ዓርብ 14 ጁላይ 2017

+++ሞት እና ክርስቲያን+++


+ አስቀድሞ በሰው ባህርይ ያልነበረ በኋላ ግን ሕግን ስለመተላለፍ በሰው ላይ መፍረስ መበስን ለማምጣት የተፈረደ ፍርድ ነበር። ስለዚህም የብሉይ ኪዳን ሰዎች ለመሞት አጅግ ይፈሩና ይጨነቁ ነበር። ከሞቱ በኋላ ወደ አምላካቸው መሄድ የለምና።
+በሐዲስ ኪዳን ቤዛ ዓለም እግዜአብሔር ወልድ በሥጋ ተገልጦ በሞቱ ሞትን ድል አድርጎ በትንሳኤው ብርሃን ከታየን በኋላ ሞት ከዚህኛው የሥቃይና የመከራ ዓለም ወደ አዲሲቱ ምድር ወደ አዲሲቱ ዓለም የምንሳፈርበት መንኮራኩር ሁኗል።
+ ስለዚህም ክርስቲያን የሆነ ወገን ሁሉ ሞትን መፍራት ትቶ እንዲያውም በሞት ላይ "ሞት ሆይ መውጊያህ የታል ሲዖል ሆይ ድል መንሳትህ የታል" በማለት በኩራት ይናገራል። በክርስቶስ ስምም ለመሞት እንደሚታረድ በግ ቢነዱትም እንኳን ልቡን አጽንቶ እየዘመረ ይሞታል።
+ ቅዱስ አግናጥዮስ ሰማዕትነት ወደ ሚቀበልበት ቦታ ከወታደሮቹ በሚቀድም ፍጥነት እየተሽቀዳደመ ይጓዝ ነበር። ምዕመናንም ከፍቅራቸው የተነሳ "እባክህ አትሙትብን " ሲሉት " ወደ ክርስቶስ ከምሄድበት መንገዴ አታከላክሉኝ" ነበር ያላቸው። እንዲያውም እጅግ የሚገርመው የቅዱስ አግናጥዮስ መልስ " እውነት እላችኋለሁ አናብስቱ እንኳን አንበላህም ብለው ቢሸሹ አንዲበሉኝ እጸልያለሁ" ነበር ያለው።
+ ውድ ኦርቶዶክሳውያን ወዳጆቼ ብንሞትም በእምነት ጸንተን በክርስቶስ ስለምንሞት ጌታችን ለአልአዛር እኅቶች እንደነገራቸው ሕያዋን ነንና አጅግ ደስ ይበለን። በምንናፍቃት ርስታችን ከቅዱሳን ጋራ እያመሰገንን ለመኖር እንበቃ ዘንድ የቅዱሳኑ ሁሉ እና የድንግል ማርያም ጸሎት ይርዳን።
አሜን።
ዲ/ን መላኩ ይፍሩ
ሐምሌ 3/2009 ዓ/ም
አዲስ አበባ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ