ሰኞ 6 ኦገስት 2018

+++ ምክንያተ ጾመ ፍልሰታ +++

ውድ ኦርቶዶክሳውያን ወንድሞችና እኅቶች እንኳን ለወላዲተ አምላክ የፍልሰታ ጾም በሰላም አደረሳችሁ።

ጾመ ፍልሰታ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ሲሆን በብዙ ምእመናን ዘንድ በተለይም በሕጻናት እጅግ የምትወደድ የጾም ወቅት ናት። አጀማመሯንም በጥቂቱ ለማዘከር ያህል እንየው።

አዛኝት ማርያም ከእግረ መስቀሉ ለፍቊረ እግዚእ "ነዋ ወልድኪ- ነያ እምከ" ተብላ ከተሰጠችው በኋላ እስከእለተ እረፍቷ ድረስ የኖረችው ከርሱ ጋር ነበር። በዚህም ምክንያት ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉ ከሌሎቹ የተለየበትን ሲያስረዱን አበው፣ እመብርሃን ከዚህ ነባቤ መለኮት ከተባለ ሐዋርያ ጋር በመኖሯም የተነሳ የገለጥውችለት ምሥጢር ሳይኖር እንደማይቀር በመናገር ነው።

ከዚህ ሐዋርያ ጋር ከኒረችም በኋላ እንደምትሞት ጌታችን በነገራት ጊዜ፣ እመብርሃን ግን መሞትን እንደማትሻ ለልጇ ለፈጣሪዋ ነገረችው። እርሱም አረጋጋትና በሲኦል የሚሰቃዩትን ነፍሳት ስቃያቸውን ባሳያት ጊዜ ለነዚህስ አይደለም አንድ ሁለት ሞትም ልሙት በማለት ተናገረች። የተወደደች ነፍሷም ከሥጋዋ ጥር 21 እለት ተለይታ እመ ብዙኃን የዓለም ሁሉ የብርሃን መውጫ ምሥራቃችን አረፈች። ሐዋርያትም በዚህ አዝነው ሥጋዋን ሊያሳርፉ ይዘው ወደ ጌቴሴምኔ እየሄዱ ሳለ አይሁድ በቅናት ተነሱባቸው።

" ቀድሞ ልጇን ቀብረው ተነሳ ዐረገ እያሉ ሲያውኩን ነበረ። አሁንም እርሷን እንዲሁ እያሉ እንዳያውኩን ኑ ነጥቀን ሥጋዋን እናቃጥል" ብለው ወደ ሐዋርያት ሄዱ። ታውፋንያ የተባለውም ሰው እጁ የአዛኝት ሥጋ ያለበት የአልጋውን ሸንኮር እንደነካ መልአከ እግዚአብሔር ቀስፎት እጁ ከአልጋው ሸንኮር ላይ ተቆርጦ ቀረ። እመብርሃን አዛኝትም አማልዳው እጁ እንደነበረው ተመለሰለት። መልአኩም የእመብርሃንን ሥጋ እና ፍቊረ እግዚእን ይዞ በገነት ከእፀ ሕይወት ሥራ አኖራቸው።(አቤት መታደል! ቅዱስ ሐዋርያ በጌታህ የተወደድህ፣ በእናቱም እጅግ የተወደድህ፣ ከጌታህም ጉያ ከእናቱም እቅፍ ለቅጽበት ያልተለየህ፣ ምስጢራትን ለማወቅ የተመረጥህ ፍቊረ እግዚእ ልጆችህን በጸሎትህ አስበን።)

ሐዋርያትም ሁሉ በሆነው ነገር እጅግ አዝነው ሳለ ስለሆነው ነገር ዮሐንስ ድንግላዊ ሐዋርያ መጥቶ ነገራቸው። እነርሱን የእመብርሃን ሥጋ እንዲሰጣቸውና በክብር እንዲያሳርፉት ጸሎት ሱባኤ ይዘው ከነሐሴ 1-14 ሱባኤ እንደፈጸሙ ሥጋዋ ተሰጥቷቸው በይባቤ ግውንዘው ቀበሯት። በቅዱስ መጽሐፍ ላይ በነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት "ተንስእ እግዚኦ ውስተ እረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ- አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህም ታቦት" የሚል ትንቢት ተነግሮ ነበርና አዛኝትም በተቀበረች በሦስተኛው ቀን በ16 ተነስታ ስታርግ ሐዋርያው ቶማስ ከሕንድ አስተምሮ ደመናን እየጠቀሰ ሲመለስ ያገኛታል። በዚህን ሰዓት አዘነና "ልጅሽም ከትንሳኤው ምስጢር ለየኝ፥ ያንቺንም ትንሳኤሽን ሳላይ" ብሎ ሲያዝን እመብርሃን ርኅርኅተ ሕሊና ትንሳኤና ዕርገቷን ያየው እርሱ ብቻ መሆኑን ነግራው ለምስክርም መግነዟን ሰጥታ ላከችው።

ቶማስም የያዘውን ይዞ ሐዋርያትን ስለእመቤታችን ሲጠይቃቸው "ጥር አርፋ ነሐሴ ቀበርናት" አሉት። እሱም እንዳላወቀ ሁኖ "ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር እንዴት ይሆናል" ሲላቸው "አንተ ስለምን ትጠራጠራለህ፥ ቀድሞም የጌታችንን ትንሳኤ ተጠራጥረህ ነበር" ብለው ይዘውት ሊያሳዩት ወደ መቃብሯ ሄዱ። በዚያ ሲደርሱ ግን ድንግል አዛኝት የለችም ነበር። ሐዋርያትም አይሁድ እንደቀድሞው መጥተው ሥጋዋን የወሰዱባቸው መስሏቸው ሲያዝኑ ቶማስ ያየውን ሁሉ ነገራቸውና መግነዟን ለበረከት ተካፈሉት።

ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የእመብርሃንን ነገር ስትርግ አይቻታለሁ እያለ ይሰብክ ዘንድ ይችላል። ሌሎቹ ግን ቶማስ አየ ብለው ከመስበክ ውጪ ምንም ማለት አይችሉም ነበርና ለቶማስ የተገለጠው ምስጢር ለነርሱም እንዲገለጥላቸው ደግመው በዓመቱ ከነሐሴ 1 አንስተው ሁለት ሱባኤ ጹመው ነሐሴ16 እለት ጌታችን ራሱ ሠራዒ ካህን፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ተራዳዒ(ንፍቅ ካህን)፣ ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ ዋና ዲያቆን ሁነው ጌታችን ቀድሶ አቁርቧቸው የትንሳኤዋንና ዕርገቷን ምስጢር ገለጠላቸው።

እኛም ከትንሳኤዋ እና ከዕርገቷ በረከትን ለማግኘት፣ ምስጢራት እንዲገለጡልን፣ መፍትሔ ለማግኘት በናፍቆት እና በፍቅር እንጾማታለን። አምላከ ቅዱሳን ከቅድስት እናታችን ረድኤትና በረከት ይክፈለን።

©ዲያቆን መልአኩ ይፍሩ ዘውሉደ ብርሃን
ሐምሌ 30/2010 ዓ.ም
አዳማ/ኢትዮጵያ