ሐሙስ 12 ኤፕሪል 2018

¶ ትምህርት ከቅዱስ ሄርማስ ኖላዊ


+ + + እግዚአብሔርን ስለመፍራት እና ዲያብሎስን ስላለመፍራት + + +

"እግዚአብሔርን ፍራ" አለኝ "ትእዛዛቱንም ጠብቅ። የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በመጠበቅህ በምታደርገው ኹሉ ላይ ኃይልን ትጎናጸፋለህ፤ የምታደርጋቸውም ኹሉ ወደር አይገኝላቸውም። እግዚአብሔርንም በመፍራትህ ነገሮችን ኹሉ በሚገባ ታከናውናለህ። ትድን ዘንድ እንዲህ ያለውን መፍራት ነው ገንዘብ ማድረግ የሚገባህ። ዳሩ ግን ዲያብሎስን አትፍራ፤ በርሱ ዘንድ ምንም ኃይል የለውምና እግዚአብሔርን በመፍራትህ በርሱ ላይ ትሰለጥንበታለህ። ነገር ግን በርሱ ዘንድ ኃይል የሌለው ያ መፈራት ያለ'ው አይደለም(መፈራት የለውም) ፤ ዳሩ ግን በርሱ ዘንድ ድንቅ ኃይል ያለው እርሱ በእውነት ይፈ'ራ ዘንድ አለ'ው። ኃይል ያለው ኹሉ መፈራት አለውና። ኃይል የሌለው ግን በኹሉ ዘንድ የተናቀ ይኾናል። ስለዚህም የከፉ ናቸውና የዲያብሎስን ሥራዎች ኹሉ ፍራ፤ እግዚአብሔርን ስለምትፈራ እኒህን (የዲያብሎስ ሥራዎች) አታደርጋቸውም፤ ከእነርሱ ራስህን ትጠብቃለህ እንጂ። ፍርሐት ኹለት ወገን ነው።

ክፉ የኾነውን ሥራ እንዳትሠራ ብትሻ እግዚአብሔርን ፍራ( ስለዚህም) ክፉውን ሥራ አትሠራውም፤ ዳግመኛም መልካም ሥራን ለመሥራት ብትሻ እግዚአብሔርን ፍራ፤ ስለዚህም መልካሙን ሥራ ትሠራለህ። በዚህም እግዚአብሔርን መፍራት ብርቱ፣ ታላቅና ድንቅ ነው። ስለዚህም እግዚአብሔርን ፍራ እናም ለርሱ ትኖራለህ፤ በቻልኸው ኹሉ መጠን እርሱን ፍራ ትእዛዛቱንም ጠብቅ ለእግዚአብሔርም ትኖራለህ።" "ለምን" አልሁ እኔም። "ጌታዬ፣ ለእግዚአብሔር ይኖራሉ ያልኸው ትእዛዛቱን ጠብቀው ስለሚኖሩት ነውን?" እርሱም እንዲህ አለኝ። "ምክንያቱም" "ፍጥረታት ኹሉ እግዚአብሔርን ይፈሩታል፤ ነገር ግን ትእዛዛቱን ኹሉም አይጠብቁም። እርሱን እግዚአብሔርን የሚፈሩት እና ትእዛዛቱንም የሚጠብቁት እነዚያ ከእግዚአብሔር ጋር በሕይወት መኖር አላ'ቸው፤ ዳሩ ግን ትእዛዛቱን በማይጠብቁት ለነርሱ ግን ሕይወት የላቸውም።"

ምንጭ፥the Shepherd of Hermas, Book two, commandment seven
አማርኛ ትርጉም፥ ዲያቆን መልአኩ ይፍሩ

©ዘዲያቆን መልአኩ ይፍሩ ዘውሉደብርሃን
            መጋቢት 18-2010 ዓ.ም
            አዲስ አበባ/ ኢትዮጵያ