ዓርብ 23 ማርች 2018

+ + + የመነኮሳት ታላቁና ከባዱ ጾር + + +

ምንጭ፥ Paradise of the Holly Fathers by St Athenasius, vol 2, p323
አማርኛ ትርጉም፥ ዲ/ን መልአኩ ይፍሩ ዘውሉደ ብርሃን

አንድ ወንድም እንዲህ አለ" በአንድ ወቅት ማኅበረ መነኮሳቱ የታላቁን የትንሳኤል ክብረ በዓል ለማክበር ተሰባሰቡ፤ በገዳሙም፣ አባቶች በሙሉ ባሕታውያኑ እና ሌሎችም መነኮሳት እንዲሁም በማኅበሩ የተሰባሰቡት ታላላቆቹም አበው ኹሉ እንዲህ ተብለው ተጠየቁ። ' በመነኮሳት ላይ ከሚመጡት ፈተናዎች ኹሉ ታላቁ እና ከባዱ ፈተና የቱ ነው?' ኹላቸውም በአንድነት መነኲሴውን በአቱን ጥሎ እንዲወጣ ከሚያደርገው ጾር የሚበልጥ ከባድ ጾር እንደሌለና ይህንም ያሸነፉት እንደኾነ ሌሎቹ ኹሉ እንደሚቀሉ ተናገሩ። ይህንን አስረዳን"
      አረጋዊውም አባት እንዲህ በማለት መለሰ " በበአት ኹኖ መንፈሳዊ ተጋድሎን መጋደል በዚያው ለመጽናት ተስፋን ይጨምራል፤ ዳሩ ግን ከበአት ተለይቶ መውጣት ፈጽሞ ተስፋ ከመቊረጥ ጋር አንድ ነው። በበአቱ መንፈሳዊ ተጋድሎን እያደረገ እና የበአቱን ጸጥታ ወዶ እስከቆየ ድረስ ጥቂት በጥቂት ወደፊት በየጊዜው አንድ በአንድ ደረጃ ከፍ ይላል። በጌታችንም ኹሉን ጾር ጨርሶ እንደሚያሸንፍ ተስፋ አለው። ስለዚህም በምላሹ እና በተጋድሎው ቅድስናን እና የክርስቶስን ጸጋ ገንዘብ ያደርጋል። ነገር ግን ሕይወት እጅግ ከባድ ኹናበት(ፈተና በዝቶበት) በአቱን ጥሎ ቢወጣ፣ ዓላማ የሌለው ጉዞንም ቢጓዝ ጾሮቹን ድል በማድረግና ታላላቅ መንፈሳዊ ሃብታትን (ቅድስናን) ገንዘብ በማድረግ ፈንታ ተስፋ ከመቊረጥ ከዚያም ከፍጹም ጥፋት (ውድቀት) ይደርሳል። ስለዚህም ዓላማ የለሽ ጉዞን የሚያመጣ (ከመአት የሚያስወጣ) ጾርን የመሰለ ሌላ ከባድ ጾር የለም በማለታቸው አበው በእውነት ተናገሩ"
      ©ዲያቆን መልአኩ ይፍሩ ዘውሉደብርሃን
                   14-07-2010 ዓ.ም
                  አዲስ አበባ/ ኢትዮጵያ

ረቡዕ 21 ማርች 2018

መልካሙ ገበሬ እና መልካሙ እረኛ


በአንድ ድንቅ በኾነ መልካም የገነት(ለምለም፣ የአትክልት )ቦታ የሚኖር እና እጅግ ጠቢብ የኾነ ድንቅ ገበሬ ነበር። በአንድ እለትም ጠቢቡ ገበሬ ዘሩን በዘራ ጊዜ ዘሩ በእሾህ መኻከል፣ በጭንጫ መሬት፣ በመንገድ ላይ እና በመልካም መሬት ላይ ወደቀ። ከእነዚህም መኻከል በመልካም መንገድ ላይ የወደቀው መልካም ፍሬን አፈራ። ለዚህም ጠቢብ ገበሬ እጅግ የሚወደው እና ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንድያ ልጅ ነበረው።

 ይህ ጠቢብ ገበሬ በጎቹን በአግባቡ አሰማርቶ የሚልክ በእረፍት ውሃ፣ በለምለም መስክ የሚመራቸው መልካም እረኛ ነበር። እኒህም በጎች ይህን በጎ እረኛቸውን በመስማት እርሱን እየተከተሉ ይኖሩ ነበር። በአንድ ወቅት አንዲት ፍየል በእነዚህ የበጎች መንጋ ተቀላቅላ ከእነርሱ ጋር ተመሳስላ ትሰማራ ጀመር። በዚህ ኹኔታ ሳሉ ይህች ፍየል የበጎቹን ጎዳና እያስቀየረች የሚመገቡበትን ቦታ አስለውጣ ወደሌላ ጎዳና ይዛቸው ትኼድ ጀመር። እንዲህ ሳሉ አንድ እላት ላይ ወደ በረሐ ይዛቸው ኼደች። በዚህ በረሐ የሚመገቡት ምግብ የሚጠጡትም ውሃ የለም ነበር።

 በዚህም በበረሐው ዋእይና ውሃ ጥም ጸንቶባቸው ይሰቃዩ ጀመር። ይህም መልካም ገበሬ በጎቹ በሰዓታቸው ወደ በረታቸው እንዳልገቡ፣ የኾነባቸውንም ሰምቶ እጅግ ተጨነቀ። አገልጋዮቹንና መልካም ወዳጆቹን ተራ በተራ ላካቸው። ከእነዚህም ከተላኩት በበረሐ ሳሉ ረሃቡ እና ውሃ ጥሙ እንዲኹም ተኲላው እየተፈራረቁ መከራው ጸንቶባቸው የተሸነፉ አሉ። ከነዚህም በበረሐው ዋዕይ፣ በውሃ ጥም ተሸንፈው የቀሩ ነበሩ፤ ከነዚህም የተረፉት በመንገድ ተኲላ የበላቸው ነበሩ። የተቀሩትን ጥቂቶቹን ግን የመንገዱ ርቀትና አቅጣጫውም ጠፍቷቸው እነርሱም ጠፉ፤ ይኸው መልካም ገበሬም የኾነውን ሰምቶ ተጨንቆ ሳለ እጅግ የሚወደውን ጠቢብና አስተዋይ አንድያ ልጁን ላከው።

 ይኸውም ታማኝና አስተዋይ ጠቢብ ልጅ በመንገድ ብዙ ከተጓዘ በኋላ እጅግ ደክሞት ነበር። ከብዙ ስቃይና እንዲሁም ከተኲላ ፈተና ከበረሐ ዋዕይ፣ ውሃ ጥም፣ እንቅፋት ይኽን ኹሉ በጽናት ተቀብሎ የታመነው የጠቢቡ ገበሬ ተወዳጅ ልጅ እንደተራ እረኛ ራሱን ዝቅ አድርጎ በመታዘዝ መንፈስ እኒህን በጎቹን በብዙ ስቃይና መከራ ካለፈ በኋላ አገኛቸው።

 እኒህንም በጎቹን ከተኲላ ተንኮን፣ ከበረሐ ዋዕይ፣ ከውሃ ጥም አድኖ እና ታድጎ በጥላውና በእረፍት ውሃ ጎዳና እየመራ ይዟቸው ወደ አባቱ ቤት ተጓዘ። ከብዙ ጉዞ እና ድካም በኋላ በዚያ ደረሱ። ለዚህም ጠቢብ እረኛ እጅግ የሚወደው ገበሬው አባቱ እና እርሱ የሚያውቋት በጥበብ የምትጠበቅ የተዘጋጀችና የታተመች ጉድጓድ ነበረቻቸው። የዚህችንም ውሃ ማንም ጠጥቷል አያውቅም። ተከፍታም አታውቅም። ተጠብቃ በጥበብ ተመልታ ኑራለች። ይኸውም በጎ እረኛ ይህችን የታተመች ጉድጓድ መዘጋቷን ሳይከፍት እጅግ ልዩ በኾነ ጥበብ ውሃውን ከርሷ ቀድቶ ለበጎቹ አጠጣ። እኒህም በጎች ከዚህች ጉድጓድ የጠጡትን ውሃ ዓይነት ጠጥተው አያውቁምና እጅግ ስለወደዷት ከርሷ ሳይለዩ የርሷን ጥና ተጠግተው መኖር ጀመሩ። የዚህችንም የተዘጋች የታተመች ጉድጓድ ውሃ ሳይከፍታት አውጥቶ መስጠት የሚቻልበትን ጥበብ ከመልካሙ ገበሬ ታዛዥ እረኛና ከጠቢቡ መልካም ገበሬ አባቱ በቀር ማንም የሚያውቅ የለም።

 ይህችውንም ጉድጓድ እንዳታድፍ በንጽሕና አድርገው የሠሯትና ይጠብቋቸው የነበሩት እኒሁ መልካም ገበሬ እና እረኛ ነበሩ። የታተመች ኾና እንድትቆይም በጥበብ ይጠብቋት ነበር። ይቆየን።

 ተጻፈ 2008 ዓ.ም
 ጎንደር/ ኢትዮጵያ
 ዲያቆን መልአኩ ይፍሩ ዘውሉደ ብርሃን

ሐሙስ 8 ማርች 2018

1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1 Timothy 3
ምዕራፍ፡3፤
1፤ማንም፡ኤጲስ፡ቆጶስነትን፡ቢፈልግ፡መልካምን፡ሥራ፡ይመኛል፡የሚለው፡ቃል፡የታመነ፡ነው።
2፤እንግዲህ፡ኤጲስ፡ቆጶስ፡እንዲህ፡ሊኾን፡ይገ፟ባ፟ዋል፤የማይነቀፍ፥የአንዲት፡ሚስት፡ባል፥ልከኛ፥ራሱን፡
የሚገዛ፥እንደሚገ፟ባ፟ው፡የሚሠራ፥እንግዳ፡ተቀባይ፥ለማስተማር፡የሚበቃ፥
3፤የማይሰክር፥የማይጨቃጨቅ፥ነገር፡ግን፥ገር፡የኾነ፥የማይከራከር፥ገንዘብን፡የማይወድ፥
4፤ልጆቹን፡በጭምትነት፡ዅሉ፡እየገዛ፡የራሱን፡ቤት፡በመልካም፡የሚያስተዳድር፤
5፤ሰው፡ግን፡የራሱን፡ቤት፡እንዲያስተዳድር፡ባያውቅ፥የእግዚአብሔርን፡ቤተ፡ክርስቲያን፡እንዴት፡
ይጠብቃታል፧
6፤በትዕቢት፡ተነፍቶ፡በዲያብሎስ፡ፍርድ፡እንዳይወድቅ፥ዐዲስ፡ክርስቲያን፡አይኹን።
7፤በዲያብሎስ፡ነቀፋና፡ወጥመድም፡እንዳይወድቅ፥በውጭ፡ካሉት፡ሰዎች፡ደግሞ፡መልካም፡ምስክር፡
ሊኖረው፡ይገ፟ባ፟ዋል።
8፤እንዲሁም፡ዲያቆናት፡ጭምቶች፥በኹለት፡ቃል፡የማይናገሩ፥ለብዙ፡ወይን፡ጠጅ፡የማይጐመዡ፥
9፤ነውረኛ፡ረብ፡የማይወዱ፥በንጹሕ፡ኅሊና፡የሃይማኖትን፡ምስጢር፡የሚይዙ፡ሊኾኑ፡ይገ፟ባ፟ቸዋል።
10፤እነዚህም፡ደግሞ፡አስቀድሞ፡ይፈተኑ፥