ሐሙስ 27 ጁላይ 2017

+++በዓለ ንግሡ ለቅዱስ ገብርኤል በናትሪ +++

" እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ" /ሉቃ 1፥19/
ውድ ኦርቶዶክሳውያን ወንድም እኅቶቼ እንኳን ለቅዱስ ገብርኤል ቅድስት ኢየሉጣን እና ቅዱስ ቂርቆስን ላዳነበት ዓመታዊ የንግሥ በዓል በሰላም አደረሳችሁ።

+ዛሬ በጅማ ሀገረ ስብከት ሥር ወደ ሚገኘው የናትሪ ደብረ ሠላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተክራቲያን ይዣችሁ ልሄድ ነው።
+ደጆችሽ አይዘጉ ባዘጋጀው መንፈሳዊ ጉዞ ላይ ለአገልግሎት ከየሰንበት ትምህርት ቤቱ ተጋብዘን ተሳትፈን የነበረበት ልዩ ጉዞ ነበር። ከአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ከተነሳን በኋላ በሰበታ አድርገን ጉዟችንን ወደ ጅማ ናትሪ ቅዱስ ገብርኤል አደረግን።
+የጉዞውም ሆነ የማኅበሩ መንፈሳዊ ዓላማ የተዘጉ አቢያተ ክርስቲያናትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማስከፈትና እነዚያንም አገልግሎት ማገልገያ መባዕ አጥተው ዳግመኛ እንዳይዘጉ ለማድረግ የታሰበ ነው።
+ይህን ዓላማ በማንገብ ጉዟችንን ስንጀምር ቀኑ ተቆጥቶ ያኮረፈ ይመስል ነበር። ሰማዩም ፊቱን አጥቁሮብን እንባውን እያነባ ነበር። ከቆይታዎች በኋላ ወልቂጤ ደርሰን የወልቂጤ ቅዱስ ሚካኤል ወገብርኤልን ቤተክርስቲያንን ተሳለምንና ከጉዟችን ትንሽ እረፍተ ወስደን ዳግም መጓዛችንን ቀጠልን።
+ የደቡብን ልዩና እጅግ ማራኪ የተፈጥሮ ገጽታ እየተመለከትን በትዝብትም ብዙ አሰብን። ይህን የመሰለ ድንቅ ለምለም ተፈጥሮ ይዞ የሚራብ ሀገርን ማየት እጅግ ለማመን ይከብዳል። ለነገሩ የአባይንስ ልጅ ውሃ ጠምቶት የለ።
+ ጊቤን እንደተሻገርን የምናገኛት በጂማ ሃገረ ስብከት ሥር ከሚገኙ አቢያተ ክርስቲያናት ውስጥ የምእራፈ ቅዱሳን አበልቲ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ወገብረ መንፈስ ቅዱስ የአንድነት ገዳምን ለመሳለም ወረድን። ቤተክርስቲያኗ በታላቅ ተጋድሎ ውስጥ ካሉ አቢያተ ክርስቲያናት ውስጥ አንዷ ናት። በዚያም ቀጣይ ተተኪ የሚሆኑ የአብነት ደቀመዛሙርት ያሉበት የአብነት ትምህርት ቤትም ያለባት ሲሆን እሊህን ደቀመዛሙርት የሚያስተምሩ ጥቂት መነኮሳት አሉ።
+ ከዚያም አለፍ ብለን ባለፈው ዓመት ሰኔ 8 ቀን ኦርቶዶክሳውያን መምእመናን ሌሊት ለጸሎት ተነስተው ሲሄዱ በአካባቢው ባሉ አክራሪ ሙስሊም ወንድሞች በሰይፍ የተመቱበት ታላቅ የተጋድሎ ቦታ የሆነውን የቁምቢ ቅዱስ ሚካኤልን ለመሳለም ወረድን። ቦታው እውነትም የተጋድሎ እና ታላቅ ሰማዕትነትን የሚጠይቅ ቦታ መሆኑን በዓይኑ ያየ ምስክር የሚሆንበት ታላቅ የተጋድሎ ቦታ ነው።
+ በዚያ ተሳልመን ለእነዚያ ጽኑዓን የተጋድሎ ወንድሞች ማገዣ የሚሆን ገንዘብ ተሰባስቦ ከተሰጠ በኋላ ጉዟችንን ቀጠልን።ንዝህላልነትና ዝለት ለሚያጠቃን አገልጋዮች ሰንበት ተማሪዎች እንዲሁም ምእመናን ታላቅ ምሳሌ የሚሆኑን የተጋድሎ ወንድሞቻችን ናቸው።
+ ከዚያ አለፍ ብለን የዶቢ ቅዱስ መድሐኔዓለምን ለመሳለም ወረድን። የቦታውን ሁኔታ ለተመለከተው በተለይም ታሪኩን ከነዚያ የዋህ ምእመናን አንደበት ለሰማ ሰው ቦታው ያለበትን ተጋድሎና የቤተክርስቲያኗን ችግር በማየት እንባውን መቀጣጠር አይቻለውም።
+ በምእመናኑ ፍጹም ተጋድሎ ጸንቶ የቆመ በመብዓ እጥረት ምክንያት ለአገልግሎት የተቸገረ ቤተክርስቲያን ነው።ይህንን የተመለከተው ዐይናችን እንደምንም እንባውን ከሳግ ጋር እየታገለበት ከልብ በማዘን የቻልነውን መባዕ እና ስጦታ በመስጠት ጉዟችንን ወደ ተነሳንብተ መዳረሻ ወደ ናትሪ ቅዱስ ገብርኤል አደረግን። ናትሪ ከተማ እንደደረስን የከተማዋን ሁኔታ ሲመለከቱ ትንሽ ከተማ ስትሆን በእግዚአብሔር ቸርነት፡ በተጋድሏቸው ጽናት እና በመልአኩ እርዳታ ጸንተው የቆሙ ክርስቲያኖችን ይመለከታሉ።
+ በዚህ ሁኔታ የጅማ ሀገረ ስብከት ትልቅ ክርስቲያናዊ ተጋድሎ ያለበት በማንኛውም ሰዓት ሰማዕትነት በራችንን አንኳኩቶ የሚመጣበት ምእመናን በስጋት የሚኖሩበት ሁኔታ ያለ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።
+ወደ ቤተክርስቲያኑ ስንገባ የማኅበሩ አገልጋይ ወንድምና እኅቶቻችን እግራችንን በማጠብ ተቀበሉን። በዚህ ቤተክርስቲያን ውስጥ ማኅበሩ ፕሮጀክት ኤርጋሞታ ብሎ የሚጠራው በሀገሬው ቋንቋ የሚሰብኩ ደቀ መዛሙርትን የሚያፈራ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት አለ። በዚህም ማኅበሩ ለቤተክህነት ከማስረከቡ በፊት 44 ደቀ መዛሙርትን አፍርቷል። በአሁኑ ሰዓት ግን በቤተ ክህነት አመራር ሥር ነው።
+ማኅበሩ ሌላም ፕሮጀክት ናቡቴ ቁጥር 1 ብሎ የሚጠራው የንብ ማነብ እና የአትክልት ማልማት ሥራ ይሠራል። በዚህም ቤተክርስቲያኑን ራሱን ለማስቻል ያገዘ ፕሮጀክት ነው።
+ ቦታው በዙሪያም ባሉ ሙስሊም ወንድሞች የተከበበ ፈተና የበዛበት ነው። ይህን የማኅበሩን ሥራ ተመልክተን ማኅበሩን ያስፋልን በማለት በልባችን ከመረቅን በኋላ የማታው የአውደ ምሕረት መርኃ ግብር ቀጠለ።
መርኃ ግብሩም እንዳለቀ የማኅሌቱ ሥርዓት ተጀምሮ ከዚያ በረከት ተሳትፈን በዓለ ንግሡን በደመቀ ሁኔታ አከበርን።
+ ስለማኅበሩ እና ስለ ዓላማው ስለሚሠራቸውም ሥራዎች እንዲሁም እንዴት በማኅበሩ ሥራ መሳተፍ እንደሚቻል እንደአምላከ ቅዱሳን ፍቃድ በቀጣይ ጊዜ አካፍላችኋለሁ።
+ እነዚህን አቢያተክርስቲያናት እና ጽኑዓን የተጋድሎ ክርስቲያን ወንድሞች እንድናስባቸው እና በቀጣይ ዓመት ለመጎብኘት የድርሻችንንም ለመወጣት በመመኘት ማስታወሻዬን ልቋጭ።
አምላከ ቅዱሳን ከቅዱሳኑ ሁሉ ረድኤትና በረከት ይክፈለን። ይቆየን።
          

 ፎቶ፡- ቀሲስ ቴዎድሮስ እሸቱ
                 -በኃይሉ ተስፋዬ
©ዘዲያቆን መላኩ
ዲያቆን መላኩ ይፍሩ ዘውሉደ ብርሃን
ሐምሌ 19 /2009ዓ.ም
ጅማ/ ናትሪ

ዓርብ 14 ጁላይ 2017

+++ሞት እና ክርስቲያን+++


+ አስቀድሞ በሰው ባህርይ ያልነበረ በኋላ ግን ሕግን ስለመተላለፍ በሰው ላይ መፍረስ መበስን ለማምጣት የተፈረደ ፍርድ ነበር። ስለዚህም የብሉይ ኪዳን ሰዎች ለመሞት አጅግ ይፈሩና ይጨነቁ ነበር። ከሞቱ በኋላ ወደ አምላካቸው መሄድ የለምና።
+በሐዲስ ኪዳን ቤዛ ዓለም እግዜአብሔር ወልድ በሥጋ ተገልጦ በሞቱ ሞትን ድል አድርጎ በትንሳኤው ብርሃን ከታየን በኋላ ሞት ከዚህኛው የሥቃይና የመከራ ዓለም ወደ አዲሲቱ ምድር ወደ አዲሲቱ ዓለም የምንሳፈርበት መንኮራኩር ሁኗል።
+ ስለዚህም ክርስቲያን የሆነ ወገን ሁሉ ሞትን መፍራት ትቶ እንዲያውም በሞት ላይ "ሞት ሆይ መውጊያህ የታል ሲዖል ሆይ ድል መንሳትህ የታል" በማለት በኩራት ይናገራል። በክርስቶስ ስምም ለመሞት እንደሚታረድ በግ ቢነዱትም እንኳን ልቡን አጽንቶ እየዘመረ ይሞታል።
+ ቅዱስ አግናጥዮስ ሰማዕትነት ወደ ሚቀበልበት ቦታ ከወታደሮቹ በሚቀድም ፍጥነት እየተሽቀዳደመ ይጓዝ ነበር። ምዕመናንም ከፍቅራቸው የተነሳ "እባክህ አትሙትብን " ሲሉት " ወደ ክርስቶስ ከምሄድበት መንገዴ አታከላክሉኝ" ነበር ያላቸው። እንዲያውም እጅግ የሚገርመው የቅዱስ አግናጥዮስ መልስ " እውነት እላችኋለሁ አናብስቱ እንኳን አንበላህም ብለው ቢሸሹ አንዲበሉኝ እጸልያለሁ" ነበር ያለው።
+ ውድ ኦርቶዶክሳውያን ወዳጆቼ ብንሞትም በእምነት ጸንተን በክርስቶስ ስለምንሞት ጌታችን ለአልአዛር እኅቶች እንደነገራቸው ሕያዋን ነንና አጅግ ደስ ይበለን። በምንናፍቃት ርስታችን ከቅዱሳን ጋራ እያመሰገንን ለመኖር እንበቃ ዘንድ የቅዱሳኑ ሁሉ እና የድንግል ማርያም ጸሎት ይርዳን።
አሜን።
ዲ/ን መላኩ ይፍሩ
ሐምሌ 3/2009 ዓ/ም
አዲስ አበባ

ሐሙስ 13 ጁላይ 2017

++++ የንስጥሮስን ጥሪ እንሽሽ ++++


"ከፈሪሳውያን ርሾ ተጠበቁ"
/ሉቃ 12፥14/


የተወደዳችሁ ኦርቶዶክሳውያን ወንድሞች እና እኅቶች፡ እንደምን አላችሁ? የእግዜብሔር ሰላም ይብዛላችሁ።
ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ከዘመነ ሐዋርያት አንስታ የክርስቶስን በጎች ተጠንቅቃ ስታሰማራ እና ስትጠብቅ፡ ከመንጎቿ የተለዩትንም የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች በሊቃውንቷ ስትረታና ስትለይ ቆይታለች። እሊህ ተረፈ አርዮሳውያን አሁንም ይህን በጎችን ወደ ኣሚታረዱበት የግፍ ካራ መምራታቸውን አላቆሙም።
በሀገራችንም ኦርቶዶክሳውያን መስለው ዳሩ ግን ፈጽመው ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ማኅበር የተለዩ ፍጹም ከሃድያን የሆኑ የተሐድሶ መናፍቃን ከተነሱ ሰንበትበት ብሏል። ከነዚህም ተረፈ አርዮሳውያን የሆኑ መምህራን ነን ባዮች መካከል ጥቂቶቹን ተመክረው በቀኖናም ሊመለሱ ያልቻሉትን ቤተክርስቲያኒቱ በቅዱስ ሲኖዶስ አውግዛ ለይታለች። እርሷን የማይወክሉ ሁነው ሳለ ዳሩ ግን በርሷ ስም የሚነግዱትንም የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች አዘግታለች።
ይህ አንዲህ ቢሆንም ግን አኒህ የንስጥሮስ ልጆች አሁንም ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ አልቻሉም። በድፍረትም ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ብለው የእምነት መሠረት መግለጫቸውን በይፋ አውጥተው እንደነበር የሚታወስ ነው። ቤተክርስቲያኒቱም ምላሹን በሊቃውንቷ አሰናድታ ለምእመኗ ሁሉ በማሳወቅ አረጋግታለች።

አሁንም ግን እነዚህ ለሥጋቸው ያደሩ ቃለ እግዜብሔርን እንዳሻቸው በመተርጎም የሚነግዱ የሲሞን ልጆች ዳግመኛ ቤተ ክርስቲያኒቱ አዘግታው የነበረውን "ቃለ ዐዋዲ" የተባለ የምንፍቅና መርዝ መርጫ አውታር ዳግመኛ ለመክፈት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።
አንዳንድ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሁለተኛው አውታር መስሏቸው በመከታተል ላይ ያሉ የዋህ ምእመናን አሉና ይህንን ነገር ቤተክርስቲያኒቱ ፈጽማ እንደምትቃወምና እንደማትፈቅድ፡ በመርሐ ግብሩ ላይም የሚጋበዙት ግለሰቦች በሃይማኖት ጉድለት ምክንያት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ተወግዘው የተለዩት እንደ አቶ አሰግድ ያሉት መሆናቸውን፡ በመርሐ ግብሩም ላይ የሚቀርቡት መዝሙራትን ኦርቶዶክሳዊ የሆኑ ለማስመሰል ቢጥሩም ከልባቸው ስላልሆነ የአርዮሳውያኑ ጭፈራ አየገነነባቸው ይወጣባቸዋል። ስለዚህም ይህን ኦርቶዶክሳዊ ያሆነ ጸረ ኦርቶዶክስ አውታር ምእመናን አንዳይከታተሉ አበክረን ልናሳስብ ለቤተሰብ ለጓደኛ ለጎረቤት ልናሳውቅ ያስፈልጋል።


"ከውሾች ተጠበቁ፡ ከክፉዋች ሠራተኞችም ተጠበቁ።" /ፊልጵ 3፥18-19/
የእነቅዱስ ቄርሎስ አምላክ ቤተክርስቲያናችንን እና መንጋዎቿን ይጠብቅልን። ተዋሕዶ ሃይማኖቴ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ፡ ብክድሽም ቀኜ ትክዳኝ። የድንግል ማርያም ልጅ እርሱ ይርዳን።
አሜን።
©ዲ/ን መላኩ ይፍሩ
ሐምሌ 4/ 2009 ዓ/ም
አዲስ አበባ፡ኢትዮጵያ

+++ ሥሉስ ቅዱስ በአበ ብዙኃን ቤት +++

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
" በቀትርም ጊዜ እርሱ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ የአድባር ዛፍ ተገለጠለት።"
(ኦሪት ዘፍጥረት 18:1)

በወርኃ ሐምሌ በሰባተኛው እለት ከምንዘክራቸው በዓላት መካከል አንዱ ቅድስት ሥላሴ በአብርሃም ቤት የተገለጡበት በዓል ነው። ይህን በዓል ስናከብር የምናስታውሳቸው ዋና ዋና ጉዳዮች አሉ። እሊህም ÷
+እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው የጥምቀት ምሳሌ ግዝረት
+ የሥላሴ በአንድነት እና በሦስትነት ለአብርሃም መገለጥ
+የቅዱሳንን ምልጃ በአጸደ ሥጋ፣ እግዜብሔር ቅዱሳኑን ምንያህል እንደሚወድ እና የሰጣቸውን ቃልኪዳን እንደሚያከብር
እግዚአብሔር አብርሃምን ከመጥራቱ በፊት አብርሃም ጣዖት በመሸጥ ይኖር እንደነበር ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል። አብርሃምም የጣዖታቱን ደካማነት ተመልክቶ ሰባብሮ ከጣለ በኋላ ፈጣሪውን ፍለጋ ወጥቷል። እጅግ ብዙ የደከመ ቢሆንም ግን አብርሃም እግዚአብሔርን በድካሙ ብዛት ሊያገኘው አልቻለም ነበር።
ከዚህ በኋላ አብርሃም "አምላከ ፀሐይ ተናበበኒ-የፀሐይ አምላክ አነጋግረኝ" ብሎ በፊጹም መሻት ቢለምን እግዚአብሔር አነጋገረው። ከወገኖቹም ተለይቶ ይወጣ እና እርሱ ወደ ሚያሳየው ምድር ይሄድ ዘንድ ሲያዘው ምንም ሳያቅማማ ወጣ። በዚህም የተነሳ እግዜብሔር ከአብርሃም ጋር ቃልኪዳንን አደረገ። ዘሩንም እንደምድር አሽዋ እንደሰማይ ክዋክብት እንደሚያበዛለት ቃልኪዳንን ሰጠው።
አብርሃምም ድንኳን ሠርቶ በተመሳቀለ መንገድ እንግዳ እየተቀበለ ሲኖር የመልካም ሥራ ጠላት የሆነው ዲያብሎስ እጅግ የተጎዳ መንገደኛ መስሎ በመገለጥ ጉዳቱንም አብርሃም እንዳደረሰበት አድርጎ በመናገር እንግዶቹን አስቀረበት። አብርሃምም እንግዳ ባለማግኛቱ ሳይበላ ለሦስት ቀን ቆየ። እግዚአብሔርም ለዲያብሎስ ዘለፋ፣ ለአብርሃም ደግሞ ክብርና ፍቅር ሲል በቀትር በመምሬ የአድባር ዛፍ ሥር ተገለጠለት። በሦስት ሽማግሌዎች አምሳል።
አብርሃምም አንድ ጊዜ ጌታዬ አንድ ጊዜ ደግሞ ጌቶች እያለ በብዙና በአንድ እያደረገ ሲጠራቸው እንመለከታለን። ለሚስቱም ሦስት መስፈሪያ ዱቄት በአንድ እንድትለውስ ነግሯት ነበር። ይህም የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት የሚገልጥ ድንቅ አነጋገር ነው።
ከዚህ በኋላም እግዜብሔር በዓመቱ ተመልሶ እንደሚመጣ ሣራም እንደምትወልድ ነገረው። ደም ቆርጣ አርጅታ ስለነበር ሳቀች። ስለዚህም ልጇን ይስሐቅ እንደምትለው ነገራት። እግዜአብሔር ከዚህ ወጥቶ ወደ ሰዶም ባቀና ጊዜ ለአብርሃም የሚያደርገውን ነግሮት ነበር።
" እግዚአብሔርም አለ። እኔ የማደርገውን ከአብርሃም እሰውራለሁን? "
(ኦሪት ዘፍጥረት 18:17)
አብርሃምን ስለሚያደርገው መንገር ለምን አስፈለገው??? መልሱ የአብርሃምን ክብር ለመግለጥና ስለነዚያ ሕዝቦች ማርልኝ ብሎ ይለምነው ዘንድ ነው።
ልክ በመጽሐፈ እዮብ ላይ እነዚያን የእዮብን ወዳጆች እዮብ እንዲማልድላቸው እንደመራቸው። ምክንያቱም ቅዱሳን ሲማልዱ፣
+ የሚማለድለት ሰው ወደ ቅዱሳኑ መጥቶ ሲለምን ይማልዳሉ
+ እግዚአብሔር ራሱ የሚማለድለትን ሰው ወደ ቅዱሳኑ ይመራዋል(መጽሐፈ እዮብ)
+ ከፍጹም ርኅራኄያቸው የተነሳ ይማልዳሉ (እንደ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ፣ እንደእመቤታችን ለበላኤ ሰብዕ)
አንዳንዶች ግን እንዲህ ስለምልጃ ሲነገር እግዚአብሔርን ርኅራኄ አልባ፡ ቅዱሳንን ደግሞ ርኅሩኃን ማድረግ ይመስላቸዋል ልቦና ይስጣቸው። ዳሩ ግን ይህም(ምልጃም) ቢሆን የእግዚአብሔርን የርኅራኄውን ብዛት የምናይበት ነው። በዚያውም ላይ እንዲጸልዩልን የሚያደርጋቸውና ቃልኪዳንም የሚሰጣቸው ርሱ እግዚአብሔር ነው።
አብርሃም ለምልጃ በቆመ ጊዜ በሚያቀርባቸው ነገሮች ሁሉ እግዚአብሔር አብርሃም የጠየቀው የቅዱሳን ብዛት ቢገኙ ሀገሪቱን እንደሚምር ነግሮት ነበር። ከሃምሳ ቅዱሳን አንስቶ እስከ አስር ቅዱሳን ድረስ ለምኖት ነበር። (ዘፍ18፥23-33)
" ይህ ከአንተ ይራቅ፤ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ትገድል ዘንድ፥ ጻድቁም እንደ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፥ እንደዚህ ያለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ። የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ አይፈርድምን?"
(ኦሪት ዘፍጥረት 18:25)
እግዚአብሔር አብርሃምን ለቃልኪዳኑ ምልክት ይሆን ዘንድ የአብርሃም ወገን የሆኑት ሁሉ እንዲገዘሩ ነግሮታል። በዚህም ምልክትነት ሕዝብ ከአሕዛብ፣ ግዙራን ከቆላፋን ይለዩ ነበር። ይህም ለሐዲስ ኪዳኑ ጥምቀት ምሳሌ ነው። በጥምቀት አማኒው ከኢአማኒው እንዲለይ።
ስለዚህም ይህን በዓል ስናከብር እሊህን ዐበይት ነገሮች በማሰብ ይሆን ዘንድ ይገባል። አምላከ ቅዱሳን እንደ አብርሃም ያሉ ደጋግ አበውን ያቆይልን።
የቅዱሳኑ ሁሉ እና የድንግል ማርያም ጸሎት አይለየን አሜን።

 ሥዕለ አድኅኖ መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ገጽ
©ዲ/ን መላኩ ይፍሩ
ሐምሌ 6/ 2009 ዓ/ም
አዲስ አበባ