ሰኞ 27 ፌብሩዋሪ 2017

ሠለስቱ አርእስተ ኃጣውዕ ክፍል ሦስት-ትዕቢት

ማቴ4፡4”ወእምዝ ነሥኦ ወወሰዶ ውስተ ቅድስት ሀገር-ከዚህ በኋላ ወደ ቅድስት ሃገር ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደው”

በዚህም በሁለተኛው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዲያብሎስን የልቡን ሀሳብ አውቆ በበጎ ፈቃዱ ሄደለት እንጂ እሱስ ይወስደው ዘንድ እንደምን ይችላል። ፈቃዱን አውቆ ሄደለት ለማለት ቅዱስ ማቴዎስ “ወወሰዶ” አለ እንጂ።
በሀሳቡም “ካህናትን ድል በማልነሳበት በገዳም ቢሆን ድል ነሳኝ እንጂ ካህናትን ድል በምነሳበት በቤተመቅደስ ቢሆን መች ድል ይነሳኝ ነበር” ብሎ ማሰቡን አውቆ ሄደለት።

“ወዓቀሞ ውስተ ተድባበ ቤተመቅደስ ወይቤሎ እመሰ አማን ወልደ እግዚአብሔር አንተ ቅንጽ እምዝየ ወተወረው ታሕተ- በቤተመቅደስ ጫፍ አቀመው አንተ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ከዚህ ዝለልና ራስህን ወደታች ወርውር አለው”
† ሰይጣን በቀደመው ፈተናውም በዚህም ፈተና ላይ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ እያለ ይናገራል። ምክንያቱ እንደቀደመው ፈተና ነው። ዳግመኛም ሰይጣን ከሰማይ የተሰማውን የአብን እና ከምድር ደግሞ የዮሐንስን ምስክርነት ቢሰማም ቅሉ ሲራብ በማየቱ ግራ ተጋብቶ ነበር። ቢሆንም ግን ሽንፈትን ስለማይወድ ዳግመኛ ይህን ፈተና ይዞ ቀደበ። ይህንም ፈተና ያመጣው
“ቢሰበር አርፈዋለሁ ባይሰበር ምትሐት ነው አሰኝበታለሁ ብሎ
ዳግመኛም ቢያደርገው ሌላጾር እሻበታለሁ(አመጣበታሁ)ብሎ
ዳግመኛም ቢያደርገው የሰይጣን ተአዛዚ አሰኘዋለሁ ባያደርገው
ድካሙን አይቼ እገባበታለሁ ብሎ”
† ተወዳጆች ሆይ ሰይጣን ሁልጊዜም በአንድ ጾር ሲፈትነን በዚያ ከጣለን በኋላ አርፎ እንደማይቀመጥ ከዚህ ልብ ልንል ያስፈልጋል። የወደቀ ዛፍ ምሣር ይበዛበታል እንዲሉ አበው በወደቅንበት የመነሳት አቅም እንስካናገኝ ድረስ በጾር ላይ ጾር እየደራረበ ያደክመናል።

† ዲያብሎስ ሁለተኛውን ፈተና ሲያቀርብ ዝም ብሎም ያለድጋፍ አልነበረም። ለርሱ ያግዘኛል ብሎ ያሰበውን የቅዱስ ዳዊትን መዝሙር ጠቅሶ ነበር።
“እስመ ጽሑፍ ከመ ለመላእክቲሁ ይኤዝዞሙ በእንቲአከ ከመ ይእቀቡከ በኩሉ ፍናዊከ ወበእደዊሆሙ ያነስኡከ ከመ ኢትትዐቀፍ በዕብን እግረከ- መላእክቱን ስለአንተ ያዝዝልሃል በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ እግርህም እንዳይሰናከል በእጆቻቸው ያነሱሃል ተብሎ ተጽፏል አለው” (መዝ 90(91)፡11)

† ሁለተኛውን ፈተና ሰይጣን ሲያመጣ ጌታችንን ወደየት እንደወሰደው ልብ ማለት ያሻል። ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ቤተመቅደስ እንደወሰደው ይነግረናል። ሰይጣን እኛን ከመንፈሳዊ ተጋድሎ ለማስወጣትና ለመጣል ሲፈልግ ክፋትን ብቻ እያሠራ አይደለም በጎ ምግባራትን ወደመሥራት ሊወስደንም ይችላል። ፈተናዎችም ሲመጡብንና ስንደክም በዚያ በደከምንበት ሰዓት እንኳን ንስሐ እንዳንገባ አመክንዮ(ምክንያት) እየደረደረ በጥቅስ እያስደገፈ ሊያደክመን ይቃጣልና በማስተዋል እንራመድ።
“ወአውሥአ እግዚእ ኢየሱስ ወይቤሎ ካዕበ ጽሑፍ ከመ ኢታመክሮ ለእግዚአብሔር አምላክከ- ጌታ አምላክህ እግዚአብሔርን አትፈታተነው ተብሎ ተጽፏል በማለት መለሰ” በትዕቢት የመጣበትን ፈተና በታላቅ ትሕትና ድል ነሳልን።

† ትዕቢት ከእኔ በላይ ማን አለ፤ እኔ ነኝ ያለሁት፤ ማን ይልቀኛል ማለት ነው። ትዕቢት ብዙዎችን የጥቀመች በመምሰል እያታለለች ከመንግሥተ እግዚአብሔር ተለይተው እንዲጣሉ ያደረገች ጾር ናት።አስቀድሞም አዳም ከገነት እንዲወጣ ያደረገችው ታላቅ ጾር ናት። አዳም የተሰጠውን ታላቅና ድንቅ ክብር ቢያውቅ ቢያስተውል እና በትዕቢት ረሱን ከፍ አድርጎ ለርሱ ያልተገባውን ነገር ባያስብ፤ የታዘዘውን ትዕዛዝ ባያፈርስ ባልሞተም ነበር። በትዕቢት የሚኖሩ እና በትዕቢት የሚናገሩ ከናፍር በእግዚአብሔር ዘንድ ፈጽሞ የተጠሉ ናቸው። እግዚአብሔር
አምላክ ትሑት ልብን እንጂ በትዕቢት የተመላ ልቡናን አይወድም። “ጌታ እግዚአብሔር፦ የያዕቆብን ትዕቢት ተጸይፌአለሁ፥ አዳራሾቹንም ጠልቻለሁ ስለዚህ ከተማይቱንና የሚኖሩባትን ሁሉ አሳልፌ እሰጣለሁ ብሎ በራሱ ምሎአል፥”[አሞ ጽ 6፡8] በማለት የእስራኤልን ትዕቢት መጠየፉን ይነግረናል።

† ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴም እንኳን ምድረ ርስትን እንዳይወርስ ያደረገችው ይህችው የትዕቢት ጾር ናት። ትዕቢት ብዙ ቅዱሳንን የፈተነች ብዙ አበውን ለመጣል ደጋግማ የሞከረች ጾር ናት። ፈርኦን እስራኤልን ዘሥጋን አስጨንቆ እያሠራቸው ሳለ እንዲለቃቸው እግዚአብሔር በብዙ ጎዳና አስጠንቅቆት ነበር። እርሱ ግን ትዕቢት በተመላበት አነጋገር “እግዚአብሔር ማነው? ሕዝቡንም አለቅም! ከእኔ እጅ ማን እንደሚያስጥላቸው አያለሁ” አለ። በዚህ ትዕቢቱ ግን ጸንቶ መቆየት አልቻለም። ከነሠራዊቱ በባሕረ ኤርትራ ሰጠመ።

† እንግዲህ ለብዚዎች መውደቅ ምክንያት የሆነችውን ትዕቢትን ገንዘብ ለኛስ ምን ይበጅ ይሆን? እንግዲህ ትዕቢትን በጾም በመጎሰም ራስን ፈጽሞ ትሑት ማድረግ ይገባል። ትሑቱን የክርስቶስን ወታደር አባ መቃርስን ምሳሌ ልናደርግ እንደርሱ ትሐትናን ገንዘብ ልናደርግ ያስፈልጋል። እርሱ ያለኃጢአቱ ያለበደሉ፤ አይቷት እንኳን የማያውቃትን ሴት አንተ ነህ እንድትጸንስ ያደረግኃት ብለው ሲደበድቡት በጸጋ ተቀበለ። ልጁንም ለማሳደግ ይረዳው ዘንድ በራሱ ላይ ትሕርምትን አበዛ። ሰዎቹም እውነቱን ሲደርሱበት ይቅርታ ለመጠየቅ ወደርሱ ሲመጡ እንዳያገኙት በአቱን ጥሎላቸው ሄደ።

† የትሕትና ታላቅ ምሳሌ የሆነችውን ተወዳጇን የመድኅን አለም እናት ወላዲተ አምላክን እናስብ። እርሷ የአምላክ እናት ትሆኛለሽ እየተባለላት እንኳን ራሱን ዝቅ አድርጋ ነበር የምትኖረው። አምላክን ከወለደች በኋላ እንኳን የወለደችው ሁሉ በእጁ የተያዘ የሁሉ ፈጣሪ ሁሉን ማድረግ የሚችል እንደሆነ እያወቀች ሄሮድስ መከራ ባመጣባት ጊዜ ፈጣሪዋን ይዛ ተሰደደች። ይህ እንደምን ያለ ትሕትና ነው። ሁሉን ማድረግ የሚችለውን ጌታ ይዞ ግን መሸሽ፤ መጠማቱንና መራቡን የበረሃውን ዋዕይ ለመጋፈጥ መሰደድ፤ ለዚህ አንክሮ ይገባል። አባ ሕርያቆስም ሲመክረን “እንግዲህ ሞን የምታለብስና ወደሲኦል የምታወርድ ትዕቢትን መታጀልን ጌጥ አናድርግ እንግዲህስ እንደማርያም አርምሞና ትእግስትን ገንዘብ እናድርግ” ብሎ የመሰከረላት።

† ከሁሉም በላይ ግን ማንም የማይተካከለው የትሕትና መምህር መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሁሉ በእጁ የተያዘ እርሱ የፍጡራን ሁሉ ፈጣሪ መጋቢ፤ የሚወስነው የሌለ ሰማይ እና ምድር እንኳን ፍጡራንም ሁሉ ሱራፌልና ኪሩቤል በመንቀጥቀጥና በፍርኃት በፊቱ የሚሰግዱለት እርሱ ድንቅና ታላቁ አምላክ ራሱን ከሁሉ ያነሰ ድሃ ባዶ አደረገ።በሁሉ በተናቀው በበረት ተወለደ። እንደኃጢአተኛ ተቆጥሮ በአደባባይ ለአእምሮ የሚከብድ አሰቃቂ እና ግሩም የሆነ መከራ መስቀልን ተቀበለልን። እንደወንጀለኛ እርቃኑን በቀራንዮ ተራራ ላይ ሰቀሉት። ቅዱሳኑም ይህን እጾብ ድንቅ የሆነ ትሕትና ተመልክተው በማድነቅ እና በመሰቀቅ “ኦ ፍቅር ዘመጠነዝ ፍቅር ኦ ትዕግስት ዘመጠነ ዝ ትዕግስት ኦ ትሕትና ዘመጠነ ዝ ትሕትና” ብለው እያለቀሱ አመሰገኑት።

† ተወዳጆች ሆይ ትሕትና በጸሎት ሕይወታችንም ተመስጦን የምትጨምርልን ልቡናችንን ወደሰማይ ከፍ የምታደርግልን የፍቅር ልጅ፤ የመታዘዝ እናት የሆነች የመንፈስ ፍሬ ናትና ይህችን ታላቅና ድንቅ ጸጋ መድኃኒታችን በቸርነቱ ለሁላችንም ያድለን። የንስሐን ዕንባ ማፍለቅና ከልብ በማልቀስ እዝግዚአብሔርን መቅረብ እንችል ዘንድ ትሕትናን ገንዘብ እናድርግ። ሁልጊዜም ጸሎተ እግዝእትነ ማርያምን እንጸልይ እናስተውል።
“እስመ በትሕትና ይትረከብ ልዕልና”
ለዚህ የቅዱሳኑ ሁሉ እና የድንግል ማርያም ጸሎት የእግዚአብሔር ቸርነት ከሁላችንም ጋር ይሁን። አሜን።
(ይቀጥላል)
መላኩ ዘውሉደ ብርሃን
የካቲት 13-2009ዓ ም
ጎንደር

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ