ቅዳሜ 6 ጃንዋሪ 2018

በእንተ ተሠግዎተ ቃል



ቅዱስ አትናቴዎስ እንዳስተማረው
ትርጉም፥ ዲያቆን መልአኩ ይፍሩ ዘውሉደ ብርሃን
(ምንጭ፥ on incarnation, St Athanasius of Alexandria፣Ch. 3)

ቃል፣ ሙስና በሞት ካልሆነ በቀር ጨርሶ መጥፋት እንዳይችል አየ። እርሱ ደግሞ አካላዊ ቃል የአብ ልጅ ኢመዋቲ [ሕያው] ነውና ሞትን በባህርዩ ሊሞት አይችልም [ለባህርዩ አይስማማም] ። በዚህ ምክንያት፤ መዋቲ ሥጋን ከሁሉ በላይ ከሆነው ከርሱ(ከቃል ጋር) በማዋሐድ [የቃል በማድረግ] ሥጋ ሌሎች ሁሉ መሞት የሚገባቸውን ሞት መሞት ይችል ዘንድ፤ ያ ሥጋ ግን ከአካላዊ ቃል ተዋሕዶ የተነሳ በኢሙስና (ባለመፍረስ) እንደገና ሕያው ኹኖ ለሌሎቹም ኹሉ ከዚያ በኋላ ሙስናን በትንሳኤው ግርማ ፍጻሜውን ያደርግለት ዘንድ [ፈጽሞ ያጠፋው ዘንድ አሰበ] ።

ይህም የነሳውን ሥጋ ለሞት አሳልፎ በመስጠት ለኃጤአት ሁሉ [ለሁሉም ሰው እድፍ] ያለ ምንም ዋጋ የቀረበ መሥዋእትና አምሃ በማድረግ ወዲያውኑ የሚገባውን ካሳ በመክፈል ከወንድሞቹ የሰው ልጆች ሁሉ ሞትን አጠፋ። በባህርይ፤ ቃለ እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ነውና ፤ስለሁሉም ሕይወት [በምትኩ] አሳልፎ ሲሰጥ በሞት የሚጠበቅበትን ሁሉ አሟልቷል። ዳግመኛም በባህርይ፡ለሰው ሁሉ ጥቅም ፡በቃል በአንድ ሥጋ ውስጥ ማደር ምክንያት ሞትን ተከትሎ የሚመጣው ሙስና በሙሉ ላይ ያለውን ኃይሉን አጣ።

ዛሬ አንድ ትልቅ ንጉሥ ትልቅ ከተማ ውስጥ ሲገባ የሚቀመጠው በአንድ ቤት ውስጥ ብቻ ነው። ዳሩ ግን በርሱ እዚያች ከተማ መግባት የተነሳ ሙሉ ከተማው ይከበራል ጠላቶችና ሌቦችም አስመስለው ለመኖር ይሞክራሉ [ያልተረበሹ መስለው] ። ለሞት ፍጻሜ ያደርግለት ዘንድ ሰዎችም ፈጽመው እንዳይጠፉ [ከፍጹም ጥፋት እንዳይደርሱ] ጌታ እና የሁለም አዳኝ የእግዚአብሔር ልጅ እኛ ዘንድ መጣ። ይህ ታላቅ ሥራ በርግጥ ከእግዚአብሔር ሊነገር ከማይቻለው በጎነቱ የተነሳ የሆነ ነው። አንድ ንጉሥ በነዋሪዋቹ ንዝህላልነት የተነሳ የተዋትን ከተማ ከጊዜያት በኋላ በሌቦች ተጎድታ ባገኛት ጊዜ ጉዳቷን ቢበቀልላት እና ከመጥፋት ቢታደጋት ስለራሱ ክብርና ጌትነት እንጂ ስለሕዝቡ ቸልተኝነት አይደለም።
ከዚህም በበለጠ ፡መልካሙ የእግዚአብሔር አብ ቃል ሰው ተብሎ የተጠራው ሳይውል ሳያድር ቀርቶ አይደለም። በራሳቸው ላይ ያመጡትን ሞት የራሱን አካል አሳልፎ በመስጠት አጠፋላቸው፤ ቸልተኛውነታቸውንም በትምህርቱ አስተካከለ እንጂ።

በዚህም ታዲያ በራሱ ኃይል የሰውን መላ ፍጥረቱን [ባህርዩን] ዳግም መለሰለት፣ አደሰለት። በሚከተሉት ጥቅሶችም የምናረጋግጠው ይህንኑ ነው
“ይህን ስለቆረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፤” [2ቆሮ5፡12]

“ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ፥ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስን ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና የምስጋናን ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን።” [ዕብ2፡6]

ከልደቱ በረከትና ረድኤትን ይክፈለን።
ወደፊት እግዚአብሔር እንደፈቀደ ሙሉውን ትርጉም ለማንበብ የበቃን እንድንኾን የቅዱሳኑ ጸሎት አይለየን። በጸሎታችሁ አስቡኝ።