ሰኞ 27 ፌብሩዋሪ 2017

“ኅቱም በአቢይ መንክር ማኅተም” “ታላቅና ድንቅ በሆነ ማኅተም የታተመ” {ውዳሴ ማርያም ዘዓርብ}

ሉቃስ 1፡34 -37 “ ማርያምም መልአኩን። ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፦ መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ  እግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፥ እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፥ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። ”
ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ የእመቤታችንን እና የመልአኩን ንግግር በጻፈበት ክፍል ስናነብ ከላይ የተጠቀሰውን ምንባብብ
እናገኛለን። ከአራቱ ወንጌላውያን መካከል ሦስቱ {ማቴዎስ፡ ማርቆስ፡ ሉቃስ} የጻፉት ወንጌል የሚያመሳስለው ነገር ቢኖርም
እንኳን አራቱም የየራሳቸው የሆነ ልዩ ጠባይ እና መገለጫም አላቸው።
ቅዱስ ሉቃስም በተለይም የጌታችንን ወልደ እጓለ እም ሕያውነት በስፋት በመግለጥ የጻፈ አባታችን ነው። በዚህም መጽሐፉ እመቤታችንን በቤተመቅደስ ሐርን ከወርቅ አስማምታ ስትፈትል መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ተገልጦ ለሰው ልጆች ሁሉ የሆነውን
ታላቅ የምሥራች አበሠራት።
እመቤታችንም የመውለድን ነገር በልቧ እንደሌለ፤ ልጅ የመውለድን ከልጅም የነገሥታት ንጉሥ የሆነውን እንደምትወልድ
ባበሠራት ግዜ “ወልድ ስለማላውቅ ” አይሆንልኝም ብላው ነበር። መልአኩ ግን ይህ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ እንጅ ተግባረ ዕሩቅ ብእሲ ማለትም በግብረ ብእሲ ወብእሲት{በሴትና በወልድ ግብር} የሚሆን እንዳይደል ዳሩግን በመንፈስ ቅዱስ ሥራ እንደሆነ
ነግሯታል።
ይህንንም ሲነግራት ከዚህ በፊት ያልተደረገ ኋላም የማይደረግ መሆኑን ስላስተዋለ በመጨረሻ ሥራው የእግዚአብሔር መሆኑን በመግለጥ ደመደመው።
የእመቤታችን ድንግልና እና በድንብልና መውለዷን ምን ልዩ ያደርገዋል?
ሀ/ የእመቤታችንን ድንግልና ልዩ የሚያደርገው ነገር
† ንጽሕተ ትንጹሐን ድንግል ማርያም ድንግልናዋ ሥጋዊ ብቻ አልነበረም፤ በሕሊናዋም ጭምር እንጂ። ይህንም
ከራሷ ንግግር በደንብ በማስተዋል ስንመለከት እናገኘዋለን።
 “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?” - በሕግ ተወስኖ ወይም ያለሕግ ግብረ ብእሲ ወብስሲት መፈጸም ከዚህ ቀደምም ሆነ በኋላ በሐሳቧ እንደሌለ በደንብ ያስገነዝበናል። ለዚህም የመጋቤ ሐዲስ ቅዱስ ገብርኤል ንግግር አጽንኦት ይሰጠናል።
“ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ” {ሉቃ 1፡28}
† ዘለአለማዊ፤ የታተመ፤ የማይፈታ፤ ያልተፈታ ድንግልና በመሆኑ። ይህም ሕዝቅኤል በራእዩ {44፡1-3} እንደተመለከተው ሲናገር “ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተ ውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ ተዘግቶም ነበር። እግዚአብሔርም፦ ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፥ ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል።”  ማለት የተመለከተውን ነገር በፍጹም መደነቅ ጽፎልን እናገገኛለን።
† አምላክን ያስገኘ፡ በእግዚአብሔር የተወደደ ንጽሕናና ውበት ያለው ነውና፤
 ቅዱስ ዳዊት በትንቢቱ “ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፥ እርሱ ጌታሽ ነውና።” {መዝሙረ ዳዊት 45፥11} ውበት ብሎ የተናገረው የእማምላክን ሥነ ላህይ{የገጽ ውበት} ብቻ አልነበረም፤ እንደውም በዋናነት ንጽሐናዋን ነው እንጂ።
 ከዚህ ድንግልና የተገኘው አምላክ ወሰብእ መቃብሩን ሳይከፍት እንደተዘጋ ከሞት ተነሳ፤ በዝግ ቤት ውስጠ ምንም ሳይከፍት ገባ {ዮሐ 20፡26} ፤ ምትሐትም እንዳይባል ቅዱስ ቶማስ ተጠግቶ ዳሰሰው። ከዚያም በመፍራትና በመንቀጥቀጥ “ጌታዬ አምላኬም” ብሎ መሰከረ።
ለ/ የእመቤታችን በድንግልና መውለድ
† ከላይ የተናገርነውን ሁሉ ያደረገው አምላክ ስለልደቱ ቀድሞ ሲነገርለት፡-
 “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።” {ኢሳ 7፡14} ተብሎ ተነግሮለት ነበር።
 ኢሳይያስ በትንቢቱ ራሱ ጌታ ስለሚሰጠን ምልክት ተናግሯል። ምልክቱ ምንድነው? ማነው ምልክቱንስ የሚሰጠን?
 ራሱ ጌታ የሰጠው ምልክት እንዴት ያለ ነው?
o ስለዚህ ነገር የኢሳይያስን መጽሐፍ ስናነብ በዚሁ ቀድመን በጠቀስነው ምንባብ ላይ መልሱን ይሰጠናል፤ “ድንግል ትጸንሳለች” በማለት።
o ታዲያ የድንግል መጽነስ ምኑ ያስደንቃል? በዚህች ድንግል መጽነስ ላይ ልዩ የሆነ ነገር ከሌለው በቀር ኢሳይያስ ምልክት ብሎ ያውም ራሱ ጌታ የሚሰጠው ምልክት ብሎ ሊናገርለት እንዴት ይችላል?
o ይህ ምልክት ታላቅ ኃይል የተጎናጸፈ እና ፍጡራንን በእጅጉ ያስደነቀ እስኪሆን ድረስ ከዋክብት እንኳን ፤ ከልደቱ መካን {ሥፍራ} ርሑቅ የነበሩትን ሰብአ ሰገልን እየመሩ እስኪያጡ ድረስ ድንቅ የሆነ ምልክት ምንኛ ድንቅ ነው?
o “ወኃይለ ልዑል ይጼልለኪ፤ የልዑል ኃይልም ይጸልልሻል” ተብሎም በቅዱስ ገብርኤል ተነግሯል። ኃይለ ልዑል የጸለላት {የከለላት፤ የጋረዳት፤ የከለከላት} ከምን ይሆን?
 ከማስኖተ ድንግልና
 ንጽሕት አድርጎ በመጠበቅ {ከኃጣውእ ከለላት}
o ኤልሳቤጥም “ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብጽዕት ናት” ብላ ስለንጽሕናዋ፤ ጌታም ነቢያቱን በማስነሳት ያናገረላትን በመፈጸሙ ንዕድ ክብርት መሆኗን መሠከረች።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እመቤታችን እማማቅድስት ድንግል በክልኤ ማርያም ወላዲተ አምላክ ከንጹሐን ይልቅ ንጽሕት የሆነች፤ በሕይወቷም ለኛ ታላቅ ምሳሌ የሆነችን፤ በድንግልና ጸንሳ በድንግልና ወልዳ መድኃኒትን የሰጠችን ንጽሕት ናትና እርሷን በማክበር እንከብር ዘንድ ከቅዱሳኑ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን። የቅዱሳኑ ሁሉ እና የእማማ ጸሎት አይለየን። አሜን።
ይቆየን!
ዲያቆን መላኩ ይፍሩ ዘውሉደ ብርሃን
ታህሳስ 13 ፤2009 ዓ/ም

ሠለስቱ አርእስተ ኃጣውዕ ክፍል ዐራት-ፍቅረ ንዋይ

ማቴ4፡8”ወእምዝ ነሥኦ ዲያብሎስ ወአእረጎ ውስተ ደብር ነዋኅ- ከዚህም በኋላ ወደረጅም ተራራ አወጣው”

ትርጓሜ ቅዱስ ወንጌል እንደሚነግረን የሰይጣንን የልቡና ፍቃድ ዐውቆ ሄደለት እንጂ እርሱስ የሚወስደው ሁኖ አይደለም። “ነገሥታትን ድል በማልነሳበት በቤተመቅደስ ቢሆን ድል ነሣኝ እንጂ ነገሥታትን ድል በምነሳበት በተራራ ቢሆን መች ድል ይነሳኝ ነበር” ብሎ ማሰቡን ዐውቆ ሄደለት።
“ወአርአዮ መንግሥታተ ኲሉ ዓለም ወኲሉ ክብሮ- የዓለምን ሁሉ መንግሥታት ክብራቸውንም ሁሉ አሳየው”
† ጠጠሩን ወርቅ ብር ቅጠሉን ግምጃ አስመስሎ አሳየው።
† አንድም “መንግሥታተ ኲሉ ዓለም” ግዛቱን ሁሉ አሳየው “ወኲሎ ክብሮ” እንስሳት አራዊቱን ፈረስ በቅሎ ሠራዊት አስመስሎ አሳየው።

ሰይጣን ምንግዜም ቢሆን ውሸታምና የሌለውን አለኝ እያለ የሚያታልል ቀጣፊ ነው። በተአምረ ማርያም ላይ የነበረውን አንድ ነጋዴ እናስታውስ። እጅግ ሃብታም የነበረ አንድ ነጋዴ ነበር። በአንድ ወቅት ግን ንብረቱ ጠፍቶበት አዝኖ ተክዞ በመንገድ መጓዝ ጀመረ። ሰይጣንም ከመንገድ ቆየውና ምን ያስተክዝሃል ቢለው ያለኝ ሁሉ ማስኖብኛል ስለዚህ አዝኛለሁ አለው። ሰይጣንም መልሶ ታዲያ ወደየት ትሄዳለህ አለው። ከእንግዲህ ወዲህስ ከብሬ በነበርኩበት አገር ተዋርጄ ሰጥቼ በኖርኩበት ሀገር ተመጽውቼ አልኖርም ብዬ ወደሌላ ሀገር እየተሰደድሁ ነው አለው።

ሰይጣንም ድንጋዩን ወርቅ አድርጎ አሳየውና ይህን ብሰጥህስ አለው። እርሱም እሺ አለና ተቀበለ። ሰይጣን ግን ተንኮሉን አስከተለ። ነገር ግን አንድ ነገር ልታደርግልኝ እወዳለሁ አለው። ከዚያም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን አምላክ አይደሉም ብለህ ካድልኝ አለው ካደለት፤ ዳግመኛም ቅዱሳንን ሁሉ ካድልኝ አለው። እርሱም ከዚያ ተወውና መመለስ ሲጀምር ቆየኝ አንድ ነገር ቀርቶኛል አለውና ከዚያ “ክርስትያኖች መመኪያችን የሚሏት አለችና እርሷን ካድልኝ” አለው። ያ ሰው ግን ይህንስ አላደርግም አለው። ሰይጣንም እርሷንማ ካልካድክ አምጣ አለና ለውጦ የሰጠውን ደንጊያ መልሶ በርሱ ልቡን ብሎ ገድሎታል። ከዚህ በኋላ ይህ ሰው በአቊራሪተ መዐት ምልጃ በመድኃኒታችንም ቸርነት ሊድን ችሏል። ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ፦
ቁ፦9 “ወይቤሎ ዘንተ ኲሎ እኁበከ እም ከመ ሰገድከ ሊተ ወአማኅከኒ- ብትሰግድልኝና እጅ ብትነሳኝ ይህ ሁሉ እሰጥኃለሁ አለው”
† ልብ በሉ ወዳጆቼ፤ ሰይጣን የቱን ያህል ደፋር እንደሆነ እናስተውል። ሠራዔ ኲሉ የሆነውን አምላክ ስገድልኝና ይህን ልስጠህ አለው። እንደምን ያለ ድፍረትና ትዕቢት ነው።
† መጽሀፈ አክሲማሮስ ይህን የሰይጣንን ትዕቢትና ድፍረት ሲነግረን መላእክት ሲያመሰግኑ እርሱ ዝም አለ
አያመሰግንም። መላእክትም ምነው አታመሰግንም አሉት እርሱም ደፋር ነውና ምን አደረገልኝ ብዬ አመሰግናለሁ። እናንተ ስታመሰግኑ ዐራተኛ እኔን አድርጋችሁ አመስግኑኝ አላቸው።

† በአንድ ጊዜም ለርሱ የወገኑትን መላእክት ከነርሱ ዐራት እንደኪሩብ መርጦ ተሸከሙኝና በሉ ኑ ተነስተን እግዚአብሔርን እንውጋ ብሎ ወደ ሰማይ መውጣት ጀመረ። እግዚአብሔር የልቡን የክፋት ጽናት ተመለከተና ከሰማይ ወደሰማይ ዝቅ እያደረገ ቢያወርደው ጽርሐ አርያምም ብትርቀው እርሱ ግን “እዩ አምላካችሁ አርያሙን ጠቅልሎ ሸሸ” ብሎ ተናገረ።(ሎቱ ስብሐት)
ቁ፦10 “ወእምዝ ይቤሎ እግዚእ ኢየሱስ ሑር እምኔየ ሰይጣን- ከዚህም በኋላ ጌታ ኢየሱስ ሂድ አንተ ሰይጣን ከኋላዬ ወግድ አለው”
† ይህ አቡሃ ለሐሰት የሆነው ሰይጣን አሁን የመጣው ለርሱ በማይገባው በእግዚአብሔር የመለኮታዊ ባሕርዩ ገንዘብ በሆነችው አምልኮት ነውና ወግድ አለው። ምክንያቱም እንዲህ ባለ አኳኋን እና አነጋገር የሚመጣ ባላጋራ ጽኑዕ ባላጋራ ነውና ጽኑዕ ባላጋራዬ ወግድ ሲለው ነው።

† “እምድኅሬየ” በማለትም ከኔ በኋላዬ በሚነሱ ከምእመናን ወግድላቸው ብሎ ሰደደልን።
ቁ፦11 “ወእምዝ ኀደጎ ዲያብሎስ- ከዚህ በኋላ ተወው”
ቅዱስ ሉቃስ እስከጊዜው [በአይሁድ አድሮ እስኪያሰቅለው] ተወው ብሎ ያቀናዋል።

† ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣን በአፍቅሮ ንዋይ በመጣበት ጊዜ በጸሊአ ንዋይ ድል ነስቶታል።
† አፍቅሮ ንዋይ ማለት ገንዘብን አጥብቆ መውደድ ማለት ነው። ገንዘብን ከልክ ባለፈ መጠን መውደድ ለደኃራዊ ሞት[ዳግም ሞት] የሚዳርግ ነው። በአሁኑ ሰዓት በዓለማችን ላይ የብዙዎቹን ተወዳጅ ወንድሞቻችንን ሕይወት ሰይጣን መጫወቻው እያደረገው ያለው በዚህ መንገድ ነው።ትልቅ ትምህርት ይሆነን ዘንድ የሚከተለውን ታሪክ እንመልከት።

† በመጽሃፈ ስንክሣር ጥር 30 ላይ የምናገኘው ታሪክ ነው።
† አንድ ፎላ የሚባል ካህን ነበር። ይህ ካህን ይኖርበት የነበረው ዘመንና ቦታ ጣዖት የሚያስመልክ አረማዊ ንጉሥ የነገሰበት ነበር። በአንድ ወቅት ይህ ካህን በተለያየ ሁኔታ ሰብስቦት የነበረውን ገንዘብ ንጉሡ ይወስድበታል። ካህኑም የተወሰደበት ገንዘብ እንዲመለስለት ይጠይቃል። ንጉሡ ግን ካህኑ ከልጅነታቸው ጀምሮ ያስተማራቸውን እና ያሳደጋቸውን ሁለት ደናግል ለንጉሡ ጣዖት እንዲሠግዱ አሳምኖ ካመጣ እንደሚመልስለት ይነግረዋል።

† ካህኑም በፍቅረ ንዋይ ፈጽሞ ተነድፎ ነበርና ሄዶ እነዚያ ደናግል ለጣዖት እንዲሠግዱ ለማሳመን ብዙ ይጥራል። እነዚያ ደናግል ግን “ቀድሞ ለክርስቶስ ሥገዱ ብለህ አስተምረህን አሁን ደግሞ ለጣዖት ሥገዱ፤ ይህ እንደምን ይሆናል” ብለው እንደማይሰግዱ ነገሩት። ብዙ ቢሞክርም ስላልተሳካለት አስገድዶ ይዟቸው ወደ ንጉሡ ፊት ይዟቸው ቀረበ። ንጉሡም አሳመንሃቸው ብሎ በጠየቀው ግዜ እንዳልቻለ ገለጸለት።

† ንጉሥም ሦስቱም እንዲያዘ አዘዘ። ሁለቱም ደናግል ታሠሩ። ካህኑንም ገንዘቡን እንዳትሰጡት ብሎ አዘዘ። ደናግሉንም አሥረው ከመሰዊያው ቦታ አዘጋጇቸው። ንጉሡ ወደካህኑ ዘወር ብሎ መምህራቸው የሆነውን ያንን ካህን ልጆቹን እርሱ ራሱ ከቀላቸው ገንዘቡን እንደሚሰጡት ነገረው። ተወዳጆች ሆይ ይህ ምን ያህል የገንዘብ ፍቅር የሚያስከፍለውን ዋጋ ተመልከቱ። ይህም ካህን በፍቅረ ንዋይ ዐይነ ልቡናው ታውሮ ነበርና እኒያን ራሱ ስለክርስቶስ አስተምሮ ያሳደጋቸውን ምስኪን ደናግል በሰይፍ ቀላቸው። እነርሱም በገዛ መምህራቸው እጅ ሰማዕትነትን ተቀበሉ።

† ዳሩግን ንጉሡ ይህ ለገዛ ልጆቹ ያልራራ ለኔም ሊመለስ አይችልም ብሎ እርሱንም እዚያው በሰይፍ አስቀላው። እንግዲህ ተመልከቱ ይህ ካህን ወይ ከክህነቱ ወይ ከደናግል የመንፈስ ልጆቹ አለዚያም ከከንዘቡ አልሆነ በሰማይም ሳይጠቀም እንዳረፈ እንደዚያ እንዳይሆንብን እናስተውል።

† ገንዘብን እኛ ሠራነው እንጂ እርሱ አልሰራንምና ለመኖር ለቁመተ ሥጋ ስንል እንሥራ እንብላ እንጂ ኑሯችንን ሁሉ ለገንዘብ አሳልፈን አንስጥ። ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ሁልጊዜም በማስተዋል እያሰብን እንራመድ።
ለጻድቅ አብርሃም ለጻድቅ እዮብ የሰጠውን ማስተዋል እና እምነት የቅዱሳኑ ሁሉ አምላክ ለሁላችንም ያድለን። አሜን።
ይቆየን!
መላኩ ዘውሉደ ብርሃን
የካቲት 17-2009 ዓ ም
ጎንደር

ሠለስቱ አርእስተ ኃጣውዕ ክፍል ሦስት-ትዕቢት

ማቴ4፡4”ወእምዝ ነሥኦ ወወሰዶ ውስተ ቅድስት ሀገር-ከዚህ በኋላ ወደ ቅድስት ሃገር ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደው”

በዚህም በሁለተኛው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዲያብሎስን የልቡን ሀሳብ አውቆ በበጎ ፈቃዱ ሄደለት እንጂ እሱስ ይወስደው ዘንድ እንደምን ይችላል። ፈቃዱን አውቆ ሄደለት ለማለት ቅዱስ ማቴዎስ “ወወሰዶ” አለ እንጂ።
በሀሳቡም “ካህናትን ድል በማልነሳበት በገዳም ቢሆን ድል ነሳኝ እንጂ ካህናትን ድል በምነሳበት በቤተመቅደስ ቢሆን መች ድል ይነሳኝ ነበር” ብሎ ማሰቡን አውቆ ሄደለት።

“ወዓቀሞ ውስተ ተድባበ ቤተመቅደስ ወይቤሎ እመሰ አማን ወልደ እግዚአብሔር አንተ ቅንጽ እምዝየ ወተወረው ታሕተ- በቤተመቅደስ ጫፍ አቀመው አንተ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ከዚህ ዝለልና ራስህን ወደታች ወርውር አለው”
† ሰይጣን በቀደመው ፈተናውም በዚህም ፈተና ላይ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ እያለ ይናገራል። ምክንያቱ እንደቀደመው ፈተና ነው። ዳግመኛም ሰይጣን ከሰማይ የተሰማውን የአብን እና ከምድር ደግሞ የዮሐንስን ምስክርነት ቢሰማም ቅሉ ሲራብ በማየቱ ግራ ተጋብቶ ነበር። ቢሆንም ግን ሽንፈትን ስለማይወድ ዳግመኛ ይህን ፈተና ይዞ ቀደበ። ይህንም ፈተና ያመጣው
“ቢሰበር አርፈዋለሁ ባይሰበር ምትሐት ነው አሰኝበታለሁ ብሎ
ዳግመኛም ቢያደርገው ሌላጾር እሻበታለሁ(አመጣበታሁ)ብሎ
ዳግመኛም ቢያደርገው የሰይጣን ተአዛዚ አሰኘዋለሁ ባያደርገው
ድካሙን አይቼ እገባበታለሁ ብሎ”
† ተወዳጆች ሆይ ሰይጣን ሁልጊዜም በአንድ ጾር ሲፈትነን በዚያ ከጣለን በኋላ አርፎ እንደማይቀመጥ ከዚህ ልብ ልንል ያስፈልጋል። የወደቀ ዛፍ ምሣር ይበዛበታል እንዲሉ አበው በወደቅንበት የመነሳት አቅም እንስካናገኝ ድረስ በጾር ላይ ጾር እየደራረበ ያደክመናል።

† ዲያብሎስ ሁለተኛውን ፈተና ሲያቀርብ ዝም ብሎም ያለድጋፍ አልነበረም። ለርሱ ያግዘኛል ብሎ ያሰበውን የቅዱስ ዳዊትን መዝሙር ጠቅሶ ነበር።
“እስመ ጽሑፍ ከመ ለመላእክቲሁ ይኤዝዞሙ በእንቲአከ ከመ ይእቀቡከ በኩሉ ፍናዊከ ወበእደዊሆሙ ያነስኡከ ከመ ኢትትዐቀፍ በዕብን እግረከ- መላእክቱን ስለአንተ ያዝዝልሃል በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ እግርህም እንዳይሰናከል በእጆቻቸው ያነሱሃል ተብሎ ተጽፏል አለው” (መዝ 90(91)፡11)

† ሁለተኛውን ፈተና ሰይጣን ሲያመጣ ጌታችንን ወደየት እንደወሰደው ልብ ማለት ያሻል። ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ቤተመቅደስ እንደወሰደው ይነግረናል። ሰይጣን እኛን ከመንፈሳዊ ተጋድሎ ለማስወጣትና ለመጣል ሲፈልግ ክፋትን ብቻ እያሠራ አይደለም በጎ ምግባራትን ወደመሥራት ሊወስደንም ይችላል። ፈተናዎችም ሲመጡብንና ስንደክም በዚያ በደከምንበት ሰዓት እንኳን ንስሐ እንዳንገባ አመክንዮ(ምክንያት) እየደረደረ በጥቅስ እያስደገፈ ሊያደክመን ይቃጣልና በማስተዋል እንራመድ።
“ወአውሥአ እግዚእ ኢየሱስ ወይቤሎ ካዕበ ጽሑፍ ከመ ኢታመክሮ ለእግዚአብሔር አምላክከ- ጌታ አምላክህ እግዚአብሔርን አትፈታተነው ተብሎ ተጽፏል በማለት መለሰ” በትዕቢት የመጣበትን ፈተና በታላቅ ትሕትና ድል ነሳልን።

† ትዕቢት ከእኔ በላይ ማን አለ፤ እኔ ነኝ ያለሁት፤ ማን ይልቀኛል ማለት ነው። ትዕቢት ብዙዎችን የጥቀመች በመምሰል እያታለለች ከመንግሥተ እግዚአብሔር ተለይተው እንዲጣሉ ያደረገች ጾር ናት።አስቀድሞም አዳም ከገነት እንዲወጣ ያደረገችው ታላቅ ጾር ናት። አዳም የተሰጠውን ታላቅና ድንቅ ክብር ቢያውቅ ቢያስተውል እና በትዕቢት ረሱን ከፍ አድርጎ ለርሱ ያልተገባውን ነገር ባያስብ፤ የታዘዘውን ትዕዛዝ ባያፈርስ ባልሞተም ነበር። በትዕቢት የሚኖሩ እና በትዕቢት የሚናገሩ ከናፍር በእግዚአብሔር ዘንድ ፈጽሞ የተጠሉ ናቸው። እግዚአብሔር
አምላክ ትሑት ልብን እንጂ በትዕቢት የተመላ ልቡናን አይወድም። “ጌታ እግዚአብሔር፦ የያዕቆብን ትዕቢት ተጸይፌአለሁ፥ አዳራሾቹንም ጠልቻለሁ ስለዚህ ከተማይቱንና የሚኖሩባትን ሁሉ አሳልፌ እሰጣለሁ ብሎ በራሱ ምሎአል፥”[አሞ ጽ 6፡8] በማለት የእስራኤልን ትዕቢት መጠየፉን ይነግረናል።

† ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴም እንኳን ምድረ ርስትን እንዳይወርስ ያደረገችው ይህችው የትዕቢት ጾር ናት። ትዕቢት ብዙ ቅዱሳንን የፈተነች ብዙ አበውን ለመጣል ደጋግማ የሞከረች ጾር ናት። ፈርኦን እስራኤልን ዘሥጋን አስጨንቆ እያሠራቸው ሳለ እንዲለቃቸው እግዚአብሔር በብዙ ጎዳና አስጠንቅቆት ነበር። እርሱ ግን ትዕቢት በተመላበት አነጋገር “እግዚአብሔር ማነው? ሕዝቡንም አለቅም! ከእኔ እጅ ማን እንደሚያስጥላቸው አያለሁ” አለ። በዚህ ትዕቢቱ ግን ጸንቶ መቆየት አልቻለም። ከነሠራዊቱ በባሕረ ኤርትራ ሰጠመ።

† እንግዲህ ለብዚዎች መውደቅ ምክንያት የሆነችውን ትዕቢትን ገንዘብ ለኛስ ምን ይበጅ ይሆን? እንግዲህ ትዕቢትን በጾም በመጎሰም ራስን ፈጽሞ ትሑት ማድረግ ይገባል። ትሑቱን የክርስቶስን ወታደር አባ መቃርስን ምሳሌ ልናደርግ እንደርሱ ትሐትናን ገንዘብ ልናደርግ ያስፈልጋል። እርሱ ያለኃጢአቱ ያለበደሉ፤ አይቷት እንኳን የማያውቃትን ሴት አንተ ነህ እንድትጸንስ ያደረግኃት ብለው ሲደበድቡት በጸጋ ተቀበለ። ልጁንም ለማሳደግ ይረዳው ዘንድ በራሱ ላይ ትሕርምትን አበዛ። ሰዎቹም እውነቱን ሲደርሱበት ይቅርታ ለመጠየቅ ወደርሱ ሲመጡ እንዳያገኙት በአቱን ጥሎላቸው ሄደ።

† የትሕትና ታላቅ ምሳሌ የሆነችውን ተወዳጇን የመድኅን አለም እናት ወላዲተ አምላክን እናስብ። እርሷ የአምላክ እናት ትሆኛለሽ እየተባለላት እንኳን ራሱን ዝቅ አድርጋ ነበር የምትኖረው። አምላክን ከወለደች በኋላ እንኳን የወለደችው ሁሉ በእጁ የተያዘ የሁሉ ፈጣሪ ሁሉን ማድረግ የሚችል እንደሆነ እያወቀች ሄሮድስ መከራ ባመጣባት ጊዜ ፈጣሪዋን ይዛ ተሰደደች። ይህ እንደምን ያለ ትሕትና ነው። ሁሉን ማድረግ የሚችለውን ጌታ ይዞ ግን መሸሽ፤ መጠማቱንና መራቡን የበረሃውን ዋዕይ ለመጋፈጥ መሰደድ፤ ለዚህ አንክሮ ይገባል። አባ ሕርያቆስም ሲመክረን “እንግዲህ ሞን የምታለብስና ወደሲኦል የምታወርድ ትዕቢትን መታጀልን ጌጥ አናድርግ እንግዲህስ እንደማርያም አርምሞና ትእግስትን ገንዘብ እናድርግ” ብሎ የመሰከረላት።

† ከሁሉም በላይ ግን ማንም የማይተካከለው የትሕትና መምህር መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሁሉ በእጁ የተያዘ እርሱ የፍጡራን ሁሉ ፈጣሪ መጋቢ፤ የሚወስነው የሌለ ሰማይ እና ምድር እንኳን ፍጡራንም ሁሉ ሱራፌልና ኪሩቤል በመንቀጥቀጥና በፍርኃት በፊቱ የሚሰግዱለት እርሱ ድንቅና ታላቁ አምላክ ራሱን ከሁሉ ያነሰ ድሃ ባዶ አደረገ።በሁሉ በተናቀው በበረት ተወለደ። እንደኃጢአተኛ ተቆጥሮ በአደባባይ ለአእምሮ የሚከብድ አሰቃቂ እና ግሩም የሆነ መከራ መስቀልን ተቀበለልን። እንደወንጀለኛ እርቃኑን በቀራንዮ ተራራ ላይ ሰቀሉት። ቅዱሳኑም ይህን እጾብ ድንቅ የሆነ ትሕትና ተመልክተው በማድነቅ እና በመሰቀቅ “ኦ ፍቅር ዘመጠነዝ ፍቅር ኦ ትዕግስት ዘመጠነ ዝ ትዕግስት ኦ ትሕትና ዘመጠነ ዝ ትሕትና” ብለው እያለቀሱ አመሰገኑት።

† ተወዳጆች ሆይ ትሕትና በጸሎት ሕይወታችንም ተመስጦን የምትጨምርልን ልቡናችንን ወደሰማይ ከፍ የምታደርግልን የፍቅር ልጅ፤ የመታዘዝ እናት የሆነች የመንፈስ ፍሬ ናትና ይህችን ታላቅና ድንቅ ጸጋ መድኃኒታችን በቸርነቱ ለሁላችንም ያድለን። የንስሐን ዕንባ ማፍለቅና ከልብ በማልቀስ እዝግዚአብሔርን መቅረብ እንችል ዘንድ ትሕትናን ገንዘብ እናድርግ። ሁልጊዜም ጸሎተ እግዝእትነ ማርያምን እንጸልይ እናስተውል።
“እስመ በትሕትና ይትረከብ ልዕልና”
ለዚህ የቅዱሳኑ ሁሉ እና የድንግል ማርያም ጸሎት የእግዚአብሔር ቸርነት ከሁላችንም ጋር ይሁን። አሜን።
(ይቀጥላል)
መላኩ ዘውሉደ ብርሃን
የካቲት 13-2009ዓ ም
ጎንደር

ሠለስቱ አርእስተ ኃጣውዕ ክፍል ሁለት

አስቀድመን በመግቢያው እ ንደተመለከትነው መድኅን አለም ኢየሱስ ክርስቶስ የሄደው ወደበረሃ ነበር። የሄደበትም ዋነኛ ምክንያት አዳም ከዚህች ዓለም በአፍአ በሆነች በገነት በሠለስቱ አርእስተ ኃጣውእ ድል ተነስቷልና ስለዚህ ጌታችንም ከዚህ ዓለም በአፍአ በሆነች በገዳም ድል ይነሳለት ዘንድ ወደ ገዳም ሄደ።
ዳግመኛም የመነኮሳት የባሕታውያን ተጋድሎአቸው ከዚህ ዓለም በአፍአ በሆነ በገዳም በበረሃ ነውና ተጋድሎአቸውን ይባርክላቸው ዘንድ ወደዚያ ሄደ።
ማቴ4፡2 ”ወጾመ አርብአ መዓልተ ወአርብአ ሌሊተ-አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ”
 ሠራዔ ሕግ ነውና ጾምን የመጀመሪያ ሕግ አደረገ። መባልዕት የኃጣውዕ መሠረት እንደሆኑ ሁሉ የበጎ ምግባራት የትሩፋት ሁሉ መሠረት ጾም ናትና።
“እማ ለጸሎት ወእኅታ ለአርምሞ ወለቅዓ አንብዕ ወጥንተ ኲሉ ገድል ሠናይት-የጸሎት እናት እና የአርምሞ እኅት የእንባም ምንጭ የሆነች የበጎ ተጋድሎ ሁሉ መሰረት ናት” እንዲል
 አርባ መጾሙም አስቀድመው አበው ነቢያት አርባ ጹመው ነበርና ከዚያ ቢያተርፍ ወይም ቢያጎድል አይሁድ ምክንያት ፈላጊዎች ናቸውና ደገኛይቱን ሕገ ወንጌልን ከመቀበል ወደኋላ ባሉ ነበር።
አንድም ዛሬ እባብ አካሉ የደገደገበት እንደሆነ አርባ ቀን ከምግብ ተከልክሎ ይሰነብታል። ከዚያም በስቁረተ ዕፅ(በእንጨት ቀዳዳ)በስቁረተ እብንም ቢሉ(በደንጊያ ቀዳዳ) አልፎ ሲሄድ ተገፎ ይወድቅለታል ይታደሳል። እናንተም አርባ ብትጾሙተሐድሶተ ነፍስን ታገኛላችሁ ለማለት ነው።ፍጻሜው ግን አዳም በአርባ ቀኑ ያገኛትን ልጅነት አስወስዷት ነበርና ካሳ መካሱን ለመናገር ነው።
ተወዳጆች ሆይ እርሱ እንዲህ ማድረጉ ለኔ ይጥቀመኝ ይበጀኝ ብሎ አይደለም። ዳሩ ግን ለደካማዎቹ ልጆቹ ለእኛ ሠርቶ አብ ነት ይሆን ዘንድ ነው እንጂ። ስለዚህም እርሱንአብነት አድርገን ጾሙን በተገባ ክርስቲያናዊ ምግባር ልንጾም ያስፈልገናል።
ስስት
ማቴ4፡3 “ ወእምዝ ርኅበ-ከዚህም በኋላ ተራበ”
† አርባ ሌትና መዓልት ከጾመ በኋላ ተራበ ይለናል ቅዱስ ማቴዎስ። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ረኃቡን ቢራብም በበጎ ፍቃዱ በተዋሐደው ሥጋ ነው። እርሱ አምስት ሺህ ሕዝብ የመገበ በብሉይ ለእስራኤል ዘሥጋ መናን ከሠማይ ያወረደና የመገበ፤አዕዋፍን ሳይዘሩ ሳያጭዱ ሳያከማቹ እርሱ አኃዜ ኲሉ የሚመግባቸው ለሁሉ ፍጥረት አስተካክሎ የሚመግብ እርሱ አኃዜ ዓለማት በእራኁ እንደምን ተራበ ለዚህስ አንክሮ ልባዌ ይገባል።
“ወቀርበ ዘያሜክሮ-የሚፈትነውም ቀረበው”
† ፈታኝ የተባለ ዲያብሎስ ወደርሱ እንደምን ሊቀርብ ቻለ? ቀድሞውኑ በጾሙ ጊዜ ስለምን ወደርሱ አልቀረበም ያልከኝ እንደሆን ጾምስ ሰይጣንን ክፉኛ የምታርቀው ሰይፍ የምትከለክለው ቅጽር እንደሆነች ቅዱስ ዮሐንስአፈወርቅን ምስክር አድርጌ እነግርሃለሁ። ቀድሞ በጾሙ ጊዜ ወደርሱ ባለመቅረቡ ጾም እንዴት ፍቱን የጾር መድኃኒት እንደሆነከዚህ ላይ ልብ ይሏል።
† በረሃቡስ ጊዜ እንዴት አውቆ ሊቀርበው ቻለ ትለኝ እንደሆን ይህማ ተራብሁ ሲል ቢሰማው ፍሬ ሲሻ ቢመለከተው ገጹን አጸውልጎ ቢታየው እንደተራበ ተረድቶ ቀረበው። ተወዳጅ ሆይ በዚህም ሰይጣን አንተ የልብህን አሳብ አውጥተህ ካልነገርከው በቀር አሳብህን እንዳያውቅብህ እወቅ። አንተ በተናገርህ ጊዜ ግን መድከምህን እና የደከምህበትን ቦታ ስላወቀ በደስታ ፈትኖ እንዲጥልህ ልብ በል።ጌታም ይህን ትምህርት እንድንወስድ እና እንድናስተውል ተራበ።
ሰይጣንም ወደርሱ ቀርቦ “እመሰ ወልደ እግዚአብሄር አንተ በል ከመ እላ አዕባን ኅብስተ ይኩና-አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ እነዚህን ደንጊያዎች እንጀራ ይሁኑ ብለህ እዘዝ አለው”
† ሰይጣን ይህን ፈተና ሲያመጣ አስቀድሞ ትርጓሜ ወንጌሉ እንደሚለን በተቀደደ ስልቻ ሁለ ትኩስ ዳቦ አስመስሎ ደንጊያዎችን ይዞ ነበር የቀረበው። የጠየቀውም ፦
 እሺ ብሎ ቢያደርግ የሰይጣን ተአዛዚ አሰኘዋለሁ ብሎ ባያደርገው ደካማ አሰኘዋለሁ ብሎ
 አንድም ቢያደርገው ሌላ ጾር እሻበታለሁ(ሌላ ፈተና አመጣበታለሁ) ባያደርገው ድካሙን አይቼ እገባበታለሁ ብሎ አስቦ ነበር።
† ወዳጆች ሆ ይ ዲያብሎስ ከየት አምጥቶ ወልደ እግዚአብሔር ከሆንክ አለው እንዴት አወቀ ትለኝ እንደሆን ቀድሞ በባህረ ዮርዳኖስ “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር” ያለውን ሰምቶ ነው። ወዳጆቼ አምላካችን በነቢያቱ “ይፈትን ልበ ወኩልያተ” የተባለለት ማእምረ ኅቡአት ስለሆነ ይህን ሐሳቡን አውቆበት የመጣበትን የስስት ፈተና በትዕግስት እንዲህ በማለት ድል ነስቶልናል።
ማቴ4፡4 “ወአውስአ እግዚእ ኢየሱስ ወይቤሎ ጽሑፍ ከመ አኮ በኅብስት ከመ ዘየሐዩ ሰብእ አላ በኲሉ ቃል ዘይወጽእ እም አፉሁ ለ እግዚአብሔር-እርሱም መልሶ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፏል ብሎ መለሰለት”
† ይህም ማለት እግዚአብሔር ዳን ያለው ይድናል ሙት ያለው ይሞ ታል ማለት ነው። ይከውም ይታወቅ ዘንድ ጌታችን አልአዛርን “አልአዛር ውጣ” በማለት አራት ቀን የሞ ላውን ሬሳ ቀስቅሷል። ዳግመኛም በስደቱ ጊዜ የዮሴፍ ልጅ ለእመቤታችን የሄሮድስ ወታደሮች እየመጡባቸው እንደሆነ በነገራት ጊዜ እመቤታችን ስትደነግጥ ጌታችን መልሶ “መልእክቱን መናገርህ በጎ አደረግህ ዳሩ ግን እናቴን ስላስደነገጥሃት እስክመጣ ድረስ ይህን ደንጊያ ተንተርሰህ ቆ የኝ” ብሎት ለፍሱን ከስጋው ለይቶ አሳርፎታል።
† ተወዳጆች ሆይ ስስት ያልተሰጡትን እና የማያገኙትን ነገር መሻት ነው። አዳም ከገነት እንዲወጣ ያደረገውም ዋነኛው አድኡ ፈተና ስስት ነው። ይህ ጾር ብዙዎቻችንን ከመንፈሳዊነት የሚያስወጣን ወንድምን ከወንድሙ አባትን ከልጁ ሀገርንም ከሀገር የሚያጣላእና እስከመጋደል የሚያደርስ ነው።
† ቃየል አቤልን እንዲገድለው ያደረገውም ዋነኛው ነገር ስስት ነው። የተሰጠኝ ይበቃኛል ብሎ ቢቀመጥ እና ለወንድሙ የተሰጠውን በማየት ባይመኝ ወንድሙን ወደመግደል ባልደረሰም ነበር። ስስት ብዙዎችን ከመንግስተ እግዚአብሔር እንዲለዩና እንዲጣሉ ያደረገ ታላቅ ጾር ነው። ዲያብሎስም በትዕቢት እንዲናገርና የሐሰት አባት እንዲባለ ያደረሰችው ስስት ናት።
አምላካችንም ይህን ጾር እንዴት ማሸነፍ እንዳለብንድል ነስቶ በመሥራት አሳይቶናል።
† ተወዳጆች ሆይ ያለኝ ይበቃኛል ማለትን እና ራስን እንዲህ ካለው ጾር በትዕግስት በመግዛት ብጾም እና በሥግደት መበጎሰም ዱሳት መጻህፍትን በማንበብ ልንዋጋው ያስፈልጋል።አምላከ ቅዱሳን ለቅዱሳኑ ሁሉ የሰጠውን የትዕግስት አዕምሮ እና ኃይልን ለሁላችንም ያድለን። የቅዱሳኑ ሁሉ እና የድንግል ማርያም ጸሎት አይለየን። አሜን
የካቲት 12፤2009ዓም
መላኩ ዘውሉደ ብርሃን
ጎንደር

ሠለስቱ አርእስተ ኃጣውዕ ክፍል አንድ መግቢያ

ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፥
ማቴ4፡1
ቅዱስ ማቴዎስ ይህንን የጌታችንን የመጾሙን ነገር መጻፍ ሲጀምር ከዚያ ወዲያ ብሎ ይጀምራል።ለምን እንዲህ በማለት ጀመረ ቢሉ አመክንዮውን ከዚህ ይናገሩታል።አስቀድሞ  በምእራፍ ሦስት ላይ መንፈስ ቅዱ በርግብ  አምሳል እንደወረደ እና ከደመናም የምወደው በርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው እንደተባለ ተናግሯልና ይህ ከሆነ በኋላ ተጠምቆም ከወጣ በኋላ ሳይውል ሳያድር እለቱን መሄዱን ለመናገር ነው።
መንፈስ ወሰደው ማለቱ እንደምን ነው ያሉ እንደሆን መንፈስ ያላት የገዛ ፈቃዱ ናት
ወሶበ ትሰምእ እንዘ ይብለከ ወሰዶ ገዳመ ኢትሐሊኬ ከመ ፍጡርውእቱ አላ መንፈስሰ ሥምረቱ ይእቲ_ገዳም  ወሰደው ሲል በሰማህ ጊዜ ፍጡር እንደሆነ አታስብ መንፈስ ያለው የገዛ ፈቃዱ በጎ ፈቃዱ ነው  እንጂ።እንዲል ።ዳግመኛም  መንፈስ ብሎ መንፈስ ቅዱስ የሚል አብነት ያመጣል።ይህስ ሰማእታትን ለደም ጻድቃንን ለገዳም  እንደሚያነሳሳቸው አነሳሳው ማለት እንዳይደለ ልብ ይሏል። በፈቃድ አንድ መሆናቸውን መናገር ነው  እንጂ።
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የማቴዎስን ወንኤል በተረጎመበት ትምህርቱ በ13ኛው ክፍለ ትምህርት ላይ ጌታችን ይፈተን ዘንድ የፈቀደበትን አመክንዮ እንዲህ ገንጾልናል።
ለእኛ አብነት ይሆነን ዘንድ ሁሉን አድርጎ አሳየን።ወደዚያ ምድረበዳ  ሄዶ ይፈተን ዘንድ ጸንቶ ሂዷል።ስለዚህም የተጠመቀ በኋላ ታላላቅ ፈተናዎችን በጽናት ይቋቋም ዘንድ እንዳለው ለመናገር።
ስለዚህ ክንዶች ተሰጠተውሃልትሰንፍ ዘንድ ሳይሆን ትፈተን ዘንድ ነው እንጂ።ስለዚህ ምክንያት ፈጣሪ ፈተናዎቹ በመጡ ግዜ አልከለከላቸውም ነበር።
1. አንተ እጅግ ጠንካራ እንደሆንህ ለማስተማር
2. ዳግመኛም ታላቅ ጸጋ ቢሰጠን እንኳን በዚያ እንዳትመካ በትሐትና እንድትኖር እኒህ ፈተናዎች አንተን እንዲህ እንድትኖር በኃይላቸው ያደርጉሃል
3. ክፉው ዲያብሎስ ለጊዜው እርሱን እንደካድህ ቢጠራጠርም ከነዚህ አርእስተ  ኃጣውእ የተነሳ ፈጽሞ እንደተውከው እና ከርሱም እንደተለየህ እርግጥ ይሆንለታልና
4. ዳግመኛም ስለዚህ ምክንያት አንተ ብርቱ እና ጠንካራ ትሆን ዘንድ ከብረትም ሁሉ የጠነከርህ ትሆን ዘንድ
5. አምስተኛም ስለተዘጋጀልህ አብትስጦታግልጽ የሆነ እማሬ ታገኝ ዘንድ ነው።
ዲያብሎስ አንተ ከፍ ወዳለ ክብር ተወስደህ ካላየ በቀር በኃይል አያጠቃህምና።ይህም ይታወቅ ዘንድ ለምሳሌ ገና ከጅምሩ አዳምን የፈተነው ታላቅ የሆነውን የተሰጠውን ክብር ተመልክቶ ነው።ዳግመኛም ስለዚሁ ምክንያት  ሲከበርና በሁሉ አምላክ ዘንድ ሲከበር ተመልክቷልና እዮብን ተቃውሞ በርሱ ላይ ተነሳሳበት።
ጌታም ወደፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ ማለቱስ እንደምን ነው ትለኝ እንደሆን ጌታ እንዲሁ ሲሄድ አላየህም ዳሩ ግን ተወሰደ ይላልና። በዚህም እኛ ዘለን ወደፈተና መግባት እንደሌለብን ዳሩ ግን ልንወሰድ እንደምንችል ሲያስተምረን ነው።

ይቆየን
                                               © መላኩ ዘውሉደ ብርሃን


11-06-2009 ዓም