ሐሙስ 13 ጁላይ 2017

++++ የንስጥሮስን ጥሪ እንሽሽ ++++


"ከፈሪሳውያን ርሾ ተጠበቁ"
/ሉቃ 12፥14/


የተወደዳችሁ ኦርቶዶክሳውያን ወንድሞች እና እኅቶች፡ እንደምን አላችሁ? የእግዜብሔር ሰላም ይብዛላችሁ።
ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ከዘመነ ሐዋርያት አንስታ የክርስቶስን በጎች ተጠንቅቃ ስታሰማራ እና ስትጠብቅ፡ ከመንጎቿ የተለዩትንም የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች በሊቃውንቷ ስትረታና ስትለይ ቆይታለች። እሊህ ተረፈ አርዮሳውያን አሁንም ይህን በጎችን ወደ ኣሚታረዱበት የግፍ ካራ መምራታቸውን አላቆሙም።
በሀገራችንም ኦርቶዶክሳውያን መስለው ዳሩ ግን ፈጽመው ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ማኅበር የተለዩ ፍጹም ከሃድያን የሆኑ የተሐድሶ መናፍቃን ከተነሱ ሰንበትበት ብሏል። ከነዚህም ተረፈ አርዮሳውያን የሆኑ መምህራን ነን ባዮች መካከል ጥቂቶቹን ተመክረው በቀኖናም ሊመለሱ ያልቻሉትን ቤተክርስቲያኒቱ በቅዱስ ሲኖዶስ አውግዛ ለይታለች። እርሷን የማይወክሉ ሁነው ሳለ ዳሩ ግን በርሷ ስም የሚነግዱትንም የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች አዘግታለች።
ይህ አንዲህ ቢሆንም ግን አኒህ የንስጥሮስ ልጆች አሁንም ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ አልቻሉም። በድፍረትም ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ብለው የእምነት መሠረት መግለጫቸውን በይፋ አውጥተው እንደነበር የሚታወስ ነው። ቤተክርስቲያኒቱም ምላሹን በሊቃውንቷ አሰናድታ ለምእመኗ ሁሉ በማሳወቅ አረጋግታለች።

አሁንም ግን እነዚህ ለሥጋቸው ያደሩ ቃለ እግዜብሔርን እንዳሻቸው በመተርጎም የሚነግዱ የሲሞን ልጆች ዳግመኛ ቤተ ክርስቲያኒቱ አዘግታው የነበረውን "ቃለ ዐዋዲ" የተባለ የምንፍቅና መርዝ መርጫ አውታር ዳግመኛ ለመክፈት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።
አንዳንድ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሁለተኛው አውታር መስሏቸው በመከታተል ላይ ያሉ የዋህ ምእመናን አሉና ይህንን ነገር ቤተክርስቲያኒቱ ፈጽማ እንደምትቃወምና እንደማትፈቅድ፡ በመርሐ ግብሩ ላይም የሚጋበዙት ግለሰቦች በሃይማኖት ጉድለት ምክንያት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ተወግዘው የተለዩት እንደ አቶ አሰግድ ያሉት መሆናቸውን፡ በመርሐ ግብሩም ላይ የሚቀርቡት መዝሙራትን ኦርቶዶክሳዊ የሆኑ ለማስመሰል ቢጥሩም ከልባቸው ስላልሆነ የአርዮሳውያኑ ጭፈራ አየገነነባቸው ይወጣባቸዋል። ስለዚህም ይህን ኦርቶዶክሳዊ ያሆነ ጸረ ኦርቶዶክስ አውታር ምእመናን አንዳይከታተሉ አበክረን ልናሳስብ ለቤተሰብ ለጓደኛ ለጎረቤት ልናሳውቅ ያስፈልጋል።


"ከውሾች ተጠበቁ፡ ከክፉዋች ሠራተኞችም ተጠበቁ።" /ፊልጵ 3፥18-19/
የእነቅዱስ ቄርሎስ አምላክ ቤተክርስቲያናችንን እና መንጋዎቿን ይጠብቅልን። ተዋሕዶ ሃይማኖቴ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ፡ ብክድሽም ቀኜ ትክዳኝ። የድንግል ማርያም ልጅ እርሱ ይርዳን።
አሜን።
©ዲ/ን መላኩ ይፍሩ
ሐምሌ 4/ 2009 ዓ/ም
አዲስ አበባ፡ኢትዮጵያ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ