃጢአት ይታየው ነበር እና አንተ በቅተሀል ተቀበል አንተ ንስሐ ግባ እያለ ይመልሳቸው ጀመር። ሕዝቡም “እርሱ ሚስቱን አቅፎ እየተኛ በንጹሑ መንበረ ማርቆስ ላይ ብናስቀምጠው ጭራሽ ይከልክለን” በማለት በሐሜት ሲጎዱ መልአከ እግዚአብሔር ተገልጾለት ሕዝቡ በሕሜት ስለተጎዳ ንጽሕናቸውን እንዲገልጽላቸው ይነግረዋል። ድሜጥሮስም ሕዝቡ ሁሉ እንጨት እንዲያመጡ ይነግራቸው እና ደመራ አስደመረ።
ከቅዳሴም በኋላ በደመራው እሳት ውስጥ እየተመላለሰ ያጥን ጀመር። ልእልተ ወይንንም ከምቋመ አንስት/ከሴቶች መቆሚያ/ አስጠርቶ “ስፍሒ አጽፍኪ - ልብስሺን ዘርጊ” በማለት ፍሕሙን እያነሳ በልብሷ ላይ ጨመረ እና እየዞረች ለሕዝቡ ሁሉ አሳየች። እርሷም ሆነ ልብሷ ምንም በእሳቱ አልተነኩም ነበር። ድሜጥሮስንም ምንድነው ይህ ነገር አባታችን ብለው ሲጠይቁት ለ48 አብረው ሲኖሩ በግብረ መርአት ወመርአዊ/በተራክቦ/ እንደማይተዋወቁ ሲገልጥላቸው ሕዝቡ ሁሉ በመጸጸት አባ ሥረይ ለነ እያሉ ይቅርታ ጠየቁ። እርሱም “ይፍታ ያንጽሕ ወያስተሥሪ” በማለት የኑዛዜን ሥርዓት ጀመረልን።
ይህም ቅዱስ አባት በመንበረ ጵጵስናው ሳለ አንድ ትልቅ ተምኔት ነበረው። ጾመ ነነዌ ዐቢይ ጾም እና ጾመ ሕዋርያት ከሰኑይ፣ ደብረ ዘይት ሆሳዕና ትንሳኤ እና ጰራቅሊጦስ ከእሑድ፣ ርክበ ካህናት እና ጾመ ድኅነት ከረቡዕ፣ ዕርገት ከሐሙስ እና ስቅለት ከዓርብ እንዳይወጣ ይመኝ ነበር። ምክንያቱም እሊህ በዓላት ለመጀመሪያ ጊዜ የዋሉት በእነዚህ እለት ስለነበር ነው።
እንዲህም እያለ ሲመኝ የታዘዘ መልአክ ወደርሱ መጥቶ በምኞት ብቻ እንደማይሆን ነግሮት ሱባኤ እንዲገባ ይነግረዋል። “ከሌሊቱ 23 ሱባኤ ግባ እና አበቅቴ ይሁንህ፤ ከቀኑ 7 ሱባኤ ግባ እና መጥቅዕ ይሁንህ” ብሎታል። ሌሊቱን አብዝቶ ቀኑን ማሳነሱም ቀኑን የተጣላ ሲያስታርቅ፣ የታመመ ሲጠይቅ እንዲህ ባለው ሁሉ ግብር ስለሚያሳልፍ ነው። ከዚህም ጥንተ አበቅቴ እና ጥንተ መጥቅዕ ይገኛሉ።
አዋጅ፦ ማንኛውም ቁጥር ከ30 ከበለጠ በ30/በዐውደ ወርኅ/ ግደፈው እና ቀሪውን ውሰድ።
የቀኑን ስናሰላ
አንድ ሱባኤ ማለት ሰባት እለት ነው።
7*7=49 ይህንም በ30 ስንገድፈው 1 ጊዜ ይደርስና 19 ይቀራል። ይህም ጥንተ መጥቅዕ ይባላል። ቀጣይ በምናነሳቸው ሌሎች ቀመሮች ላይ በዓላትን ለማውጣት እና የየዓመታቱን መጥቅዕ ለማውጣት እንገለገልበታለን።
የሌሊቱን ስናሰላ
23*7=161 ይህንም በ30 ስንገድፈው 5 ጊዜ ይደርስና 11 ይቀራል። ይህም ጥንተ አበቅቴ ይባላል። ቀጥለን በምናነሳቸው ሌሎች ቀመሮች ላይ ሌሊትን ለማውጣት እና የየዓመታቱን አበቅቴ ለማውጣት እንገለገልበታለን። ይህም በተለይም ካህናት ጸሎትን ለማሣረግ አሥርቆት የሚያደርጉበት ነው።
ባሕረ ሐሳብን ማን መማር አለበት? †
በጉባኤ ቤት ከመጻሕፍት ጉባኤ ጋር በአንድነት የሚሰጥ ትምህርት ነው። በዚህም ካህን የሆነ ሁሉ በበረሀ ጥላ ሥር እንዳለች ምንጭ የሚያረካ እንዲሆን መማር አለበት። ምክንያቱም በዓላትን እና አጽዋማትን አወጥቶ ለልጆቹ መንገር አለበት እና ነው።
ምእመናንም ቢሆኑ በተለያየ ምክንያት ከሀገር የሚወጡበት አጋጣሚ ስለሚኖር በባዕድ ሀገር ሁነው በዓላትን በአግባቡ ለማክበር እና አጽዋማትን ለመጾም ማወቅ ያስፈልጋቸዋል።
የባሕረ ሐሳብ ስሌት †
የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር የሚጀምረው ከጥንታት ነው። ጥንትነቱም ከፍጥረተ ዓለም፣ ከፍጥረተ ፀሐይ፣ ከፍጥረተ ጨረቃ እና ክዋክብት ነው። ዓለም የተፈጠረበት እለተ እሑድ ጥንተ እለት ይባላል። እንዲህም መባሉ ፍጥረታት መፈጠር የጀመሩበት እለት በመሆኑ ነው።
አዝርዕት እጽዋት እና አትክልት የተፈጠሩበት እለተ ሠሉስ ደግሞ ጥንተ ቀመር ይባላል። ቁጥር የተጀመረበት እለት ስለሆነ ነው።
ፀሐይ ጨረቃ እና ክዋክብት የተፈጠሩበት እለተ ረቡዕም ጥንተ ዖን/ዮን/ በመባል ይታወቃል። ዖን ማለትም ብርሃን ማለት ነው። በመጽሐፍ “ዖን ይእቲ ስማ ለፀሐይ” እንዲል። ይቆየን።
ይቀጥላል።
©ዘዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
መስከረም 14 – 2010 ዓ.ም
አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ