ዓርብ 27 ኦክቶበር 2017

††† ባሕረ ሐሳብ (አምስት - ማጠቃለያ) †††

      በባለፈው የባሕረ ሐሳብ ትምህርት ቆይታችን ከመጥቅዕ አንስተን የቀረውን የባሕረ ሐሳብ ክፍል ተመልክተን ነበር። እንደአምላከ ቅዱሳን ፍቃድ እንቀጥላለን፤ የሥሉስ ቅዱስ ቸርነት አይለየን።
   ንኩራን አቅማራት
     እሊህም ንኩራን ያልኋቸው ከዚህ በፊት በተማማርንበት መንገድ የማናሰላቸው ዓመታት ስላሉ የእሊያን ዓመታት በዓላት እና አጽዋማት ለማውጣት የምንጠቀምባቸውን የቀመር መንገዶች ነመጠቆም ነው። ለምሳሌ በ2005 ዓም ላይ ወንበር ከዜሮ በታች (negative) ይሆናል። ይህ ማለት በዚህ ዓመት ላይ አበቅቴ እንደአዲስ የሚጀምርበት ዓመት ነው ማለት ነው። በ2006 ዓም ደግሞ ወንበር አልቦ(ዜሮ) ስለሚሆን በዚህ ዓመት ያለውን አበቅቴ እና መጥቅዕ እስካሁን በተመለከትነው መንገድ መፈለግ አንችልም። እነዚህን የምንፈልግበት መንገድ የሚከተለው ነው።
     ወንበር ከዜሮ በታች በሚመጣብን ጊዜ፣ ሁልጌም እንዲህ ያለ ዚገጥመን፣ በዚያ ዓመት አበቅቴው ዑደቱን የሚጨርስበት የመጨረሻው ዓመት ነው ማለት ነው። ለአበቅቴ መጨረሻው ደግሞ 18 ነው። ስለዚህም በዚህ ዓመት ላይ አበቅቴውን 18 በማድረግ ማስላት እንችላለን።
o   የ2005 ዓምን በዓላት እና  አጽዋማት በዚህ መንገድ አበቅቴውን  ፈልገህ፣ ከ30 ላይ አበቅቴውን በመቀነስ መጥቅዑን ካገኘህ በኋላ በዓላት እና አጽዋማቱን አውጣ።
     በሌላ ጊዜ ደግሞ ወንበር አልቦ ወይም ባዶ ሊመጣ ይችላል። በዚህ ዓመት ላይ ደግሞ በዓላትን ለማውጣት ብንሻ፣ ወንበር አልቦ ስለሆነብን አበቅቴና መጥቅዕን ማስላት አንችልም። እንዲህ ያለ በገጠመን ጊዜ መስከረም 30 የዋለበት እለት ተውሳክ መባጃ ሐመር ይሆናል። መጥቅዑም 30 ተደርጎ ይወሰዳል። ከዚህ በኋላ በዓላትን እና  አጽዋማትን መውጣት እንችላለን።
o   የ2006 ዓምን በዓላት እና  አጽዋማት በዚህ መንገድ መጥቅዑን እና መባጃ ሐመሩን ፈልገህ በዓላት እና አጽዋማቱን ፈልግ።
   ስያሜ አውራኅ ወእለታት
      የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ወራቷንም ሆነ እለታቷን ስትሰይም መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ እንጂ እንደሌላው ዓለም የሚመለክ ጣዖትን ወይም አንድ ምድራዊ ንጉስን መሠረት አድርጋ አይደለም። ይህ ግልጽ ይሆንልን ዘንድ በመጠኑ እንመልከተው።

      የእለታት ስያሜ በቤተክርስቲያናችን እና በምዕራቡ ዓለም
      የምእራቡ ዓለም እለታትን የሰየመው የሚያመልካቸውን ጣዖታት መሠረት በማድረግ ነው።ለዚህም  እንደምሳሌ የሚከተለውን እንይ
o   Monday ማለት የጨረቃ ቀን ለማለት ነው። ይኸውም ጨረቃን ስለሚያመልኩ ከዚያ መታሰቢ ያ ለማድረግ ነው።
o   Sunday ማለት የፀሐይ ቀን ለማለት ነው። ይኸውም ፀሐይን ያመልኩ ስለነበር የሰየሙለት መታሰቢያ ነው።
      ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ግን እለታትን ስትሰይም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ይዛ ነው። ለዚህም እያንዳንዱን እለት ለምን እንደተሰየመ እና ምን  ማለት እንደሆነ እንደሚከተለው እንናገራለን።
o   እሑድ ማለት አሐደ አንድ አደረገ ካለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም አንደኛ ማለት ነው። ይኸውም ለፍጥረታት መፈጠር የመጀመሪያው እለት ስለሆነ ነው። በዚህም እለት ስምንት ፍጥረታት ተፈጥረዋል።
o   ሰኑይ ማለት ሰነየ ሁለት አደረገ ካለቅ የግእዝ ቃል የተገኘ ነው። ለፍጥረታት መፈጠር ሁለተኛው እለት በመሆኑ ሁለተኛ ለማለት ሰኑይ ተብሏል። በዚህም እለት ውሃ ለሦስት ተከፍሏል። የተፈጠረው ግን አንድ ፍጥረት ብቻ ነው። እርሱም ጠፈር ነው።
o   ሠሉስ  ማለት በአማርኛው ማግሰኞ በመባል የሚታወቀው ሲሆን ሠለሰ ሦስት አደረገ ካለው የግእዝ ቃል ተገኝቶ ሦስተኛ የሚል ትርጉም ያለው ቃል ነው። ፍጥረታት የተፈጠሩበት ሦስተኛው እለት ስለሆነው። በዚህም እለት ሦስት ፍጥረታት ተፈጥረዋል።
o   ረቡዕ ማለት ረብዐ አራት አደረገ ካለው የግእዝ ቃል የተገኘ ነው። ትርጉሙም አራተኛ ማለት ነው። ይኸውም ለፍጥረት መፈጠር አራተኛ የሆነ እለት ማለት ነው። በዚህም እለት ሥኦስት የብርሃን ፍጥረታት ተፈጥረዋል።
o   ሐሙስ ማለት ሐመሰ አምስት አደረገ ከሚል የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን አምስተኛ ማለት ነው።ይኸውም ለፍጥረታት መፈጠር አምስተኛ እለት ማለት ነው። በዚህም ሦስት ፍጥረታት ተፈጥረዋል።
o   ዓርብ ማለት ዓርበ ተካተተ ካለው ቃል የተገኘ ሲሆን መካተቻ ማለት ነው። ፍጥረታት ተፈጥረው የተካተቱበት እለት ስለሆነ ማለትም ፍጥረት ተፈጥረው የተጨረሱት በዚህ እለት ነው።
o   ቀዳሚት ማለት የመጀመሪያዋ ማለት ሲሆን የመጀመሪያዋ መባሏም ለሰንበትነት ነው። ይህም ማለት እግዚአብሔር ፍጥረታትን ከፈጠረ በኋላ ያረፈባት እለት ናትና ነው። ስለዚህም የመጀመሪያይቱ ሰንበት ለማለት ቀዳሚት አላት። ሁለተኛይቱ ሰንበት እሑድ ናትና።
      የአውራኅን ስያሜ እና ሌሎችንም ከዚህ የሰፉትን ነገሮች ከሚከተሉት እና  ከሌሎችም መጻሕፍት በማንበብ ታሰፉት ዘንድ እጠቁማለሁ። የቅዱሳኑ ምልጃ እና ቃልኪዳን፣ የእማምላክ አማላጅነት የእግዚአብሔር ቸርነት አይለየን።
      የሚነበቡ መጻሕፍት
o   የኢትዮጵያ ታላቁ ሀብት ባሕረ ሐሳብ
o   ባሕረ ሐሳብ  
o   የዘመን አቆጣጠር እና ሌሎችም።
ተፈጸመ ነገረ ባሕረ ሐሳብ በሰላመ እግዚአብሔር አሜን።
©ዘዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
ጥቅምት 12 2010 .

ጎንደር/ኢትዮጵያ

††† ባሕረ ሐሳብ (አራት) †††

      በባለፈው የባሕረ ሐሳብ ትምህርት ቆይታችን ወንበርን፣ አበቅቴን እና መጥቅዕን ተመልክተን ነበር። ባለፈው ክፍል ካቆምንበት ከመጥቅዕ የቀረውን እና ሌሎቹንም እንደአምላከ ቅዱሳን ፍቃድ እንቀጥላለን፤ የሥሉስ ቅዱስ ቸርነት አይለየን።
መጥቅዕን በባለፈው ክፍል በተማማርናቸው መንገዶች ካገኘን በኋላ በዓላትን እና አጽዋማትን ለማግኘት ቀድመን መጥቅዕ የሚውልበትን እለት ማወቅ ይጠበቅብናል። ለዚህም የሚከተለውን አዋጅ ልብ ይሏል።
አዋጅ
    1/መጥቅዕ ከ14 ቢበዛ በመስከረም ንዛ፣ መጥቅዕ ከ14 ቢያንስ ከጥቅምት ዳብስ
ይህም ማለት መጥቅዕን ስንፈልግ ያገኘነው ውጤት ከ14 ቢበልጥ በዓለ መጥቅዕ በመስከረም ይውላል። መጥቅዕ ከ14 ቢያንስ ደግሞ በዓለ መጥቅዕ በጥቅምት ይውላል ማለት ነው። ይህም በቀጣይ ለምንመለከተው ቀመር ወሳኝ ነው።
     መባጃ ሐመር
      መባጃ ሐመር፥ ቃልነቱ ግእዝ ወይም ሌላ አይደለም። ፍርንዱስ ነው። ይህም ማለት የአማርኛ እና የግእዝ ቃላት ጥምረት ውጤት ነው ማለት ነው። መባጃ 'ባጀ፤ ከረመ' ካለው የአማርኛ ቃል የተገኘ ሲሆን ማክረሚያ ማለት ነው። 'ሐመር' ማለት ደግሞ በግእዝ መርከብ ማለት ነው። ስለዚህም በአጠቃላይ ትርጉሙ ማክረሚያ መርከብ ማለት ነው። ስሌቱም እንደሚከተለው ነው።
      ይህም ቀመር ነነዌን ጨምሮ ሌሎቹንም በዓላት እና አጽዋማት ለማግኘት የምንጠቀምበት ቀመር ነው። ይህም የሚሰላው መጥቅዕን በዓለ መጥቅዕ ከዋለበት እለት ተውሳክ ጋር በመደመር የምገኘው ውጤት ከ30 ቢበልጥ በ30 በመግደፍ የሚገኝ ነው።
                        መጥቅዕ + በዓለ መጥቅዕ የዋለበት እለት ተውሳክ = መባጃ ሐመር
     ተውሳክ
ተውሳክ ወሰከ፣ ጨመረ ካለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ጭማሪ ማለት ነው። ይህም ሁለት ዓይነት ሲሆን አንደኛው የእለታት ተውሳክ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ የበዓላት እና የአጽዋማት ተውሳክ ነው። እሊህን አንድ በአንድ በመጠኑ እንመለከታቸዋለን።


የእለታት ተውሳክ
      የእለታት ተውሳክ የምንላቸው ከቀዳሚት አንስቶ እስከ ዓርብ ያሉትን እለታት ተውሳካት ነው። ይኸውም ከቀዳሚት ይጀምራል። ይህም የሚገኘው በዓለ መጥቅዕ ከዋለበት እለት ሳኒታ /ማግስት/ እስከ ነነዌ ያለውን በመቁጠር በ30 በመግደፍ ነው።
       በዓለ መጥቅዕ በቀዳሚት ቢውል፣ ከዚህ እስከ ነነዌ ያለውን ቢቆጥሩት 128 ይሆናል፤ እሑድ ቢውል፣ ከዚህ እስከ ነነዌ ያለው 127 ይሆናል፤ ሰኑይ ቢውል 126፤ ሠሉስ ቢውል 125፤ ረቡዕ ቢውል 124፤ ሐሙስ ቢውል ደግሞ 123፤ ዓርብ ቢውል ደግሞ 122 ይሆናል። እሊህንም በ30 ቢገድፏቸው እያንዳንዳቸው እንደሚከተለው ይሆናሉ።
እለት         ተውሳክ
ቀዳሚት       8
እሑድ          7
ሰኑይ            9
ሠሉስ           5
ረቡዕ            4
ሐሙስ          3
ዓርብ            2  ይሆናሉ።
ለምሳሌ
የ2010 ዓምን መባጃ ሐመር እንፈልግ።
የ2010 መጥቅዕ 16 ነው። መስከረም የባተው ሰኑይ እለት ነው። ከመስከረም መባቻ እለት ሰኑይ እስከ ሳምንቱ ሰኑይ 8፣ ከሳምንቱ ሰኑይ እስከ ቀጣዩ ሳምንት ሰኑይ 15፣ በማግስቱ ሠሉስ 16 ይሆናል። መስከረም 16 የዋለው በዓለ መጥቅዕ እለቱ ሠሉስ ነው ማለት ነው። ስለዚህም በዓለ መጥቅዕ የዋለው ሠሉስ ስለሆነ ተውሳኩ 5 ይሆናል።
መጥቅዕ + በዓለ መጥቅዕ የዋለበት እለት ተውሣክ = መባጃ ሐመር
ከዚያም የተገኘውን ውጤት በ30 በመግደፍ ቀሪውን መውሰድ።
16 + 5 = 21 በ2010 ዓም 21 መባጃ ሐመር ይሆናል።
መጥቅዕ + በዓለ መጥቅዕ የዋለበት እለት ተውሣክ፣ ከዚህ የተገኘውም ከሠላሳ ቢተርፍ በ30 ገድፈህ ቀሪውን ውሰድ። የበዓለ መጥቅዕም ተውሳክ፣ ሠሉስ እለት ስለሆነ ተውሳኩ 5 ነው።
16 + 5= 21 ይህም ከ30 ያነሰ ስለሆነ እንዳለው እንወስደዋለን።
የበዓለት እና የአጽዋማት ተውሳክ
      በዓላት እና አጽዋማት የሚውሉበትን እለት ለማወቅ ከበዓላቱ እና ከአጽዋማቱ ተውሳክ ጋር መባጃ ሐመርን በመደመር ከ30 ቢበልጥ በ30 ግደፍ። የቀረውንም ውሰድ። ሌሎቹ በዓላት እና አጽዋማት በተውሳክ ሲወጡ ነነዌ ግን በደረቅ መባጃ ሐመር ትወጣለች። ምክንያቱም እርሷ ምንም ተውሳክ የላትም። ተውሳካቱም የሚከተሉት ናቸው።
ነነዌ                                0
ዐቢይ ጾም                     14
ደብረ ዘይት                   11
ሆሳዕና                           2
ስቅለት                           7
ትንሣኤ                          9
ርክበ ካህናት                   3
ዕርገት                           18
ጰራቅሊጦስ                    28
ጾመ ሐዋርያት                29
ጾመ ድኅነት                    1           ይሆናሉ።
      የበዓላት እና የአጽዋማትን ተውሳክ ለማግኘት ነነዌ ከዋለችበት እለት ሳኒታ/ማግስት/ እስከ በዓሉ ወይም ጾሙ ድረስ በመቁተር የተገኘውን በ30 በመግደፍ የሚገኘው ቀሪ የበዓሉ ወይም የጾሙ ተውሳክ ይሆናል።
አዋጅ፤
    1/ በዓለ መጥቅዕ በመስከረም ከዋለ ነነዌ በጥር ትውላለች።
    2/ በዓለ መጥቅዕ በጥቅምት ከዋለ ነነዌ በየካቲት ትውላለች።
    3/ በዓለ መጥቅዕ በመስከረም ውሎ የእለት ተውሳክ እና መጥቅዕ ሲደመሩ ከ30 ቢተርፍ በ30 ይገደፍና ነነዌ በየካቲት ትውላለች።
      ከላይ በተናገርነው መሠረትም የ2010 ዓም መባጃ ሐመር 21 ስለሆነ በዓለ መጥቅዑም በመስከረም ስለዋለ ነነዌ በደረቁ በመባጃ ሐመር ስለምትወጣ ጥር 21 ትገባለች ማለት ነው። ከዚህ በኋላ ያሉትን አጽዋማት እና በዓላትን ለማግኘት በመባጃ ሐመሩ ላይ የበዓሉን ወይም የጾሙን ተውሳክ ጨምሮ ከ30 ቢበልጥ በ30 በመግደፍ ቀሪውን መውሰድ ነው።
መባጃ ሐመር + የበዓል ወይም የጾም ተውሳክ = በዓል ወይም ጾም የሚውልበት እለት
ምሳሌ እንዲሆነንም የጀመርነውን የ2010 ዓም በዓላት እና አጽዋማት አወጣጥ እንመልከት።
      ዐቢይ ጾም፥
= 21+ 14
= 35 ይህን በ30 ቢገድፉት 1 ደርሶ 5 ይቀራል።
ስለዚህም የ2010 ዓ.ም ዐቢይ ጾም የካቲት 5 ይገባል ማለት ነው።

ደብረ ዘይት፥
= 21+ 11
= 32 ይህንም በ30 ቢገድፉት 1 ደርሶ 2 ይቀራል።
ስለዚህም የ2010 ዓ.ም ደብረ ዘይት መጋቢት 2 ይገባል ማለት ነው።

ሆሳዕና፥
=21 + 2
= 23 ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ሆሳዕና መጋቢት 23 ይውላል ማለት ነው።

ስቅለት፥
= 21 + 7
= 28 ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ስቅለት መጋቢት 28 ይውላል ማለት ነው።

ትንሳኤ፥
= 21 + 9
= 30 ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ትንሳኤ መጋቢት 30 ይውላል ማለት ነው።

ርክበ ካህናት፥ ይህ በዓል ደግሞ ኤጲስ ቆጶሳት
ለቤተክርስቲያን ጉሳይ የሚሰበሰቡበት ነው።
= 21 + 3
= 24 ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ርክበ ካህናት ሚያዝያ 24 ይውላል ማለት ነው።
ዕርገት፥
= 21 + 18
= 39 ይህን በ30 ቢገድፉት 1 ጊዜ ደርሶ 9 ይቀራል። ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ዕርገት ግንቦት 9 ይውላል ማለት ነው።

ጰራቅሊጦስ፥
= 21 + 28
=29 ይህን በ30 ቢገድፉት 1 ጊዜ ደርሶ 19 ይቀራል።
ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ጰራቅሊጦስ ግንቦት 19 ይውላል ማለት ነው።

ጾመ ሐዋርያት፥
= 21 + 29
= 50 ይህን በ30 ቢገድፉት 1 ጊዜ ደርሶ 20 ይቀራል። ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ጾመሐዋርያት ግንቦት 20 ይውላል ማለት ነው።

ጾመ ድኅነት(የዐርብ ረቡዕ ጾም)፥
= 21 + 1
= 22 ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ጾመ ድኅነት ግንቦት 22 ይውላል ማለት ነው።
(የእሥራ ምእት ወአሠርቱ ዓም በዓላት እና አጽዋማት)
      እስከዚህ ድረስ የበዓላት እና የአጽዋማት አወጣጥ የሚያሳይ ጥቂት መነሻ የሚሆኗችሁ ናቸው። ከዚህ የሚበልጥ ለመማር እና ይበልጥ ጠልቆ ለማዳበር ግን የኢትዮጵያ ታላቁ ሃብት ባሕተ ሐሳብ፣ ባሕረ ሐሳብ የተባሉትን መጻሕፍት እና ሌሎቹንም በመመልከት እንድታዳብሩት ለማሳሰብ እወዳለሁ።
      ይበልጥ ለማንበብ እንዲያስችሏችሁ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ ለመፈለግ ሞክሩ። አንዳንድ ዓመታት ላይ ወንበር አልቦ/0/ የሚሆንበት ጊዜ አለ። በዚህን ጊዜ እንዴት በዓላት እና አጽዋማትን ማግኘት ይቻላል? ይህን እና ሌሎችንም ንኩራን (የተለዩ) ጉዳዮች በቀጣዩ የማጠቃለያ ጦማር ጠብቁ። ይቆየን።
ይቀጥላል።
©ዘዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
ጥቅምት 5 2010 .

ጎንደር/ኢትዮጵያ

እሑድ 8 ኦክቶበር 2017

††† ባሕረ ሐሳብ-(ክፍል ሦስት)†††

       እንኳን ለወርኃ ጽጌ በሰላም አደረሳችሁ ውድ ኦርቶዶክሳውያን ወንድሞች እና እኅቶች። ወርኃ ጽጌ በቤተ ክርስቲያናችን በናፍቆት ከሚጾምባቸው እና የውድ እናታችንን የድንግል በክልኤ ወላዲተ አምላክ ማርያምን የስደቷን ነገር እና ጌታችንም ገና ከሕጻንነቱ አንስቶ መከራ መቀበሉን በማሰብ የምናመሰግንባት ወቅት ናት። በቤተክርስቲያናችንም ሊቃውንቱ ከመጀመሪያው ሳምንት እሑድ “ሀለፈ ክረምት/በተክሌ አቋቋም/ ወይም ትዌድሶ መርዓት/በጎንደር አቋቋም/” በማለት ጀምረው በስስት እያመሰገኑ በመጨረሻም “ሕብረ ሐመልሚል ወጸዓድዒድ ተፈጸመ ማኅሌተ ጽጌ” በማለት የጽጌውን ወቅት ምስጋና ይጨርሳሉ።
ወርኃ ጽጌ የምንለው ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6 ያለውን  ወቅት ነው። በዚህም ወቅት በቤተክርስቲያናችን ለምስጋና የምንጠቀምባቸው የዜማ ጸዋትው ማኅሌተ ጽጌ፣ ሠቆቃወ ድንግል የመሰሉትን ነው። መልካም ወርኃ ጽጌን እየተመኘሁ ቀድመን ወደ ጀመርነው የባሕረ ሐሳብ ትምህርት እንመለስ። በባለፈው ክፍል የባሕረ ሐሳብን ከአዝማናት ተነስተን፣ መስፈርታት የሚባሉትን፣ በየተወሰነ ጊዜ እየዞሩ የሚመጡትን አዕዋዳት የሚባሉትን፣ ዓመተ ወንጌላውያንን ከነስሌቱ፣ እለተ ዮሐንስን ከነስሌቱ ተመልክተን ነበር። ለነዚህ ሁሉ እንደምሳሌ ሁኖ እንዲያገለግለን ቀድሞ የተለጠፈውን የ2010 ዓ.ም በዓላት እና አጽዋማት ማውጫ እንድትመለከቱ እያሳሰብሁ የቅዱሳኑን ምልጃ እና የእግዚአብሔርን ቸርነት ረዳት በማድረግ የዛሬውን ትምህርት እጀምራለሁ።
ወንበር  †
ወንበር ተደላድሎ ለመቀመጥ የሚያገለግል እንደሆነ ሁሉ በባሕረ ሐሳብ ትምህርትም በዓላትን እና አጽዋማትን አደላድሎ በትክክል ለማውጣት የሚያገለግለን ቀመር ወንበር ተብሎ ይጠራል። ወንበርን ለማግኘት የሚከተሉትን የስሌት አማራጮች መጠቀም እንችላለን።
1/በሊቃውንት መንገድ ሲወጣ
በዚህ መንገድ ስናወጣ የዓመተ ዓለምን የሺህ ቤት በዓቢይ ቀመር/532/ እንገድፈዋለን። ከዚያ የሚገኘውንም ቀሪ ከመቶ ቤቱ ጋር በመጨመር ከማእከላዊ ቀመር/76/ የሚበልጥ ከሆነ በማእከላዊ ቀመር/76/ መግደፍ፣ ከዚህም የሚገኘውን ቀሪ ከአሥር እና ከአንድ ቤቱ ጋር በመጨመር በንዑስ ቀመር/19/ መግደፍ፣ ከዚያም ከሚገኘው ቀሪ 1 በመቀነስ የሚገኘው ውጤት ወንበር ይሆናል።
ምሳሌ፦ የ2010ን ወንበር እንፈግ
ዓዓ= 5500 + 2010 =7510 ከዚህ በኋላ ይህን በየቤታቸው እንመድብ
7000/532 =13 ቀሪ 84 ፣    84 + 500 = 584
584/76 =7 ቀሪ 52 ፣     52 + 10 =62
62/19=3 ቀሪ 5
አዋጅ
“አሐደ አእትት ለዘመን - አንዱን ለዘመኑ ስጠው” ይህም ማለት ዘመኑን ጀመርነው እንጂ አልፈጸምነውምና አንዱን ከቀሪው ላይ እናነሳለን ማለት ነው።
5 – 1= 4 ስለዚህ የ2010 ዓም ወንበር 4 ወጣ ይባላል ማለት ነው።/እናንተ ደግሞ የ1992 እና 2011ን ወንበር ለማውጣት ሞክሩ_ መልሱን በቀጣዩ ጊዜ እንመልሳለን_ እናንተም በኮመንት መመለስ ትችላላችሁ። በመልሱ ላይ ግን ያሰላችሁበትን መንገድ ማሳየት አትዘንጉ።/
2/በቀላል መንገድ ሲወጣ
በዚህኛው መንገድ ደግሞ ዓዓ በቀጥታ በንዑስ ቀመር መግደፍ ከዚያም ከሚገኘው ቀሪ ላይ አንድን በመቀነስ ወንበርን ማግኘት ይቻላል። ስሌቱም እንደሚከተለው ነው።
ምሳሌ፦ የ2010ን ወንበር በዚህ መንገድ እንፈልግ
ዓዓ = 2010 + 5500= 7510
7510/19 = 395 ቀሪ 5፣ ከዚህ በኋላ ከ5 ላይ 1 ስንነሳ 4 ይቀራል። በ2010 ዓም 4 ወንበር ወጣ ይባላል ማለት ነው።/ከላይ በመጀመሪያው ምሳሌ የሠራስኋቸውን ዓመታት በዚህኛውም መንገድ ደግማችሁ ለማስላት ሞክሩ/

አበቅቴ †
አበቅቴ ማለት ተረፈ ዘመን ማለት ነው። ይህም በጨረቃ እና በፀሐይ ዑደት መኻከል ያለውን ልዩነት የሚናገር ነው። በልደተ አበቅቴ ወይም አበቅቴ 0 በሚሆንበት ጊዜ ጨረቃ እና ፀሐይ ዓውደ ዓመታቸውን እኩል በመስከረም መባቻ/መስከረም 1/  ይጀምራሉ። የጨረቃ አንድ ዓመት ማለት 354 እለት ከ54 ኬክሮስ ስለሆነ ከፀሐይ ቀድማ ዑደቷን ትጨርስና ደግማ ሁለተኛውን ዑደት ትጀምራለች። ከዚህ በኋላ ጨረቃ እና ፀሐይ ዳግመኛ በመስከረም 1 በአንድ መስኮት እኩል ዑደታቸውን የሚጀምሩት ከ19 ዓመታት በኋላ ነው። ይህም ጨረቃ ዑደቷን ከጨረሰችበት እለት እስከ ጳጉሜን 5 እለት ያለውን ቆጥረው ከ30 ቢበልጥ በ30 ገድፈው የሚያገኙት ቀሪ የሚቀጥለው ዓመት አበቅቴ ይሆናል።
አበቅቴ ዋነኛው ጥቅሙ ከሕፀፅ ጋር በመሆን ሌሊትን ለማውጣት ሲሆን፣ ይህንም ካህናት በአሥርቆ ጸሎት ለማሣረግ ይጠቀሙበታል። ይህን የአሥርቆ መንገድ እንደአምላከ ቅዱሳን ፈቃድ በሌላ ጊዜ በሌላ ተከታታይ ጡመራ የምንማማረው መሆኑን ለመጠቆም እወዳለሁ።
አበቅቴን ለማስላት የተለያዩ መንገዶችን መጠቀም እንችላለን።
1/ ወንበርን በጥንተ አበቅቴ/11/ በማብዛት በ30 በግደፍ እና የሚገኘውን ቀሪ መውሰድ ነው።/አስታውሱ፦ ጥንተ አበቅቴ እያልን የምንጠራው ቅዱስ ዲሜጥሮስ በማታ የገባውን ሱባኤ ቀምሮ ያገኘውን ቁጥር ይኸውም 11ን ነው/
ምሳሌ፦ የ2010 ዓም አበቅቴን ለማግኘት
ወንበር * ጥንተ አበቅቴ/30 ከዚህም የሚገኘውን  ቀሪ መውሰድ ነው።
/አስታውሱ፦በባሕረ ሐሳብ ሕግ ዋናው የምንጠወምበት ነገር የሚገኝን ቀሪ ነው።/
4 * 11/30 = 1 ቀሪ 14፣ ይህም ማለት በ2010 ዓም 14 አበቅቴ ወጣ ይባላል።
2/ በአዋጅ መሠረት አበቅቴ እና መጥቅዕ ሁለቱ ሲጨመሩ ሁልጊዜም 30 ስለሚሆኑ ቀድመን መጥቅዕን ካገኘን ከ30 ላይ መጥቅዕን በመቀነስ አበቅቴን መግኘት ይቻላል።
/አዋጅ፦ “አበቅቴ ወመጥቅዕ ክልኤሆሙ ኢየአርጉ እም ሠላሳ፣ ወኢይወርዱ እምሠላሳ፣ ወትረ ይከውኑ ሠላሳ - አበቅቴ እና መጥቅዕ ሁለቱ ተጨምረው ከሠላሳ አይበልጡም፣ ከሠላሳ አያንሱም፣ ሁልጊዜም ሠላሳ ይሆናሉ።”/
ምሳሌ፦ የ2010 ዓም መጥቅዕ 16 ነው።/እንዴት እንደመጣ በቀጣዩ ቀመር እንመለከታለን/
30 – 16 =14 ስለዚህ በ2010 ዓም 14 አበቅቴ ወጣ እንላለን ማለት ነው።
3/ የአሁኑን ዓመት አበቅቴ ካወቅን የሚቀጥለውን ዓመት አበቅቴ ለማግኘት በአሁኑ ዓመት አበቅቴ ላይ ጥንተ አበቅቴን በጨመር ከ30 ቢተርፍ በ30 በመግደፍ የሚገኘው ቀሪ የሚቀጥለው ዓመት አበቅቴ ይሆናል ማለት ነው።
ምሳሌ፦ የ2010 ዓም አበቅቴ 14 ነው። ስለዚህ የ2011ን አበቅቴ ለመፈለግ በዚህ ላይ ጥንተ አበቅቴን ጨምሮ በ30 መግደፍ ነው።
14 + 11= 25፣ ነገር ግን 25 ከ30 ስለሚያንስ እንዳለ እንወስደዋለን ማለት ነው። በዚህም መሠረት በ2011 ዓም 25 አበቅቴ ወጣ እንላለን።
4/ ከምንሠራበት ዓመት በፊት ባለው ዓመት ጨረቃ ዑደቷን ከጨረሰችበት እለት አንስተን እስከዚያው ዓመት ጳጉሜን 5 እለት ያለውን በመቁጠር በ30 ገድፈን የሚገኘው ቀሪ የምንፈልገው ዓመት አበቅቴ ይሆናል ማለት ነው።/ለበለጠ ማብራሪያ የኢትዮጵያ ታላቁ ሀብት ባሕረ ሐሳብ የሚለውን መጽሐፍ ተመልከቱ/

መጥቅዕ †
መጥቅዕ ማለት ጠቅዐ፣ ደወለ ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ደወል ማለት ነው። መጥቅዕ መባሉም ደወል ሲደወል ካህናት ምእመናን ለስብሐተ እግዚአብሔር እንዲሰበሰቡ ሁሉ፣ በመጥቅዕም ተራርቀው የነበሩ በዓላት እና አጽዋማት ይሰበሰባሉ እና ነው። መጥቅዕ ከእለታት እና ከበዓላት ተውሳክ ጋር በመጨመር በዓላትን እና አጽዋማትን የሚያስገኝ ቀመር ነው። መጥቅዕ እንደ ወንበር እና እንደ አበቅቴ ሁሉ በተለያየ መንገድ ሊሰላ ይችላል። እንደሚከተለው ነው።
  1/ ወንበርን በጥንተ መጥቅዕ/19/ በመሰብሰብ የከዚያም የሚገኘውን በ30 በመግደፍ የሚገኘው ቀሪ መጥቅዕ ይባላል። /አስታውሱ፦ ጥንተ መጥቅዕ እያልን የምንጠራው ቅዱስ ዲሜጥሮስ በቀን የገባውን ሱባኤ ቀምሮ ያገኘውን ቁጥር ይኸውም 19ን ነው/
ምሳሌ፦ የ2010 ዓም መጥቅዕን ስንፈልግ
 ወንበር * ጥንተ መጥቅዕ/30 ከዚያም የሚገኘውን ቀሪ ውሰድ
4 * 19/30 = 2 ቀሪ 16 ስለዚህም በ2010 ዓም 16 መጥቅዕ ወጣ እንላለን።
2/ አበቅቴና መጥቅዕ ድምራቸው ሁል ጊዜም 30 ስለሆነ ከ30 ላይ አበቅቴን ቢቀንሱ መጥቅዕ ይገኛል።
3/ የፈለግነውን ዓመት መጥቅዕ ለማግኘት ከፈለግነው ዓመት በፊት ያለው ዓመት መጥቅዕ ላይ ጥንተ መጥቅዕን/19/ በመጨመር ከ30 ቢተርፍ በ30 በመግደፍ የሚገኘው ቀሪ የፈለግነው ዓመት መጥቅዕ ይሆናል ማለት ነው። ይቆየን።
ይቀጥላል።
©ዘዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
መስከረም 28 – 2010 ዓ.ም
ጎንደር/ኢትዮጵያ

ሰኞ 2 ኦክቶበር 2017

††† ባሕረ ሐሳብ-(ክፍል ሁለት)†††


††† ባሕረ ሐሳብ-ክፍል ሁለት†††
      የተዋሕዶ  ልጆች በባለፈው ቆይታችን የባሕረ ሐሳብን ምንነት እና የት መጣ እንዲሁም ማን ደረሰው የሚሉትን ተመልክተናል። ለዛሬ ደግሞ ካቆምንበት በመቀጠል እንማማራለን። የቅዱስ ድሜጥሮስ አምላክ ምስጢሩን ይግለጥልን።
     አዝማናት
      አዝማናት የምንላቸው ሦስት ናቸው። እሊህም ዓመተ ፍዳ/ኩነኔ/፣ ዓመተ ምሕረት እና ዓመተ ዓለም ናቸው።
o   ዓመተ ፍዳ፥ የምንለው ከአዳም በደል እስከ ክርስቶስ በሥጋዌ መገለጥ ድረስ ያለውን የመከራ እና የጭንቅ ዘመን ነው። ይኸውም በቤተክርስቲያን ታሪክ ምሁራን በአራት ይከፈላል። የመጀመሪያው ከአዳም እስከ ሙሴ ያለው ዘመነ አበው ይባላል፡ ደጋጉ ቅዱሳን አበው/the righteous holly patriarchs/ የተነሱበት ዘመን ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ዘመነ መሳፍንት የሚባለው ነው፡ ይኸውም ከሙሴ እስከ ሳዖል ያለው ዘመን ነው። ሦስተኛው ደግሞ ከሳዖልም ጀምሮ ዘመን ዘመነ ነገሥት ይባላል። እነ ቅዱስ ዳዊትን የመሳሰሉ ነገሥታት የተነሱበት ዘመን ነው። አራተኛው ዘመን ደግሞ እስከ ቅዱስ ዮሐንስ ዘመን ያለው ዘመን ዘመነ ካህናት ይባላል። ጌታችንና ፈጣሪያችን ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደውም በዚህኛው ዘመን ነው።
o   ዓመተ ምሕረት፥ የምንለው ደግሞ ከተወዳጁ ቤዛችን እና ሕይወታችን በሥጋዌ መገለጥ አንስቶ እስከ ዓለም ፍጻሜ ያለው ዘመን ነው። ይህም በውስጡ በቤተክርስቲያን ታሪክ ምሁራን የተከፋፈሉ አዝማናት ያሉ ሲሆን ከነዚህም መኻከል ዘመነ ሐዋርያት፣ ዘመነ ተላውያነ ሐዋርያት፣ ዘመነ ሊቃውንት፣ ዘመነ ሰማእታት የሚባሉት ይገኙበታል።
o   ዓመተ ዓለም፥የምንለው ደግሞ የዓለምን መላ እድሜ የሚናገር ዘመን ነው። ይኸውም ከላይ የተመለከትናቸው ሁለት አዝማናት ሲጨመሩ የሚገኘው ውጤት ነው።



ዓመተ ፍዳ + ዓመተ ምሕረት= ዓመተ ዓለም
     መስፈርታት
      በዓለሙ የጊዜ መለኪያ ተብለው ሴኮንድ፣ ደቂቃ፣ ሰዓት እየተባለ እንደሚቆጠረው ሁሉ ቤተ ክርስቲያናችንም የራስዋ የሆነ ዘመናትን እስከ ቅጽበት ድረስ እንኳን የምትሰፍርባቸው መስፈርታት አሏት። እሊህም እለት፣ ኬክሮስ፣ ካልኢት፣ ሣልሲት፣ ራብኢት፣ ኃምሲ እና ሣድሲት የሚባሉት ናቸው።
t       በአጠቃላይ ስድስት መስፈርታት ያሉ ሲሆን እሊህም ያላቸው ግንኙነት እንደሚከተለው ነው።
ኬክሮስ-  60 ኬክሮስ=1 እለት ነው
ካልኢት- 60 ካልዒት=1 ኬክሮስ ነው
ሣልሲት- 60 ሣልሲት=1 ካልዒት ነው
ራብዒት- 60 ራብዒት=1 ሥልሲት ነው
ኃምሲት- 60 ኃምሲት=1 ራብዒት ነው
ሳድሲት- 60 ሳድሲት=1 ኃምሲት ነው /ጳጉሜን ከተሰኘው ጦማር/
      እኒህም መስፈርታት አዝማናቱን በትክክል ለመለካት የሚያገለግሉን ናቸው።

     አዕዋዳት
      ዐውድ ማለት ዙሪያ፣ ክበብ፣ ከበር እስከ በር ካመት እስካመት ያለ፣ ለተወሰነ ክበብ ሁሉ የሚነገር ነው።በብዙ ቁጥር ሲነገር አዕዋዳት ይባላል።/ኪ..ክ/
      ዓመተ ዓለም መቁጠሪያ መስፈሪያ የሚሆኑ ሰባት አዕዋዳት አሉ። እነርሱም ዐውደ እለት፣ ዐውደ ወርኅ፣ ዐውደ ዓመት፣ ዐውደ አበቅቴ፣ ዐውደ ፀሐይ፣ ዐውደ ማኅተም እና ዐውደ ቀመር ናቸው።

1/ዐውደ እለት፥ ከእለተ እሑድ ጀምሮ እስከ ቀዳሚት ባሉት ሰባት እለታት እየተመላለሱ ዐውደ ወርኅን ያስገኛሉ።
2/ዐውደ ወርኅ፥ በፀሐይ ዘወትር በ30 እለት በመመላለስ ዐውደ ዓመትን ያስገኛል። በጨረቃ ደግሞ አንድ ግዜ 29 አንድ ግዜ ደግሞ 30 እለት ይሆናል። ይኸውም ፦ 1ኛ/ መስከረም 2ኛ/ ጥቅምት 3ኛ/ ኅዳር 4ኛ/ ታኅሳስ 5ኛ/ ጥር 6ኛ/ የካቲት 7ኛ/ መጋቢት 8ኛ/ ሚያዝያ 9ኛ/ ግንቦት 10ኛ/ ሰኔ 11ኛ/ ሐምሌ 12ኛ ነሐሴ 13ኛ ጳጉሜን ናቸው።
3/ዐውደ ዓመት፥ ይኽም በፀሐይ 365 እለት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልኢት ሲሆን በጨረቃ ደግሞ 354 እለት ከ22 ኬክሮስ ነው። ከፀሐይ ወሮች አጽፈ ወርኅ ከጨረቃ ወሮች ደግሞ ሕጸጽ ይገኛሉ።
ዐውደ ጳጉሜን በማለት የሚጠራ በየአራት አመቱ የሚዘዋወረውን የጳጉሜን ስድስት መሆን የሚያሳይ ዑደር ቢኖርም አበይት የምንላቸው ግን ከላይ የተናገርናቸው ናቸው።
4/ዐውደ አበቅቴ፥ ይኸውም በ19 ዓመት አንድ ጊዜ እየዞረ የሚከሰት ሲሆን ሁነቱም ፀሐይ እና ጨረቃ ልክ እንደተፈጠሩ ሁነው በአንድ መስኮት ተራክቦ የሚያደርጉበት ነው። ይህም ማለት በ19 ዓመት አንድ ጊዜ ዐውደ ዓመታቸውን እኩል መስከረም 1 ይጀምራሉ ማለት ነው።
5/ዐውደ ፀሐይ፥ ይህ ደግሞ በየ28 ዓመት አንዴ እየዞረ የሚመጣ ነው። በዚህም ዐውድ፣ ወንጌላዊ እና እለት ይገናኛሉ። ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ሲሆን እለቱ ደግሞ ረቡዕ ነው።
6/ዐውደ ማኅተም፥ ማኅተም ማለት አኅተመ ዘጋ፣ ፈጸመ ካለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን በዚህም አገባብ መጨረሻ የሚል ትርጉም ይሰጠናል።ይህ ዐውድ በ76 ዓመት አንድ ጊዜ እየዞረ የሚመጣ ነው። በዚህም ዐውድ፣ አበቅቴ እና ወንጌላዊ ይገናኛሉ። አበቅቴው 18 ሲሆን የአበቅቴዎች ሁሉ ፍጻሜ እንደሆነ፣ ወንጌላዊውም ቅዱስ ዮሐንስ ለወንጌላውያን መጨረሻ ነው።
7/ዐውደ ቀመር/አቢይ ቀመር/፥ ይህ ዐውደ  ደግሞ በየ532 ዓመት አንድ ጊዜ የሚዖድ ሲሆን በዚህ ዐውድ ደግሞ እለት፣ አበቅቴ እና ወንጌላዊ ይገናኙበታል። እለቱ ሰኑይ፣ አበቅቴው 18 እና ወንጌላዊው ደግሞ ዮሐንስ ነው። አውዱ በዘመነ ማቴዎስ እለተ ሠሉስ ላይ አንድ ብሎ ይጀምር እና ከ532 ዓመታት በኋላ እለተ ሰኑይ ላይ በዘመነ ዮሐንስ ይፈጽማል።
     ዓመተ ወንጌላውያን
      ይህ ቀመር ዓመተ ዓለምን በዓውደ  ጳጉሜን በመግደፍ የሚገኘውን ቀሪ በመውሰድ የሚገኝ ነው። ይኸውም ማለት ቀሪው፦
1 ቢሆን ዓመቱ ዓመተ ማቴዎስ ይሆናል
2 ቢሆን ዓመቱ ዓመተ ማርቆስ ይሆናል
3 ቢሆን ዓመቱ ዓመተ ሉቃስ ይሆናል
0 ቢሆን/ያለቀሪ ቢካፈል/ ዓመቱ ዓመተ ዮሐንስ ይሆናል ማለት ነው። ከዚህ በኋላ ግን ለአራት ስትካፈል የተገኘችው ድርሻ መጠነ ራብዕት ትባላለች። ትርጉሙም ለአራት ተካፍሎ የተገኘ ድርሻ እንደማለት  ነው። ይህንም እለተ ዮሐንስን ስንፈልግ የምንጠቀምበት ነው።
     እለተ ዮሐንስ
      ይህ ቀመር ደግሞ መስከረም 1 እለት የሚውልበትን እለት የምናውቅበት ቀመር ነው። ይህንም ለማግኘት መጠነ ራብእትን ከዓመተ ዓለም ጋር በጨመር በ7 መግደፍ ከዚያም የሚገኘውን ቀሪ መውሰድ ነው። ይኸውም ተካፍሎ የሚገኘው ቀሪ፦
1 ቢሆን እለቱ ሠሉስ ይሆናል
2 ቢሆን እለቱ ረቡዕ ይሆናል
3 ቢሆን እለቱ ሐሙስ ይሆናል
4 ቢሆን እለቱ አርብ ይሆናል
5 ቢሆን እለቱ ቀዳሚት ይሆናል
6 ቢሆን እለቱ እሐድ ይሆናል
0 ቢሆን/ያለቀሪ ቢካፈል/ እለቱ ሰኑይ ይሆናል ማለት ነው።
      እለተ ዮሐንስ የምጀምረው ከሠሉስ ነው። ምክንያቱም ጥንታትን ስንነጋገር ጥንተ እለት ሠሉስ መሆኑን ተናግረናል። መስከረም 1 እለት እለተ ዮሐንስ መባሉም ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በብሉይ ኪዳን እና በሐዲስ ኪዳን መሸጋገሪያ ላይ የተገኘ ነቢይ ወሰማዕት ነው፤ መስከረም 1 እለትም የአዲስዘመን መቀበያ የዘመን መሸጋገሪያ ስለሆነ እለት ዮሐንስ ይባላል።
                                                                    ይቆየን።
ምንጭ፦ ባሕረ ሐሳብ በአለቃ  ያሬድ ፈንታ
           -የኢትዮጵያ ታላቁ ሀብት ባሕረ ሐሳብ 
                                                ይቀጥላል። 
                  ©ዘዲያቆን መልአኩ ይፍሩ 
                መስከረም 22 2010 .
                  ጎንደር/ኢትዮጵያ