እሑድ 6 ኦገስት 2017

“ኢትብልኡ ሥጋ ዘእንበለ ዓሣ” /ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 15/


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

ጾም ፦ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ የምናስገዛበት ምግባር ነው። ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ሥጋ በመንፈስ ላይ ሊሰለጥን እንደሚታገሉ ገልጦልናል። እንዲሁም ”ቅንኡ ለእንተ ተአቢ ጸጋ-ለምትበልጠው ጸጋ ቅኑ/ትጉ/” በማለት ስለነገረን የሥጋን ፈቃድ በነፍስ ፈቃድ ድል አድርገን ለነፍስ ለማስገዛት ልንተጋ ያስፈልጋል።
      ጾም እና መባልእት /ምግቦች/
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረት በጾም ወራት የምንመገባቸው እና
የማንመገባቸው ምግቦች አሉ። ለዚህም መሠረት የሚሆነን ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፦
“ጉልበቶቼ በጾም ደከሙ ሥጋዬም ቅቤ በማጣት ከሳ” /መዝ108(109) ፡24/
በማለት የሚነግረን ነው። ሌሎችም ይህን የመሰሉ መሠረት የሚሆኑን የቅዱስ መጽሐፍ ቃላት አሉ።
    ሀ/በጾም ወቅት የማይበሉ መባልእት፦
በወርኃ ጾም የማይበሉት መባልእት ጥሉላት ነክ የሆኑ ምግቦች ናቸው። የእሊህም ምግቦች መከልከል ምክንያት ሰውነታችንን የሚገነቡ እና ለሰውነት መታደስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው መባልእት ስለሆኑ ነው። በዚህም ውስጥ ሥጋ፣ ቅቤ፣ ወተው፣ ወዘተ የመሰሉትን ይካተቱበታል።በሥጋ ሥር የዓሳን ጉዳይ እንደሚከተለው እንመልከት።
ዓሣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ ለብዙ ጊዜያት ሲያከራክር የቆየ ጉዳይ ነው። ይህም ሠለስቱ ምእት በፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 15 ላይ “ኢትብልኡሥጋ ዘእንበለ ዓሣ”ያሉትን በመያዝ ነበር የሚከራከሩት።

 አንዱ ወገን “ዘእንበለ ዓሣ”የሚለውን ከዓሣ በቀር ሌላ ሥጋ አትብሉ የሚል ሲሆን
 ሌላኛው ደግሞ “ዘእንበለ ዓሣ”የሚለውን ዓሣንም ጨምሮ ሥጋ አትብሉ የሚል ነው።

የ“ዘእንበለ ዓሣ”ትርጉም ሁለት አይነት ስለሆነ እንዲህ ክርክር ሊያስነሳ የሚችል ቢሆንም እንኳን ለምሳሌ ያህል በወርኃ ጾም ዓሣን እንዳንበላ የሚያደርጉን ሁለት መሠረታዊ ምክያቶችን እንመልከት።
     ምክንያት 1/ በዚህ አንቀጽ “ዘእንበለ ዓሣ” ተብሎ የተነገረው ክርክር ቢያስለሳም እንኳን ሠለስቱ ምእት በሌላ አንቀጽ “ለእመ ተገዓዝክሙ በጾም አድልዉ ለጾም-በጾም ምክንያት በተከራከራችሁ ጊዜ ለጾም አድሉ” በማለት ተናግረዋል።
ስለዚህም ለዚህ ክርክር መቋጫው የምናደርገው ለጾም ማድላትን ነው። ስንኳን በጾም ወራት፣ በመደበኛው ቀንም ቢሆን ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “ሥጋ መብላቴ ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ ሥጋ ባልበላ ይሻለኛል” ብሏል።
     ምክንያት 2/ ዓሣ በውስጡ የያዛቸው ንጥረ ምግቦች/nutrients/ በሳይንሱ ዓለም የተደረጉ ጥናቶች እንዳረጋገጡትእጅግ ገንቢና ጠጋኝ የሚባሉ ናቸው። የጾመ መሠረታዊው ዓላማ ደግሞ ቅዱስ ዳዊትም እንደተናገረው ሥጋን ማድከም እና ነፍስን በሥጋ ላይ በምግባር ማሠልጠን ማበርታት ስለሆነ የዓሣ ሥጋን መመገብ ደግሞ ከዚህ የጾም ጋር ፈጽሞ አትስማማም።
በጾም ወቅት ዓሣን መመገብ ማለት ሥጋን ለነፍስ ፈቃድ አስገዛለሁ ብለው እየደከሙ ዳሩግን ይህን ድካም መልሶ ከንቱ ማድረግ ነው። ስንኳን የዓሣ ሥጋ ይቅርና ከአትክልት ምግቦችም፣ ከጥራጥሬም ቢሆን ሰውነትን የሚያበረታታ እና እጅግ ገንቢ ጠጋኝ የሆኑ ምግቦችን በተለይም በጾም ወቅት ከመመገብ ልንከለከል ያስፈልጋል። እንዲህ ካላደረግን ሥጋችንን ለነፍሳችን እናስገዛለን ብለን የምንሠግደው ሥግደት፣ የምንጸልየው ጸሎት የምናለቅሰው ልቅሶ ከንቱ ድካም ይሆንብናል።
እግዚአብሔር የሚወደውን አይነት ጾም ጹመን የጾሙን በረከት ያድለን ዘንድ የቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት ይርዳን።
ምንጭ፦ መርሐ ጽድቅ ባህለ ሃይማኖት
፦ፍትሐ ነገሥት
ወስብሐት ለእግዚዕብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።
ይቆየን።
©ዘዲያቆን መላኩ ይፍሩ
ሰኔ 29/2009 ዓም
አዲስ አበባ/ ኢትዮጵያ

ዓርብ 4 ኦገስት 2017

+++ ደጆችሽ አይዘጉ እና የሚሠራቸው ሥራዎች+++




በቅድሚያ ስለመዘግየቴ ይቅርታችሁን እጠይቃለሁ። በመቀጠልም ቃል የገባሁላችሁን የደጀችሽ አይዘጉ ማኅበር አመሠራረት፡ ሥራ እና እንዴት መሳተፍ እንደሚቻል ቀጥሎ መጻፍ እጀምራለሁ።
በ1998 ዓ.ም በረከተ ቅዱሳንን ለመቀበል ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ መስመር በአንድ መኪና የሞሉ ምእመናን ጉዞ ጀመሩ። ጉዟቸውን በሰላም እንዲያስፈጽማቸው በእምነት በልባቸው እየጸለዩ እየተጓዙ ሳለ ከአዲስ አበባ 235 ኪሎ ሜ ርቀት ላይ ከምትገኘው ናትሪ ከተማ ሲደርሱ ከባድ የሆነ ዝናብ ስለያዛቸው ጉዟቸውን መቀጠል አልቻሉም። በዚህም የተነሳ ዝናቡ እስኪያባራላቸው በዚያውም ቅድስት ቤተክርስቲያንን ለሳለም ወደ ናትሪ ደብረ  ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ጎራ ይላሉ።
        ምእመኑም በዚያ ያየው እጅግ የሚያሳዝን ነገር ነበር። የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅኔ ማኅሌት በላስቲክ ተሸፍኖ፤ መቅደሱ መካነ መቃብር ሁኖ ነበር ያገኙት። በዚህም ልቡናቸው ፍጹም አዝኖ እርስ በርሳቸው በመተባበር እና የአካባቢውን ምእመናን በማስተባበር የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ አዋቅረው የናትሪ ደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያንን ሕንጻ አሠሩ።
        ሥራው እንደጠናቀቀ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑትን ብጹእ አቡነ እስጢፋኖስን ጠርተው ሕንጻውን ሲያስረክቡ ብጹእነታቸው የወጣቶቹን ትጋት ተመልክተው በማበረታታት ሌሎችን ጨምሮ 142 አቢያተ ክርስቲያናትን በአደራ አስረከቧቸው። ማኅበሩም ከዚህ በኋላ ከ2000 ዓም አንስቶ ኢይትአጸዋ አናቅጽኪ -ደጆችሽ አይዘጉ” ተብሎ ሥራውን በትጋት ቀጠለ።
በ2002 ዓም ቅዱስ ፓትርያርኩ በተገኙበት ልዩ የገቢ ማሰባሠቢያ መርሐ ግብር በሚሊኒየም አዳራሽ በማዘጋጀት ያገኘውን ገቢ ተጠቅሞ አቢያተ ክርስቲያናቱን የሚደግፍ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ ” የሚባል ፕሮጀክት ቀርጾ መንቀሳቀስ ጀመረ። ይህም አንድ ሰው በ800 ብር ማለትም የአንድ ካህንና የአንድ ዲያቆን ደመወዝ የሚሸፍንበት የአገልግሎት ሱታፌ መንገድ ነው። በዚህም ላለፉት አሥር አመታት የክርስቲያናዊ ቤተሰብ ”ን ጨምሮ ሰባት ፕሮጀክቶችን ቀርጾ በሦስት ዓላማዎች ላይ ጸንቶ በመሥራት ቆይቷል።
የማኅበሩ ዓላማ
ሀ/ የተዘጉ አቢያተ ክርስቲያናትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተከፍተው አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ።
ለ/ በልማት ራሳቸውን በማስቻል ማስተሳሠር።
        + አቢያተ ክርስቲያናት ራሳቸውን በራሳቸው በልማት ከደገፉ በኋላ ሌሎች አቅም የሌላቸውን አቢያተ ክርስቲያናት እንዲደግፉ ማድረግ
ሐ/  ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት።
        + ይህ ዓላማ ስብከተ ወንጌልን እንዲሁ ማስፋፋት ታስቦ የታቀደ ሳይሆን በራሳቸው ቋንቋ መስበክ የሚችሉ መምህራንን በማፍራት ምእመኑን ወንጌልን በራሱ ቋንቋ መማር እንዲችል የሚያደርግ ትልቅ ዓላማ ነው።
        + አንድ ሰውን በማያውቀው ቋንቋ ከምናናግረው ይልቅ በራሱ ቋንቋ እና ባህል ተጠቅመን ስናስተምረው ባህሉን ወጉንና ቋንቋውን በቅርብ ስለሚያውቀው ከልቡ ዘልቆ የገባዋል። ለዚህም ነው ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን አበው በትርጓሜያቸው ላይ ኢየሩሳሌምን፤ ደብረ ታቦርን  በልደታ ቤተክርስቲያን/ጎንደር/ በሀገራችን ወንዞች ተራሮች እያደረጉ መስለው የሚያሳዩን።
        + ከዚህም ባሻገር ምእመኑን በራሱ ቋንቋ ማስተማር፤ ቋንቋን በመጠቀም ሠርገው ከሚገቡ ተረፈ አርዮሳውያን መታደግ ያስችላል። /ሐዋርያት በበአለ ሃምሳ ያደረጉትን ልብ በል/
በማኅበሩ እየተሠራባቸው ያሉ ፕሮጀችቶች
ማኅበሩ የሊማት 3 ፕሮጀክቶችና ሌሎች 4 ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ በ7 ፕሮጀክቶች እየሠራ ይገኛል። እሊህም፦
        1/ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ፦ ይህ ፕሮጀክት አንድ ቤተሰብ የአንድ ካህን እና የአንድ ዲያቆን ደመወዝ የሚሸፍንበት መንገድ ነው።
        2/ኤርጋሞታ፦ ይህ ደግሞ  በቋንቋቸው የሚያስተምሩ መምህራነ ወንጌልን የሚያፈራ ፕሮጀክት ነው።ለዚህም የሚሆን ሕንጻ በናትሪ ደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ አሠርቷል። ለመጀመሪያ ጊዜም በዚህ ትምህርት ቤት 44 መምህራንን አስመርቆ በጅማ ሀገረ ስብከት በ17ቱም ወረዳዎች አሰማርቶ በአገልግሎት ላይ ይገኛሉ። በአሁኑ ጊዜ ግን ይህን ሥራ ቤተክህነት ተረክቦ እየሠራው ይገኛል።
        3/ናቡቴ ፦ይህ ፕሮጀክት ሦስት ክፍሎች አሉት፦
                ሀ/ የንብ እርሻ፦ ወደ 30 የሚጠጉ አቢያተ ክርስቲያናት የሚጠቀሙበት ነው።
                ለ/ የራስ አገዝ ሕንጻ፦ በአሁኑ ሰዓት በጅማ ዋና ከተማ እያሠራው ያለ ሕንጻ ሲሆን ለሕንጻው ማሠሪያ ቦታውን  ከአንድ ክርስቲያናዊ አባት በ750 ሺህ ብር በመግዛት ነው ያገኘው። የግንባታ ፈቃድ ለማግኘትም ትልቅ ትዕግስትን የጠየቁ ከ4 ዓመታት በላይን ፈጅቷል።
                ሐ/ የቡና እርሻ፦ ሊሙ ኮሳ በተባለ ሥፍራ የሚበኝ 26 ሄክታር የሚሸፍን የቡና እርሻ ነው።
        4/ጥበበ ባስልኤል ፦ይህ ፕሮጀክት ምእመናን ሙያቸውን በዓመት አንድ ጊዜ ለቤተክርስቲያን የሚያውሉበት ነው። ሊስትሮዋች፤ ዶክተሮች፤ ኢንጅነሮች፤ የጽዳት ሠራተኞች፤ በየትኛውም የሙያም ሆነ የዕውቀት ደረጃ ላይ ሚገኙ ባለሞያ ምእመናን ሞያቸውን በዓመት አንድ ጊዜ ለቤተክርስቲያን በማዋል አቢያተ ክርስቲያናትን ይደግፋሉ።
        5/መዝገበ ሰማይ ፦በሌላ አጠራር አክስዮን በማለት የምናውቀው ሲሆን ባለ1ሺህ እና ባለ3 ሺህ አክስዮን የሚገዛበት ነው።
        6/ፕሮጀክት ሎዛ ፦ይህ ደግሞ አንድ ብር ለአንድ ቤተክርስቲያን በሚል መሪ ቃል የሚሠራ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ማሻሻያ ተደርጎበት በአዲስ መልኩ ሥራው ተጀምሯል።
        7/ትሩፋተ ወንጌል
        በአጠቃላይ ማኅበሩ እንዲህ ያሉ በጎ መንፈሳዊ ሥራዎችን እየሠራ ያለ የቤተ ክርቲያን ልጅ ነው።እኛም ሁላችን የክርስቶስ ልጆች የሥላሴን ልጅነት የምናገኝባት፤ ሥጋ ወደሙን የምንቀበልባት፤ እናም ቅዱሱን የእግዚአብሔርን ቃል የምንማርባትን ቤተክርስቲያን በጸሎትም ለማሰብ እና በትጋት ለማገዝ በፍጹም ጥብዓት እንደ ቅዱስ ጳውሎስና እንደ ቅዱስ ዳዊት በመትጋት ልቆም ያስፈልጋል።
        በአገልግሎቱ ለመሳተፍና አቢያተክርስቲያናቱን ለማገዝ በማኅበሩንም ለመሳተፍ ከልብ የሆነ መሻት ብቻ ነው የሚያስፈልገው።
የማኅበሩ አድራሻ፦ ሃያ ሁለት ቅዱስ ዑራኤል ሕንጻ 4 ፎቅ ቢሮ ቁጥር
                ስልክ ቁጥር፦ 0913067122/0472111515
©ዘዲያቆን መላኩ ይፍሩ
ሐምሌ 28 2009 ዓም
አዲስ አበባ፡ ኢትዮጵያ