እሑድ 24 ሴፕቴምበር 2017

††† ባሕረ ሐሳብ †††


ኢትዮጵያ ሀገራችን እጅግ ከምትኮራባቸው ሀብቷ መሀከል አንዱ ነገር የዘመን አቆጣጠሯ እንደሆነ ይታወቃል። ይህም የአሥራ ሦስት ወራት ባለቤት እና በዓላትን በራሷ በትክክለኛው ቀመር እንድታከብር አድርጓታል። የዚህን የአቆጣጠሯን ትክክለኛነት ከቦታው ስንደርስ እንናገራለን። በዚህ ተከታታይ ጦማርም ስለባሕረ ሐሳብ ምንነት፣ ስለስሌቱ፣ እንዲሁም የኛን የዘመን አቆጣጠር ከምን እንደመጣ እና ስለ ትክክለኛነቱ እንማማራለን። በዚህም በዓላትን እና አጽዋማትን ለማውጣት ያህል እንዲረዳን እንጂ ከስፋትና ጥልቀቱ የተነሳ እጅግ ጠልቀን አንነጋገርም። የቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት እና የእግዚአብሔር ቸርነት አይለየን።
የባሕረ ሐሳብ ምንነት †
ባሕረ ሓሳብ ማለት ከሁለት ጥምር ቃላት የተገኘ ሕብረ ቃል ሲሆን ትርጉሙም፤
ባሕር ማለት ዘመን ማለት ነው። “በመዳልው ደለወ ዓለመ ወበመሥፈርት ሰፈራ ለባሕር” እንዲል።
ሐሳብ ማለት ደግሞ ቁጥር ማለት ነው። ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ብፁዓን እለ ተኀድገ ሎሙ ኃጢአቶሙ ወእለ ኢሐሰበ ሎሙ ኲሎ ጌጋዮሙ - ኃጢአታቸው የተተወላቸው በደላቸውንም ያልቆጠረባቸው ንዑዳን ናቸው ” /መዝ 31፡1/በማለት እንደተናገረው ሐሳብ ማለት ቁጥር የሚል ትርጉም ይይዛል።

ባሕረ ሐሳብን ማን ደረሰው †

ባሕረ ሀሳብን ለማወቅ ብዙ አበው የተመኙ እና የደከሙ ቢሆንም የተገለጸው ግን ለእስክንድርያ 12ኛ ሊቀ ጳጳስ ለነበረው ለቅዱስ ድሜጥሮስ ነበር። እርሱም ልክ እንደቅዱስ ሕርያቆስ የቤተክርስቲያን ዕውቀት ያልነበረው ዳሩ ግን መስተገብረ ምድር /ገበሬ/ ነበር። የርሱ አባት እና አጎቱ በዘመነ ሰማዕታት ከኢየሩሳሌም ተሰደው ከባዕድ ሀገር ይኖሩ ነበር። የድሜጥሮስ አባት እንደራኒቆስ ሲባል አጎቱ ደግሞ አስተራኒቆስ ይባላል። ለአስተራኒቆስም ልእልተ ወይን የተባለች መልከመልካም ልጅ ነበረችው። የእረፍቱ ጊዜ ሲደርስም /በዚያ ስፍራ ከነርሱበቀር ሌላው ሁሉ አሕዛብ ነበርና/ “ልጄን ለአሕዛብ እንዳትድራት ብሎት ሞተ”።

ሁለቱም ለአቅመ አዳም ወሔዋን ሲደርሱ እንደራኒቆስ የወንድሙን አደራ በማስታወስ “ለአሕዛብ አጋብቼ ሕንፃ ሃይማኖት ከሚፈርስ ሕንፃ ሥጋ ቢፈርስ ይሻላል” በማለት ልእልተ ወይንን እና ቅዱስ ድሜጥሮስን ያጋቧቸዋል። በሠርጋቸውም እለት ማታ ሥርዓተ መርአት ወመርአዊ እንዲፈጽሙ ከጫጉላ ሲተዉአቸው እነርሱ ግን የወንድማማች ልጆች ስለሆኑ ሩካቤ ለመፈጸም ባለመፈለጋቸው በሐዘን ተውጠው ያለቅሱ ጀመር።

ልእልተ ወይንም “ይህን የሠራህ እኔን ንቀህ ነው ወይስ ተዛምዷችንን” አለችው። እርሱም የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም እንጂ እርሷንም ሆነ ዝምድናቸውን ንቆ አለመሆኑን ነገራት። ከዚህ በኋላ ሁለቱም ተስማምተው እንደባል እና ሚስት መስለው እየኖሩ ነገር ግን በሩካቤ ሳይተዋወቁ እንዲኖሩ ወሰኑ። በንጽሕናም ሲኖሩ መልአከ እግዚአብሔር አንድ ክንፉን ለልእተ ወይን አንድ ክንፉን ለድሜጥሮስ አልብሷቸው ይተኙ እና ጠዋት በርግብ አምሳል በመስኮት ሲወጣ ይታያቸው ነበር።

እንዲህም ባለ የንጽህና ጉዞ 48 ዓመታትን አብረው ከኖሩ በኋላ የእስክንድርያው 11ኛ ሊቀ ጳጳስ ዮልያኖስ የእረፍቱ ጊዜ ደርሶ ነበር እና ከርሱ ቀጥሎ የሚሾመው ማን እንደሆነ ለመንገር ሕዝቡን በቤተክርስቲያን ጠራ። ቅዱስ ድሜጥሮስም ወደእርሻው በገባ ግዜ ያለ ጊዜዋ የደረሰች የወይን ፍሬ አገኘ እና ያችን ለሊቀ ጳጳሱ ይዞ ሄደ። ለጳጳሱም በሰጠው ጊዜ ከርሱ ቀጥሎ እንደሚሾም በሱባኤ ስለተገለጠለት ቅብዓ ሜሮን ቀብቶ ሥርዓተ ጵጵስናን ፈጽሞለታል። ይህ ሲሆን ግን ቅዱስ ድሜጥሮስ አላወቀም ነበር።/የኢትዮጵያ ታላቁ ሀብት ባሕረ ሀሳብ/

ከጥቂት ቀናትም በኋላ ሊቀ ጳጳሱ ሲያርፍ ከርሱ ቀጥሎ ሊቀ ጳጳስ የሚሆነው ቅዱስ ድሜጥሮስ እንደሆነ ነግሯቸው ነበርና መንበር ብቻውን አያድርም በማለት ሂደው በመንበረ ማርቆስ ላይ ሊቀ ጳጳስ እንደሚሆን ነገሩት። እርሱ ግን “እኔ በአንድ በኩል ማይ’ም ገበሬ ነኝ፣ በዚያውም ላይ ሕጋዊ ነኝ። እንዴት በንጹሑ በማርቆስ መንበር ላይ እቀመጣለሁ” ቢላቸውም እነርሱ ግን ግድ አሉትና አስቀመጡት።

ለድሜጥሮስም ቅዳሴ እና መጻህፍት ተገልጠውለት ሕዝቡን ያስተምራቸው ጀመር። ከንጽሕናውም የተነሳ የሕዝቡ ሁሉ ኃጢአት ይታየው ነበር እና አንተ በቅተሀል ተቀበል አንተ ንስሐ ግባ እያለ ይመልሳቸው ጀመር። ሕዝቡም “እርሱ ሚስቱን አቅፎ እየተኛ በንጹሑ መንበረ ማርቆስ ላይ ብናስቀምጠው ጭራሽ ይከልክለን” በማለት በሐሜት ሲጎዱ መልአከ እግዚአብሔር ተገልጾለት ሕዝቡ በሕሜት ስለተጎዳ ንጽሕናቸውን እንዲገልጽላቸው ይነግረዋል። ድሜጥሮስም ሕዝቡ ሁሉ እንጨት እንዲያመጡ ይነግራቸው እና ደመራ አስደመረ።

ከቅዳሴም በኋላ በደመራው እሳት ውስጥ እየተመላለሰ ያጥን ጀመር። ልእልተ ወይንንም ከምቋመ አንስት/ከሴቶች መቆሚያ/ አስጠርቶ “ስፍሒ አጽፍኪ - ልብስሺን ዘርጊ” በማለት ፍሕሙን እያነሳ በልብሷ ላይ ጨመረ እና እየዞረች ለሕዝቡ ሁሉ አሳየች። እርሷም ሆነ ልብሷ ምንም በእሳቱ አልተነኩም ነበር። ድሜጥሮስንም ምንድነው ይህ ነገር አባታችን ብለው ሲጠይቁት ለ48 አብረው ሲኖሩ በግብረ መርአት ወመርአዊ/በተራክቦ/ እንደማይተዋወቁ ሲገልጥላቸው ሕዝቡ ሁሉ በመጸጸት አባ ሥረይ ለነ እያሉ ይቅርታ ጠየቁ። እርሱም “ይፍታ ያንጽሕ ወያስተሥሪ” በማለት የኑዛዜን ሥርዓት ጀመረልን።

ይህም ቅዱስ አባት በመንበረ ጵጵስናው ሳለ አንድ ትልቅ ተምኔት ነበረው። ጾመ ነነዌ ዐቢይ ጾም እና ጾመ ሕዋርያት ከሰኑይ፣ ደብረ ዘይት ሆሳዕና ትንሳኤ እና ጰራቅሊጦስ ከእሑድ፣ ርክበ ካህናት እና ጾመ ድኅነት ከረቡዕ፣ ዕርገት ከሐሙስ እና ስቅለት ከዓርብ እንዳይወጣ ይመኝ ነበር። ምክንያቱም እሊህ በዓላት ለመጀመሪያ ጊዜ የዋሉት በእነዚህ እለት ስለነበር ነው።

እንዲህም እያለ ሲመኝ የታዘዘ መልአክ ወደርሱ መጥቶ በምኞት ብቻ እንደማይሆን ነግሮት ሱባኤ እንዲገባ ይነግረዋል። “ከሌሊቱ 23 ሱባኤ ግባ እና አበቅቴ ይሁንህ፤ ከቀኑ 7 ሱባኤ ግባ እና መጥቅዕ ይሁንህ” ብሎታል። ሌሊቱን አብዝቶ ቀኑን ማሳነሱም ቀኑን የተጣላ ሲያስታርቅ፣ የታመመ ሲጠይቅ እንዲህ ባለው ሁሉ ግብር ስለሚያሳልፍ ነው። ከዚህም ጥንተ አበቅቴ እና ጥንተ መጥቅዕ ይገኛሉ።
 አዋጅ፦ ማንኛውም ቁጥር ከ30 ከበለጠ በ30/በዐውደ ወርኅ/ ግደፈው እና ቀሪውን ውሰድ።
የቀኑን ስናሰላ
አንድ ሱባኤ ማለት ሰባት እለት ነው።
7*7=49 ይህንም በ30 ስንገድፈው 1 ጊዜ ይደርስና  19 ይቀራል። ይህም ጥንተ መጥቅዕ ይባላል። ቀጣይ በምናነሳቸው ሌሎች ቀመሮች ላይ በዓላትን ለማውጣት እና የየዓመታቱን መጥቅዕ ለማውጣት እንገለገልበታለን።
የሌሊቱን ስናሰላ
23*7=161 ይህንም በ30 ስንገድፈው 5 ጊዜ ይደርስና  11 ይቀራል። ይህም ጥንተ አበቅቴ ይባላል። ቀጥለን በምናነሳቸው ሌሎች ቀመሮች ላይ ሌሊትን ለማውጣት እና የየዓመታቱን አበቅቴ ለማውጣት እንገለገልበታለን። ይህም በተለይም ካህናት ጸሎትን ለማሣረግ አሥርቆት የሚያደርጉበት ነው።
ባሕረ ሐሳብን ማን መማር አለበት? †
በጉባኤ ቤት ከመጻሕፍት ጉባኤ ጋር በአንድነት የሚሰጥ ትምህርት ነው። በዚህም ካህን የሆነ ሁሉ በበረሀ ጥላ ሥር እንዳለች ምንጭ የሚያረካ እንዲሆን መማር አለበት። ምክንያቱም በዓላትን እና አጽዋማትን አወጥቶ ለልጆቹ መንገር አለበት እና ነው።
ምእመናንም ቢሆኑ በተለያየ ምክንያት ከሀገር የሚወጡበት አጋጣሚ ስለሚኖር በባዕድ ሀገር ሁነው በዓላትን በአግባቡ ለማክበር እና አጽዋማትን ለመጾም ማወቅ ያስፈልጋቸዋል።

የባሕረ ሐሳብ ስሌት †

የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር የሚጀምረው ከጥንታት ነው። ጥንትነቱም ከፍጥረተ ዓለም፣ ከፍጥረተ ፀሐይ፣ ከፍጥረተ ጨረቃ እና ክዋክብት ነው። ዓለም የተፈጠረበት እለተ እሑድ ጥንተ እለት ይባላል። እንዲህም መባሉ ፍጥረታት መፈጠር የጀመሩበት እለት በመሆኑ ነው።
አዝርዕት እጽዋት እና አትክልት የተፈጠሩበት እለተ ሠሉስ ደግሞ ጥንተ ቀመር ይባላል። ቁጥር የተጀመረበት እለት ስለሆነ ነው።
ፀሐይ ጨረቃ እና ክዋክብት የተፈጠሩበት እለተ ረቡዕም ጥንተ ዖን/ዮን/ በመባል ይታወቃል። ዖን ማለትም ብርሃን ማለት ነው። በመጽሐፍ “ዖን ይእቲ ስማ ለፀሐይ” እንዲል። ይቆየን።
ይቀጥላል።
©ዘዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
መስከረም 14 – 2010 ዓ.ም
አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ

ሐሙስ 21 ሴፕቴምበር 2017

የእሥራ ምእት ወአሠርቱ ዓ.ም በዓላት ወአጽዋማት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
አሜን።
ውድ ወዳጆቼ እንኳን ለ2010 ዓ.ም በሰላም አደረሳችሁ። የባሕረ ሐሳብ ትምህርቱን በተከታታይ ለመጦመር የተቻለኝን ጥረት አደርጋለሁ።
የእሥራ ምእት ወአሠርቱ ዓ.ም ዘመነ ማርቆስ በዓላትና አጽዋማት
1/ ዓመተ ዓለም ማለት የዓለም እድሜ ማለት ነው።
ዓ.ዓ(ዓመተ ዓለም)= ዓመተ ፍዳ + ዓመተ ምሕረት
=5500+2010
=7510 ይሆናል።
2/ ወንጌላዊ ፥ ይህ ቀመር ዓመቱን የሚመግበውን ወንጌላዊ የምናውቅበት ነው።ይህም ከላይ ደምረን ያገግኘነውን ዓመተ ዓለም በ4 መግደፍ(4 እያደረጉ መመደብ) ከዚህም የሚቀረው ቀሪ ወንጌላዊ ይሆናል።
7510/4=1877 ቀሪ 2
ይህ የተገኘው ቀሪ
1 ቢሆን ማቴዎስ ይሆናል
2 ቢሆን ማርቆስ ይሆናል
3 ቢሆን ሉቃስ ይሆናል
0 (ያለቀሪ ቢካፈል ደግሞ) ዮሐንስ ይሆናል

ስለዚህ የ2010 ዓ.ም መጋቢ ወንጌላዊ ማርቆስ ነው ማለት ነው። እዚህ ቀመር ላይ ተካፍላ የተገኘችው ድርሻ መጠነ ራብዕት ትባላለች። ለዐራት ተካፍላ የተገኘች ድርሻ እንደማለት ነው። እርሷም ከዓመተ ዓለም ጋር ተጨምራ እለተ ዮሐንስን ለማስገኘት የምታገለግል ናት።

3/ እለተ ዮሐንስ፥ ይህ ቀመር መስከረም መች እንደሚብት(እንደሚገባ) የሚነግረን ነው። ይህም የሚሰ'ላው መጠነ ራብዕትን እና ዓመተ ዓለምን ደምረው በ7 መግደፍ ከዚያም ቀሪውን መውሰድ ነው።
=7510+1877
=9389 ይህን በ7 ቢገድፉት 1341 ቀሪ 0 ይሆናል።
ቀሪው 0 ቢሆን ሰኑይ
1 " ሠሉስ
2 " ረቡዕ
3 " ሐሙስ
4 " ዓርብ
5 " ቀዳሚት
6 " እሑድ ይሆናል። ቁጥሩም ከሠሉስ 1 ብሎ መጀመሩ በእኛ አቆጣጠር ጥንተ ቀመርን(የቁጥር መጀመሪያ) ሠሉስን ስለምናደርግ ነው ። ስለዚህ የ2010 መስከረም ወር የሚብተው ሰኑይ እለት ነው።

4/ ወንበር፥ መጥቅዕ እና አበቅቴ የሚባሉትን አስልተን ለማግኘት የምንጠቀምበት ቀመር ነው። ይህም የሚገኘው ዓመተ ዓለምን በ19 በመግደፍ ከዚያም ከሚገኘው ቀሪ ላይ "አሐደ አእትት ለዘመን- አንዱን ለዘመኑ ስጠው" በሚለው አዋጅ መሠረት አንድ ስንቀንስ ወንበርን
እናገኛለን።
7510 በ19 ቢገደፍ 395 ቀሪ 5 ይሆናል። ከቀሪው 1 ስንቀንስ 4 ይገኛል። በ2010 ዓ.ም 4 ወንበር ወጣ ማለት ነው።

5/ አበቅቴ፥ ይሄ ቀመር ደግሞ ከሕጸጽ ጋር እየተደመረ ሌሊትን የሚያስገኝ ነው። ስሌቱም
ወንበር× በጥንተ አበቅቴ(11) ከዚህ በኋላ በ30 መግደፍ ከዚያም የሚገኘውን ውጤት ቀሪውን ውሰድ።
= 4×11
= 44 ይህን በ30 ግደፍ። 1 ደርሶ 14 ይቀራል።
ስለዚህም በ2010 ዓ.ም 14 አበቅቴ ወጣ።

አዋጅ ፡
  አበቅቴ እና መጥቅዕ ሁልጊዜም ተደምረው 30
ነው የሚሆኑት።

6/ መጥቅዕ፡ ትርጉሙ ደወል ማለት ነው። ደወል ሲደወል ምዕመናን ካህናት ለጸሎት እንዲሰበሰቡ ሁሉ መጥቅዕም
በዓላቱን ሁሉ ይሰበስባቸዋልና ነው።
ስሌቱም
ወንበር× በጥንተ መጥቅዕ(19) ከዚህ በኋላ በ30 መግደፍ ከዚያም የሚገኘውን ውጤት ቀሪውን ውሰድ።
= 4×19
= 76 ይህን በ30 ግደፍ። 2 ደርሶ 16 ይቀራል። ስለዚህም በ2010 ዓ.ም 16 መጥቅዕ ወጣ።

አዋጅ፥
መጥቅዕ ከ14 በላይ ከሆነ ብዓለ ምጥቅዕ በመስከረም ይውላል፥ መጥቅዕ ከ14 በታች ቢሆን በዓለ መጥቅዕ በጥቅምት ይውላል።
የ2010 ዓ.ም መጥቅዕም በምን እለት እንደሚውል ለማወቅ ከእለተ ዮሐንስ አንስተን መቁጠር ነው። መጥቅዕ 16 ስለሆነ በዓለ መጥቅዑ ጥቅምት ወርኅ ላይ ይውላል።
"መጥቅዕ ከ14 ቢበዛ በመስከረም ንዛ መጥቅዕ ከ14 ቢያንስ ከጥቅምት ዳብስ" እንዲል መስከረም የባተው ሰኑይ ስለሆነ ሰኑይ ለሰኑይ 8፡ ሰኑይ
ለሰኑይ 15 ይሆናል። ሠሉስ 16 ይሆናል። ስለዚህ በዓለ መጥቅዕ ሠሉስ እለት ይውላል። ይህንም ማወቃችን በዓላትን እና አጽዋማትን ለማወቅ የምትረዳንን መባጃ ሐመርን ለማግኘት ይህ ቀመር ስለሚያስፈልገን ነው።

7/ መባጃ ሐመር፥ ቃልነቱ ግእዝ ወይም ሌላ አይደለም። ፍርንዱስ ነው። ይህም ማለት የአማርኛ እና የግእዝ ቃላት ጥምረት ውጤት ነው ማለት ነው። መባጃ 'ባጀ፤ ከረመ' ካለው የአማርኛ ቃል የተገኘ ሲሆን ማክረሚያ ማለት ነው። 'ሐመር' ማለት ደግሞ በግእዝ መርከብ ማለት ነው። ስለዚህም በአጠቃላይ ትርጉሙ ማክረሚያ መርከብ ማለት ነው። ስሌቱም እንደሚከተለው ነው።

መጥቅዕ + በዓለ መጥቅዕ የዋለበት እለት ተውሣክ
ከዚያም የተገኘውን ውጤት በ30 በመግደፍ ቀሪውን መውሰድ። በዓላት እና አጽዋማት የሚውሉበትን እለት ለማወቅ ከበዓላቱ እና ከአጽዋማቱ ተውሳክ ጋር መባጃ ሐመርን በመደመር ከ30 ቢበልጥ በ30 ግደፍ። የቀረውንም ውሰድ። ነነዌ ግን በደረቅ መባጃ ሐመር ትወጣለች።

ትውሣክ፥
ማለት ጭማሪ ማለት ነው። ሁለት ዓይነት ተውሣካትን እንመለከታለን።
የእለታት ተውሳክ፥
ይህ ከቅዳሜ አንስቶ እስከ አርብ የሚቆጠር ሲሆን ቅዳሜን 8 ብሎ ዝቅ እያለ ይቆጥር እና ዐርብ ላይ 2 ይሆናል።
ቀዳሚት 8
እሑድ 7
ሰኑይ 6
ሠሉስ 5
ረቡዕ 4
ሐሙስ 3
አርብ 2 ይሆናል።
ስለዚህም በዓለ መጥቅዕ የዋለው ሐሙስ ስለሆነ ተውሳኩ 3 ይሆናል።

የ2010 ዓ.ም መባጃ ሐመሩንም ስናሰላ
መጥቅዕ + በዓለ መጥቅዕ የዋለበት እለት ተውሣክ፣ ከዚህ የተገኘውም ከሠላሳ ቢተርፍ በ30 ገድፈህ ቀሪውን ውሰድ። የበዓለ መጥቅዕም ተውሳክ፣ ሠሉስ እለት ስለሆነ ተውሳኩ 5 ነው።
16 + 5= 21 ይህም ከ30 ያነሰ ስለሆነ እንዳለው እንወስደዋለን። ስለዚህም በ2010 ዓ.ም 19 መባጃ ሐመር ወጣ።
አዋጅ፤
    1/ በዓለ መጥቅዕ በመስከረም ከዋለ ነነዌ በጥር ትውላለች።
    2/ በዓለ መጥቅዕ በጥቅምት ከዋለ ነነዌ በየካቲት ትውላለች።
    3/ በዓለ መጥቅዕ በመስከረም ውሎ የእለት ተውሳክ እና
መጥቅዕ ሲደመሩ ከ30 ቢተርፍ በ30 ይገደፍና ነነዌ በየካቲት ትውላለች። የበዓላት እና የአጽዋማት ተውሣክ
ነነዌ 0
ዐቢይ ጾም 14
ደብረ ዘይት 11
ሆሳዕና 2
ስቅለት 7
ትንሣኤ 9
ርክበ ካህናት 3
ዕርገት 18
ጰራቅሊጦስ 28
ጾመ ሐዋርያት 29
ጾመ ድኅነት 1

8/ ነነዌ፡ በደረቅ መባጃ ሐመር የምትወጣ ተውሳክ የሌላት ናት። ስለዚህም በ2010 ዓ.ም ነነዌ በጥር 19 ትውላለች ማለት ነው። ከዚህ በታች የቀሩትን በዓላት እና አጽዋማት ለማግኘት ተውሣኩን ከመባጃ ሐመር ጋር መደመር የሚገኘውን ውጤት ከ30 ቢተርፍ በ30 ገድፎ ቀሪውን ወስዶ በቀጣዩ ወርኅ ማዋል ነው። ቀድሞት ከነበረው በዓልም ያነሰ ድምር ከተኘ በቀጣዩ ወር ይውላል።

10/ ዐቢይ ጾም፥
= 21+ 14
= 35 ይህን በ30 ቢገድፉት 1 ደርሶ 5 ይቀራል።
ስለዚህም የ2010 ዓ.ም ዐቢይ ጾም የካቲት 5 ይገባል ማለት ነው።

11/ ደብረ ዘይት፥
= 21+ 11
= 32 ይህንም በ30 ቢገድፉት 1 ደርሶ 2 ይቀራል።
ስለዚህም የ2010 ዓ.ም ደብረ ዘይት መጋቢት 2 ይገባል ማለት ነው።

12/ ሆሳዕና፥
=21 + 2
= 23 ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ሆሳዕና መጋቢት 23 ይውላል ማለት ነው።

13/ ስቅለት፥
= 21 + 7
= 28 ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ስቅለት መጋቢት 28 ይውላል ማለት ነው።

14/ ትንሳኤ፥
= 21 + 9
= 30 ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ትንሳኤ መጋቢት 30 ይውላል ማለት ነው።

15/ ርክበ ካህናት፥ ይህ በዓል ደግሞ ኤጲስ ቆጶሳት
ለቤተክርስቲያን ጉሳይ የሚሰበሰቡበት ነው።
= 21 + 3
= 24 ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ርክበ ካህናት ሚያዝያ 24 ይውላል ማለት ነው።
16/ ዕርገት፥
= 21 + 18
= 39 ይህን በ30 ቢገድፉት 1 ጊዜ ደርሶ 9 ይቀራል። ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ዕርገት ግንቦት 9 ይውላል ማለት ነው።

17/ ጰራቅሊጦስ፥
= 21 + 28
=29 ይህን በ30 ቢገድፉት 1 ጊዜ ደርሶ 19 ይቀራል።
ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ጰራቅሊጦስ ግንቦት 19 ይውላል ማለት ነው።

18/ ጾመ ሐዋርያት፥
= 21 + 29
= 50 ይህን በ30 ቢገድፉት 1 ጊዜ ደርሶ 20 ይቀራል። ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ጾመሐዋርያት ግንቦት 20 ይውላል ማለት ነው።

19/ ጾመ ድኅነት(የዐርብ ረቡዕ ጾም)፥
= 21 + 1
= 22 ስለዚህ የ2010 ዓ.ም ጾመ ድኅነት ግንቦት 22 ይውላል ማለት ነው።
የ2010 ዓ.ም ባሕረ ሐሳብ ደረሰ ተፈጸመ በሰላመ እግዚአብሔር አሜን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።
©ዘዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
አዲስ አበባ/ ኢትዮጵያ
መስከረም 1/ 2010 ዓ.ም